Friday, June 2, 2023

ቻይናን ማዕከል ያደረገውን የአሜሪካ ፖሊሲ ይዘው የመጡት ማይክ ፖምፒዮና የኢትዮ አሜሪካ ግንኙነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት የጀመሩት ከመቶ ዓመት በፊት በዳግማዊ ምንሊክ የንግሥና ዘመን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ባላት ቅርበት የተነሳ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ስላላት እንወዳጃት ብሎ የወቅቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዥቬልት የወተወተው ዕውቁ የአሜሪካ ዲፕሎማት ሮበርት ስኪነር፣ የመጀመርያው የአሜሪካ ለንግድና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያለመ ዲፕሎማት ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ተላከ፡፡ ይኼም ግንኙነት ግቡ ያደረገው ከአሜሪካ ቀድመው በቅኝ ግዛት ከአፍሪካ ጋር ግንኙነት የጀመሩት የአውሮፓ አገሮች በመሆናቸው፣ አሜሪካ በዚህ ሳቢያ ያጣችውን የግንኙነት ዕድል ማካካስ ነበር፡፡

በእነዚህ መቶ ዓመታት አሜሪካ በብዛት በኢትዮጵያና በቀጣናው ብቸኛ የኢኮኖሚ፣ የመከላከያ፣ የደኅንነትና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተደማጭነትና ተመራጭነትን አግኝታ የቆየች ሲሆን፣ ጉልህ ተፅዕኖ ያለው የውጭ ተቀናቃኞች በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ በእነዚህ ዘርፎች አልተገኙም፡፡

በደርግ መንግሥት ዘመን ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ግፊት ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ያጋደለ የፖለቲካ ግንኙነት በመመሥረት ከሩሲያ ጋር ጠንከር ያለ ወዳጅነት መፍጠር ብትችልም፣ በአሜሪካ ግፊትም ሆነ ቀጥተኛ ተሳትፎ የደርግ መንግሥት አጭር ዕድሜ እንዲኖረው ተደርጓል ሲሉ ምልከታቸውን የሚያጋሩ አሉ፡፡

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት በብዛት በመከላከያና በደኅንነት ዘርፎች ላይ በማተኮር የዘለቀ ሲሆን፣ በኢኮኖሚ ረገድ ኢትዮጵያም ሆነች የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ይኼ ነው የሚባል ጥምረት ከአሜሪካ ጋር ፈጥረዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀ ግንኙነት ያላት አሜሪካ በዕርዳታና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በብድር አቅርቦት ሊስተካከላት የሚዳዳ አንድም የምዕራብም ሆነ የምሥራቁ ዓለም ጎራ ማግኘት ዘበት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የእኛ ሥሪት ናት፤›› እስከ ማለት የደረሰ ትምክህት በአሜሪካ ዘንድ አለ የሚሉ አጥኚዎች አሉ፡፡

ከሞላ ጎደል የአሜሪካ መንግሥት ፕሬዚዳንቶች በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀያየር ፖሊሲ በኢትዮጵያና በቀጣናው ይዞ የቆየ ሲሆን፣ በመከላከያና በደኅንነት ዘርፎች በመረጃ ልውውጥና በመሣሪያ አቅርቦት ረገድ አሜሪካን የሚስተካከል አጋር ማግኘት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያ የሚታሰብ አልነበረም፡፡

ከእነዚህ የደኅንነት ዘርፍ ግንኙነቶች በተለየ ግን በንግድና በኢንቨስትመንት ረገድ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ. በ2015 የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ 834 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ 80 በመቶ ያህል ወደ አሜሪካ ያጋደለ ጉድለት ያለው ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ረገድም የአሜሪካ ኩባንያዎች ባላቸው የኢንቨስትመንት ቁጥርም ይሁን የመዋዕለ ንዋይ መጠን ከሚጠቀሱ አገሮች አሥረኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ነች፡፡ ስለሆነም በኢኮኖሚ አቅምም ሆነ በፖለቲካ ተፅዕኖ አነስተኛ ተደማጭነት ያላቸው አገሮች ከአሜሪካ ቀድመው በእነዚህ ዘርፎች ጉልህ አሻራ ማሳረፍ ችለዋል፡፡

ይኼ ሆኖ ሳለም እምብዛም የተፅዕኖ ማጣትና የተሰሚነት መቀነስ ያልተሰማት አሜሪካ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ አኅጉር ያላት ሥፍራ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ እንደሆነ የተረዳችና ሥጋትም የገባት ይመስላል፡፡

የዓለም የኃይል ግንኙነት አሠላለፍ ቅኝት ከጂኦ ፖለቲክስ ወደ ጂኦ ኢኮኖሚክስ እየተለወጠና በኢኮኖሚ ጠንካራ መሆንና በኢኮኖሚያዊ ትስስሮች መጋመድ ቀዳሚው ስትራቴጂ በሆነበት ግሎባላይዜሽን፣ የአሜሪካ የተለመደ አካሄድ (Business as Usual) የማያስኬድ መሆኑን በተለይ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በግልጽ ማመላከቻዎች እየታዩ የመጡ ይመስላሉ፡፡

የአርባ ዓመታት የቻይና የኢኮኖሚ ተዓምር ድህነትን ከመቀነስ፣ በቴክኖሎጂ ራስን ከመቻል፣ በወጪ ንግድ ግዙፍ አዎንታዊ ገቢ ከማስገኘት፣ በርካታ ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮችን ከማፍራትና ጠንካራ የማስፈጸም አቅም ከመገንባት በዘለለ፣ ባለ አንድ አጥቅ (Uni-Polar) የዓለም ሥርዓት ወደ ባለ ብዙ አጥቅ (Multi-Polar) የዓለም ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ያፋጠነው ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት አገሮች ለማንኛቸውም ተግባራት ወደ አሜሪካ ወይም በምዕራብ አውሮፓ ወደሚገኙ አጋሮቿ ብቻ ከመሮጥ በተጨማሪ፣ አማራጮችን ለማየትና ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችል ሥርዓት መታየት ጀምሯል፡፡ ይኼም ጅምር በዓለም አቀፍ ፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ አነስተኛ አቅም ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የእስያ አገሮች የፖሊሲ ነፃነትን ማጣጣም እንዲችሉ የሚያስችል በር የከፈተ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

ቻይና በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በኢንቨስትመንትም ሆነ በንግድ ግንኙነት የሚስተካከላት የውጭ አጋር አለመኖሩ አሌ የማይባል ሀቅ ሲሆን፣ ለአፍሪካ ምርቶች አስተማማኝ መዳረሻና ለአፍሪካ የኢንቨስትመንት ፍላጎት የተዘረጋ እጅ፣ እንዲሁም ለአፍሪካ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የገንዘብ ምንጭ ሆናለች፡፡ በዚህም ሳቢያ በሚገነቡ ወደቦች፣ መንገዶች፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ የባቡር መስመሮች፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያዎች የቻይናን አሻራ ማግኘት ቀላል ነው፡፡

የቻይና የውጭ ግንኙነትም ደረጃ የተበጀለትና ትኩረት ያለውና የኢትዮ ቻይና ግንኙነትም ወደ ከፍተኛ ደረጃ ግንኙነት ያደገ ሲሆን፣ የቻይና ኢንቨስትመንት ካለባቸው አገሮች በበለጠ የፕሮጀክቶች ብዛትና የአፈጻጸም ብቃት በኢትዮጵያ እንደሚታይ መላኩ ሙሉዓለም የተባሉ ጸሐፊ ለሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ በጻፉት ጽሑፍ አስረድተዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፎች ብቻ ሳይሆን ቻይና በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች የመከላከያና የደኅንነት መሣሪያዎችን በማቅረብ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተች ስትሆን፣ ለቴሌኮም አቅርቦትም ሆነ መከታተያ መሣሪያዎችን ለአፍሪካ አገሮች በማቅረብ ሁለቱ የቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች ሁዋዌና ዜድቲኢ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅርብ ዓመታትም ቻይና በዕርዳታ ረገድ ሚናዋን መጫወት የጀመረች ሲሆን፣ ቻይና ኤይድ በተባለው ተቋም አማካይነት የልማት ድጋፍ ሥራዎችን በስፋት ታከናውናለች፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎችም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ግፊት ይደረግባቸዋል፡፡

ሆኖም ከአካባቢ ጥበቃና ከፍተኛ በሆነ ብድር ተበዳሪዎችን ለመዝፈቅ ያለመ አዳኝነት የሚታይበት ሥልት ትጠቀማለች በማለት ምዕራባውያኑ ቻይናን ይወቅሷታል፡፡ ለዚህም ቻይና እያስፋፋች ያለችው የቤልት ኤንድ ሲልክ መንገድ ኢንሼቲቭ በመሣሪያነት ያገለግላል ሲሉ ይተቻሉ፡፡

ይኼ ትችትና ሥጋት በዋናነት የብድሩን የንግድ ግንኙነቱ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ግንባታው ተጠቃሚ ከሆኑት የአፍሪካና የሌላ አኅጉር አገሮች የሚደመጥ ሳይሆን፣ ከምዕራቡ ዓለም በተለይም ከአሜሪካ የሚመጣ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የአሜሪካ መንግሥት ከቻይና ጋር ያሉ ግንኙነቶችን ለመተቸት ያገኘነውን መድረክ ሁሉ የሚጠቀመው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው የኢትዮጵያ ዋና መዲና አዲስ አበባ የቻይና ኢንቨስትመንት ቀዳሚ መዳረሻ ከሆነች በኋላ ነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊጎበኛት የፈቀደው፡፡ ይኼም ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የአኅጉሪቱን ወይም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ካነገበ ዓላማ የመነጨ ሳይሆን፣ አሜሪካ በቻይና ጉልህ እንቅስቃሴ በገባት ሥጋት ሳቢያና ያንን ለመቀልበስ በሚደረግ ጥረት ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡

የአሜሪካ የአፍሪካ ፖሊሲ ከአሁን ቀደም በነበሩ ፕሬዚዳንቶች ዘመን በዕርዳታና በልማት ፕሮግራሞች፣ እንዲሁም በፀጥታና በደኅንነት ዘርፍ በፀረ ሽብር አጋርነት ግልጽ የሆነ መስመር የነበረው ቢሆንም፣ በተለይ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አፍሪካ ለአሜሪካ ያላት ሥፍራ የት ዘንድ ነው ለሚለው ጥያቄ አንድ መልስ ለመስጠት ያዳግታል፡፡ ለዚህም ይመስላል በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሥር የሚመጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይኼንን በማብራራት የሚጠመዱት፡፡

በፕሬዚዳንቱ የሦስት ዓመት ከመንፈቅ የሥልጣን ዘመንም በአስተዳደሩ ከፍተኛ  ባለሥልጣን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሁለተኛው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፣ አስቀድመው በሴኔጋልና በአንጎላ ጉብኝት አድርገው ነው ሰሞኑን ኢትዮጵያን መዳረሻቸው ያደረጉት፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት የአፍሪካ ጉብኝት ሲያደርጉ በነበሩበት ወቅት ከሥልጣናቸው በመነሳታቸው ጉዟቸውን ያቋረጡት፣ የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር የተመለሱት፡፡

የማይክ ፖምፒዮን ጉብኝት በአጽንኦት የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ ተንታኞችና ታዛቢዎች፣ ጉብኝቱ የተደበላለቀ መልዕክት ያዘለ መገለጫ አለው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በዋናነነት ለአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ሥጋት የሆነችው ቻይና በአፍሪካ ያላትን ሥፍራ ሚዛን ለመድፋት የሚደረግ ሩጫ እንደሆነ ዕሙን ነው ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

በዚህ ረገድ ግን አሜሪካ ምን የተለየ አማራጭ ይዛ ብትመጣ ነው ይኼንን የቻይና የአፍሪካ ተፅዕኖ ልትገዳደር የምትችለው ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ በተለይ በኢንቨስትመንቱ ረገድ አሜሪካ የቻይናን ያህል መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደማትችል፣ እንዲሁም የአሜሪካ የግል ድርጅቶች የተለያዩ የፖለቲካና አካባቢያዊ ሥጋቶች ዋስትና ከመንግሥት ማግኘት ካልቻሉ ገንዘባቸውን ማውጣት ስለማይፈቅዱ፣ አሜሪካ በዚህ ረገድ ስኬት ለማስመዝገብ ያስቸግራታል ይላሉ፡፡

ከዚህ በላይም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ከቻይና ገበያና ኢኮኖሚ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑና ሊተካ የማይችል በመሆኑ፣ ቻይናን ከኢትዮጵያም ሆነ ከተቀሩት የአፍሪካ አገሮች መነጠል የማይታለም መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ከየትኛውም የዓለም ክፍል በበለጠ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ወደ ቻይና በብዛት መጓዛቸው፣ እንዲሁም የአፍሪካ ገበያ በቻይና ምርቶች የተጥለቀለቀ በመሆኑና በይበልጥ የተቆራኘ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደሆኑ በማመላከት፣ ይኼንን የሚተካ አማራጭ ማምጣት ለተቀናቃኞች ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ግንኙነት ምክንያት አፍሪካ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቻይና ዜጎች መናኸሪያ እየሆነች ነው በማለት፣ በአፍሪካ የሚወለዱ ሁለተኛ ትውልድ ዜጎችም እየተፈጠሩ ነው ሲሉ ምልክታቸውን ያጋራሉ፡፡ ይኼም እየሰፋ ሲሄድና ሲጠናከር በቻይናና በኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች መካከል ፖለቲካዊ ትስስር የሚመጣበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ያሳያል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት በሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግን ወደ ምዕራቡ ያደላ ትስስር ለመፍጠር ያላቸው ፍላጎት ምልክቶች መታየታቸውንና ከቻይና ለመራቅ ፍላጎቶች እንዳላቸው በማመላከት፣ ቻይና ግን የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ላይ ባደረገችው ድርድርና ለኢትዮጵያ ባራዘመችላት የ30 ዓመታት የመክፈያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት አሳይታለች የሚሉ አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአማራና በኦሮሞ ባለሀብቶች በተዘጋጀ የሰላምና የፍቅር ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከዓለም ባንክና ከዓለም ገንዘብ ድርጅት መበደር ከራስ እናት የመበደር ያህል ነው በማለት አነስተኛ የብድር ምጣኔና ረዥም የመክፈያ ጊዜ ያላቸው ብድሮች መሆናቸውን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ሌሎች አበዳሪዎች ለባቡር ግንባታ አበድረው ባቡሩ ተገንብቶ ሥራ ሳይጀምር ክፈሉ ይላሉ ሲሉም ወርፈዋል፡፡

ቻይናም እየተለወጠ ባለው የዓለም የኃይል አሠላለፍ ባላት ግንዛቤ መሠረት ኢኮኖሚያዊ ጡንቻዋን በማፈርጠም፣ በዚያ ሳቢያ ማግኘት የምትችለውን በማግኘትና መስጠት የምትችለውን ለመስጠት ዝግጁ ናት ሲሉ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖና ተደማጭነት በዘለለ የወታደራዊ ተፅዕኖ ፍላጎት ስላላትም፣ በጂቡቲ የመጀመርያ የሆነውን የወታደራዊ ጦር ሠፈር መሥርታለች፡፡

ከዚህ አለፍ ሲልም እየዘመኑና እየተወሳሰቡ ባሉት የወታደራዊና የደኅንነት ቴክኖሎጂዎች በምድርም፣ በአየርም፣ በህዋም ጠንካራ ተፎካካሪ ዘርፍ እየገነባች ስለምትገኝ በብዛት ከምዕራቡ ዘርፍ ጋር የተቆራኘው የወታደራዊና የደኅንነት ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት፣ ወደ ቻይና ማማተርን የግድ ሊል ይችላልም የሚሉ አልታጡም፡፡

ያም ሆነ ይህ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቦይንግ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ አማካይነት ያላት ቁርኝት በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ፣ አሜሪካና ኢትዮጵያ ታሪካዊም ኢኮኖሚያዊም ግንኙነታቸው በቀላሉ የሚተካ አይደለም ይላሉ፡፡

ነገር ግን በዲፕሎማሲው ዓለም በተለመደው አገላለጽ ‹ዘላቂ ጠላትም ሆነ ዘላቂ ወዳጅ› ባለመኖሩ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ አገሮች፣ ከቻይናና ከአሜሪካ መምረጥ የሚኖርባቸው ጊዜ ይመጣ ይሆን ሲሉ የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡

ይኼንን ጥያቄ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ‹‹ለምን መምረጥ ያሻል?›› ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳሉ፡፡

‹‹ኬንያ በዓለም ታላላቅ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆኑ አገሮች የውክልና ጦርነት ውስጥ መግባት አትፈልግም፤›› በማለት፣ ‹‹ኬንያ በርካታ ምርጥ ወዳጆች ሊኖሯት ይችላሉ፤›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡

ስለዚህም መምረጥ የግዴታ ተደርጎ ግፊት መቅረብ እንደሌለበትና ከሁሉም ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለባቸው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኬንያታ፣ ለሁሉም የሚሆን ዕድል አለ ብለን እናምናለን ብለዋል፡፡

ይሁንና አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ቻይናን ለመቀናቀንና ለመገዳደር ዓላማ ከማድረግ ይልቅ አማራጭ በመሆንና የተሻለ ዕድል በመፍጠር ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ተመልካቾች ይናገራሉ፡፡ ይኼ ካልሆነ ግን በንግድም ሆነ በሌላ ሰበብ አፍሪካን የሁለቱ አገሮች የጦርነት ዓውድማ ከማድረግ የዘለለ ሚና መጫወት አይቻልም ይላሉ፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -