Wednesday, June 7, 2023

መጪው ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ከ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ሥልጣን የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በቀን አንዴ እንኳን መመገብ የማይችለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀን ሦስቴ መብላት እንዲችል ማድረግ አንዱ ዓላማው እንደሆነ፣ ሌላው ዓላማ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፋት እንደነበር በተደጋጋሚ ሲናገር የተደመጠ ጉዳይ ነበር፡፡

የመጀመርያውን ዓላማ በተመለከቱ ኢሕአዴግ ረዥም ርቀት እንደተጓዘ በርካቶች የሚስማሙበት ቢሆንም፣ ያንኑ ያህል ደግሞ ነቀፌታ የሚሰነዝሩም አሉ፡፡ ሆኖም በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገትና የመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ በዚህ ዓላማ ዙሪያ ቢያንስ ቁርጠኝነት የተያበት ጥረት ተደርጓል የሚለው አገላለጽ በርካቶችን ያስማማል፡፡ በዚህም ሳቢያ ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አገሮች ተርታ ተሠልፋ ስሟ በተደጋጋሚ ሲጠራ ተደምጧል፡፡ ምንም እንኳ ዕድገቱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም፣

ሁለተኛውን ግብ በሚመለከት ግን እንደ 28 ዓመታት ቆይታው ተነፃፃሪ የሚሆን ስኬት ተመዝግቧል የሚለው ሐሳብ ላይ የኢኮኖሚውን ያህል ስምምነት ማግኘት ከባድ ይሆናል፡፡ በአገሪቱ የተፈጠረው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትም ሆነ ለአምስት ተከታታይ ጊዜያት የተካሄዱ ምርጫዎች በዚህ ረገድ እምብዛም ወደፊት ያላራመዱ ናቸው ሲሉ የሚከሱም አሉ፡፡ ስለዚህም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፋይዳ ቢስ ከማድረግና ከአገር እንዲሸሹ ግፊት ከመፍጠር፣ እንዲሁም ለእስር ከመዳረግ ባሻገር በሰውና በንብረት አቅመ ጠንካራ የሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ ተደርጓል ሲሉ የፓርቲዎች ተወካዮች በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ከርመዋል፡፡ ከአሁን ቀደም የተደረጉ አምስት አገራዊ ምርጫዎች ቢኖሩም፣ ከኢሕአዴግ ውጪ ያለ አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ ለሥልጣን ቅርብ ሊሆን ያልቻለባቸው ምርጫዎች ነበሩ፡፡ እየተሻሻለ ሊመጣ ይገባ በነበረበት በመጨረሻው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ኢሕአዴግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን መቶ በመቶ ተቆጣጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ መዘዝ አስከትሏል፡፡

በእነዚህ የምርጫ ዘመኖች በብዛት ኢሕአዴግ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ የሚያቀርበው መከራከሪያ አማራጭ የፖሊሲ አጀንዳዎች የሏቸውም የሚል ሲሆን፣ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥምረትም ሆነ በተናጠል ፖሊሲዎችን በማበጀትና የኢሕአዴግን ፖሊሲዎችና ትግበራዎች በግልጽ በመተቸት ለምርጫ ፉክክር ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡

ከእነዚህ አገራዊ ምርጫዎች በተለየ መንገድ የበርካቶችን ቀልብ የሳበውና ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ዕርምጃ ራሱን የቻለ አሻራ ያኖራል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቀው የ2012 አገራዊ ምርጫ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 የድምፅ መስጫ ቀን እንደሚሆንና የምርጫው የመጨረሻ የተጣራ ውጤት እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ማብቂያ ገደማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ያመጣው የለውጥ ተቃውሞ ተከትሎ የተደረጉ የሕግና የተቋም ማሻሻያዎች አንዱ ትኩረት የነበረው፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊና የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረጉንና ለቀጣይ ምርጫ ስኬት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ቢገልጽም፣ በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ቀውስ ከምንጩ ተጠንቶ መፍትሔ ሳይቀመጥና ፅንፍ የረገጡ የፖለቲካ ሐሳቦች ሳይታረቁ የሚደረግ ምርጫ ውጤቱ ያማረ አይሆንም ሲሉ፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ምርጫው ካልተደረገ አሁን ያለው መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ስለሚያጣ፣ ምርጫው በጊዜ መደረግ አለበት ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በእነዚህ ክርክሮች መካከል በሚሰጡ መግለጫዎችና በሚደረጉ ንግግሮች አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግን ያከሰመው ብልፅግና ፓርቲ፣ ምርጫውን ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ ሲል በተደጋጋሚ ተደምጧል፡፡

በተለይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማድረግ መወሰኑን ከተረዱ በኋላ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ያስታወቁ ሲሆን፣ ተፎካካሪ ያደርገናል ብለው ያሰቧቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ለምርጫ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ሲያስታውቁ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ በዘለለም ከተለያዩ መሰሎቻቸው ጋር በመጣመር ለምርጫ ፉክክር በአንድ ዓርማ ለመወዳደር ሲዘጋጁም ተስተውለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ዝግጅት እያደረጉ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ሲሆን፣ 16 ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ይናገራሉ፡፡ ኢዜማ ከፖለቲከ ፕሮግራሙ በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ የግብርና፣ የምግብ፣ የገንዘብና የበጀት፣ የኢንቨስትመንት፣ የፋይናንስና ባንክ፣ የባህል፣ የቱሪዝምና የተቀናጀ ከባቢ፣ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የማኅበራዊ ዋስትና፣ የሥራ፣ የጤና፣ የትምህርትና ሥልጠና፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና ፈጠራ፣ የከተማና የተቀናጀ የገጠር ልማት፣ የኢነርጂ፣ የውኃና አካባቢ፣ እንዲሁም የዳያስፖራ ፖሊሲዎችን እንዳዘጋጀ የተናገሩት አቶ ናትናኤል፣ ዝርዝሮች ግን ገና ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊሰት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ በድረ ገጹ ላይ የሰብዓዊ መብት፣ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የደኅንነት እንዲሁም የአንድነት ፖሊሲዎችን አስፍሯል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በተመሳሳይ የመንግሥት አደረጃጀትን፣ የኢኮኖሚ ልማትን፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ፣ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ዘርፎች፣ እንዲሁም በምርጫ ሥርዓት ዙሪያ ያሉትን የፖሊሲ አማራጮች በፕሮግራሙ ላይ አስፍሯል፡፡

እንዲህ ዓይነት የፖሊሲና የፕሮግራም አማራጮችን ይዞ ለምርጫ መገኘት አንዱ የተፎካካሪነት ዕድልን፣ ግፋ ሲልም አሸናፊነትን ይዞ እንደሚመጣ በርካቶች በሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች የሚገልጹ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት በሚያደርጓቸው ንግግሮች ተፎካካሪዎች ሥልጣንን በፖሊሲ አማራጭ ተደግፈው ብቻ ማግኘት እንደሚችሉ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

ይሁንና የፖለቲካ ሥርዓቱና የደጋፊዎች ማሰባሰብ ሥራዎች የብሔር ማንነት ላይ የተመረኮዙ ሆኖ ሳለ፣ የፖሊሲ አማራጮችን አወዳድሮ ለማስመረጥ ይቻላል ወይ ሲሉ የሚጠይቁ አሉ፡፡

ይኼንን ጥያቄ አስመልክቶ ከእንግሊዝኛ ድረ ገጽ መጽሔት ጋር ከወራት በፊት ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ ለመራጮቻችሁ ምን የፖሊሲ አማራጮችን ይዛችሁ ነው ለምርጫው የምትዘጋጁት ሲባሉ፣ ‹‹እኛ እስከሚገባን ድረስ የፖሊሲ ጉዳዮች ለኦሮሞ ሕዝብ ሁለተኛ ናቸው፡፡ ከሕዝባችን ጋር ስንወያይ ነው የቆየነው፡፡ ለሕዝባችን ቀዳሚውና እጅግ ጠቃሚው ጉዳይ ቢኖር የራሳቸውን ተወካዮች መምረጥ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና እውነተኛ በሆነ ምርጫ በተወካዮቻቸው በኩል በእጃቸው ማስገባት ነው፡፡ ሕዝባችንንም ለዚሁ ነው የምናዘጋጃቸው፤›› ብለው ነበር፡፡

በተመሳሳይ የተለያዩ የብሔር ማንነት ላይ ተመርኩዘው የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር በሚያደርጓቸው ውይይቶች ሲናገሩ እንደሚደመጡት የፖሊሲ አማራጭና ሐሳቦችን ሲያስቀምጡ ሳይሆን፣ በተቋቋሙበት የብሔር ዘውግ ያለ ሰው ብቻ ሊያስተዳድራቸው ስለሚገባ በዚያው አረዳድ ምርጫ እንዲመርጡ ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም የፖሊቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮችን ይዘው በብዛት በብሔር ማንነት ላይ ተመርኩዘው ለተመሠረተ ፖለቲካዊ ሥርዓት መዘጋጀታቸው፣ እምብዛም አያዋጣም ሲሉ ሐሳብ የሚሰጡ አሉ፡፡ ቀጣዩ ምርጫም በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረቱ ፓርቲዎች የበላይነትን ሊይዙ እንደሚችሉት በመጠቆም የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች በማንነት ላይ የተመሠረቱ ጥቃቶችና እንዲሁም የደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎች የምርጫውን አዝማሚያ የሚያመላክቱ ናቸው ይላሉ፡፡ ስለዚህም በዚሁ ስሜት የፖሊሲ አማራጮች ፋይዳ ምንድነው በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ሆኖም ግራም ነፈሰ ቀኝ በብሔር ቀረቤታቸው ድምፅ የሚያገኙና የሚመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ የሆኑ የሕዝቡን ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉት፣ ግልጽና ቀጥተኛነት ያላቸው ፖሊሲዎች በመቅረፅ ስለሚሆን ወደዘያው መምራታቸው አይቀርም ብለው የሚከራከሩ ታዛቢዎች፣ ይኼንን ማድረግ ካቃታቸው ግን ሥልጣን ላይ የመቆየት ዕድላቸው አናሳ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በሌላ ወገን ያሉ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ የብሔር ፓርቲዎች በራሳቸው እርስ በርስ የሚፎካከሩባቸው ፖሊሲዎችን ማቅረብ እንዳለባቸውና በዚያ ላይ የተመሠረተ ድምፅ ማግኘት እንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ፡፡ ምርጫ የተለያዩ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ተመዝነው ለሥልጣን የሚመረጡበት ሥርዓት ነው በማለት፡፡

ከዚህ አለፍ ሲልም የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር የተደራጁም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁም ቢሆኑ፣ የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቅሙ ስለሚሆኑ፣ ለአነስተኛ ቡድን ብቻ ተብሎ የሚሠራ ፖሊሲ የለም የሚሉ አሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -