ለአየር መንገድና ለባቡር ኮርፖሬሽን የ400 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፍሏል
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2012 ዓ.ም. የመጀመርያው መንፈቅ በኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻለበትን ውጤት በማስመዝገቡ ከታክስ በፊት ከ428 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ፡፡ በግማሽ ዓመቱ የዓረቦን ገበያውን በ52 በመቶ ማሳደግ እንደቻለ ድርጅቱ ገልጿል፡፡
በኢንዱስትሪው ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ በመያዝ ለዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ዘንድሮም ሰፊ የገበያ ድርሻ በመያዝ ዘልቋል፡፡ ከጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የገበያ ድርሻው ቅናሽ እየታየበት ቢመጣም፣ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት አፈጻጸሙ ግን ከዚህ ቀደም የነበረውን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ለማስፋፋት እንደቻለ አስታውቋል፡፡
መድን ድርጅት የግማሽ ዓመት አፈጻጸሙን በማስመልከት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ማሰባሰብ የቻለው የዓረቦን መጠን 3.75 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት አኳያ የ1.3 ቢሊዮን ብር ወይም 52.5 በመቶ ብልጫ ያሳየበት በመሆኑ፣ በመድን ኢንዱስትሪው ውስጥ የነበረውን የገበያ ድርሻ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ከፍ እንዳደረገው ያሳያል፡፡ በግማሽ ዓመቱ መድን ድርጅትን ጨምሮ 17ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካሰባሰቡትና ሰባት ቢሊዮን ብር ገደማ ከሆነው የዓረቦን ገቢ ውስጥ ከግማሽ በላዩን የመድን ድርጅት መውሰዱ ለገበያ ድርሻው ከፍ ማለት አመላካች ነው ተብሏል፡፡
በ2012 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን፣ ከጠቅላላው የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ 53 በመቶውን የገበያ ድርሻ እንዲይዝ አስችሎታል፡፡ ከአምናው በተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም በ18.3 በመቶ ጭማሪ የታየበት የገበያ ድርሻ እንዳስመዘገበ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በመሆኑም 16ቱ የግል የመድን ኩባንያዎች በጋራ የያዙትን ከግማሽ በላይ የገበያ ድርሻ በዚህ ግማሽ ዓመት የለወጠ አኃዝ ያደርገዋል፡፡ በአምናው ግማሽ ዓመት ወቅት 16ቱ የግል የመድን ኩባንያዎች 55.3 በመቶ የገበያ ድርሻ አስመዝገበው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት መንፈቅ ላይ ያስመዘገቡት የገበያ ድርሻ ግን ወደ 47.1 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት 16ቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያስመዘገቡት የገበያ ድርሻ እስከ 62 በመቶ አሻቅቦ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የነበረው የገበያ ድርሻ እስከ 38 በመቶ ዝቅ ያለባቸው ዓመታት እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የድርጀቱ አፈጻጸም ከፍተኛ ዕድገት እንደታየበት መረጃዎች ቢያመላክቱም፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን ግን በድርጅቱ ታሪክ በከፍተኛነቱ ተመዝግቧል፡፡ 990 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ አውሏል፡፡ ይህ የካሳ ክፍያ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተከፈለው ካሳ አንፃር በ94.4 በመቶ ወይም በ480.6 ሚሊዮን ብር ብልጫ ይዟል፡፡
በግማሽ ዓመቱ የተፈጸመው የካሳ ክፍያ ይህን ያህል ለመጨመሩ አንዱ ምክንያት፣ ከአውሮፕላን ግጭት ጋር ተያይዞ ለተለያዩ የመለዋወጫ ዕቃዎች ግዥና ለመሰል የመድን ሽፋኖች እንዲውል ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈሉ ነው፡፡ በቅርቡም ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተከፈለው 100 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካሳም የስድስት ወራት ወጪውን አንሮበታል፡፡
ይህም ሆኖ ኩባያው በግማሽ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠንና በሌሎች አፈጻጸሞቹ ያገኘው ትርፍ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ካስመዘገበው የበለጠ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ የድርጅቱ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከታክስ በፊት 247.99 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህም በ2011 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከተመዘገበው አኳያ ሲነፃፀር የ8.5 በመቶ ብልጫ አሳቷል፡፡
በየዓመቱ የመድን ሽፋን የሚሰጥባቸው ዘርፎች እያደጉ መምጣታቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የመድን ሽፋኑና የተሸከመው የሥጋት መጠን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሱ ይገልጻል፡፡ በ2011 በግማሽ ዓመት ከነበረው ከ284.9 ቢሊዮን ብር አኳያ የዘንድሮው ብልጫ አለው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ሽፋን ድርጅት ከ44 ዓመታት በላይ በኢንዱስትሪው የዘለቀ መንግሥታዊ መድን ሰጪ ድርጅት ነው፡፡