Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክፍትሕ በዓባይ ውኃ

ፍትሕ በዓባይ ውኃ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የህዳሴው ግድብ የውኃ አሞላል ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ከግብፅና ሱዳንም አልፎ በዓለም ባንክና በአሜሪካ ታዛቢነት ድርድር ሲደረግ ሰንብቷል፡፡ ለፊርማ የሚበቃው ሰነድ ከቴክኒክና ከሕግ አንፃር ታይቶ ለማዘጋጀት ጊዜ ተቆርጧል፡፡ ግብፅም ሆነች ሱዳን ለመስኖም ሆነ ለኃይል ማመንጫ ግድብ ሲሠሩ ከኢትዮጵያ ስምምነት አልጠየቁም፡፡ ኢትዮጵያም አልሰጠችም፡፡ ሁለቱ አገሮች ዓባይን በብቸኝነት ለመጠቀም በቅኝ ገዥዋ እንግሊዝም አማካይነትም ኋላም ከነፃነት ማግሥት በራሳቸው

ውል ሲያደርጉ ኢትዮጵያንም ሆነ፣ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ከውኃው እንደሚጋሩ አገሮች ሳይቆጥሯቸው ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዓባይ ውኃ መገልገልን በሚመለከት ተፈጻሚ የሚሆኑ ሕግና ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎችን ጨምሮ እንደ ህዳሴው ግድብ ዓይነት ፕሮጀክቶች በሚሠሩበት ጊዜ እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች ሊኖራቸው የሚችለውን ሕጋዊ አንድምታ መጠቆም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

መንደርደሪያ

ወንዝ በአንድ አገር ዜግነት ላይፀና ይችላል፡፡ ሁለትም ሦስትም አሊያም እንደ ዓባይ (ናይል) አሥራ አንድ አገርን በማካለል የአሥራ አንድ አገር ዜግነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ዓባይ አሥራ አንድ አገሮችን ስለሚያካልል ሁሉንም ያገናኛል፣ ከሁሉም ጋር ይገናኛል፡፡ ዝምድናው ከአንዱ አገር ጋር ብቻ ባለመሆኑ ሕጋዊ ግንኙነቱም እንዲሁ የበዛ ነው፡፡ ዜግነት የግለሰብ ከአንድ አገር ጋር የሚኖረው ሕጋዊ ግንኙነት አይደል!

ዓባይ ከስምንት አገሮች መንጭቶም፣ ጎልብቶም፣ ሁለቱ ሱዳኖችን በመጠኑ አረስርሶ በረሃዋን ግብፅን አገር እንድትሆን ቀን ከሌሊት በትጋት አገልጋይነቱን በታማኝነት እየተወጣ ነው፡፡ ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ማለትም ከታንዛኒያ፣ ከኬንያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከሩዋንዳ፣ ከቡሩንዲ፣ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የሚፈልቀው ውኃ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች የሆኑትን ደቡብ ሱዳንን፣ ሱዳንንና ግብፅን ሐሩራማ፣ ረግረጋማቸውን ጨምሮ የማይጠረቃ ግድባቸውንም ዕፀዋትና እንስሳት መሬትና ሰዎቻቸውንም ሲሳይ ሆኗል፡፡ ከስምንቱ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ብቻዋን የውኃውን 86 ከመቶ ታዋጣለች፡፡

ይህን ያህል ውኃ የምታዋጣው ኢትዮጵያ ግን ከበይ ተመልካችነት ያለፈ ድርሻ አላት ለማለት የሚያስችል ግልጋሎት እያገኘች አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ በድህነትና በርሃብ እየተቆራመደ፣ በአንፃራዊነት የግብፅ ገበሬ በዓባይ ውኃ በልፅጓል፡፡ የዓባይን ልጅ ውኃ እየጠማው፣ ግብፆች ያለምሥጋናም ያላዘኔታም ከዓባይ ይጠጣሉ፡፡ በዓባይ ውኃ አርሰው ይመገባሉ፡፡ በዓባይ ውኃ ኤሌክትሪክ ያመነጫሉ፡፡ ለፋብሪካዎቻቸው ኃይል ያቀብላሉ፡፡

የዓባይ ውኃ የዓመት መጠኑ 54 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሳይሆን 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው በሚል በአስዋን ግድብ የሚተነውን አሥር ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር ውኃ ቀንሰው 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቡን ብቻ ተካፈሉ፡፡ በዚህም ሱዳን በ1929ኙ ስምምነት 4.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የነበረው ድርሻዋ ወደ 14.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ፣ የግብፅ ደግሞ ከ49.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ወደ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለመካፈል ተስማሙ፡፡ የውኃውም ብቸኛ ባለቤት ሁለቱ ብቻ እንደሆኑ አወጁ፡፡ በተለይ እነዚህ ሁለት ስምምነቶች የተፋሰሱን አገሮች ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ አደረገው፡፡

ኀልዮቶቹ

በዓባይ ውኃ ፍትሕ እንዲሰፍን የውኃን አጠቃቀም በሚመለከት ሕግጋትና ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ እንዳለመታደል ግን ሁለቱም በተሟላ ሁኔታ የሉም፡፡ በሁለቱም መጥፋት ፍትሕም እንዲሁ የለችም፡፡ ዓባይ የአንድ አገር ወንዝ ስላልሆነ በብሔራዊ ሕግ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ አልበለዚያም የወንዙ ተጋሪ አገሮች በሚያወጡት ሕግ ነው ሊተዳደር የሚችለው፡፡

ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በሚመለከት አስገዳጅና አሳሪ የሆነ ዓለም አቀፍ ሕግ አለ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ ለሕግ መሠረት የሚሆኑ ሁለት ተፃራሪና አንድ መካከለኛ መንገድ የመረጠ፣ በጥቅሉ ሦስት ኀልዮቶች አሉ፡፡ አንዱ ‹‹ፍፁም የግዛት ሉዓላዊነት›› (Absolute territorial sovereignty) ኀልዮት የሚባለው በተለይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች (ማለትም ውኃው በብዛት የሚመነጭበት) በግዛታቸው ውስጥ ያለን ንብረት እንዳሻቸው የመጠቀም ሥልጣን እንዳላቸው የሚቀነቀንበት ነው፡፡

የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የሚመርጡት ይህንን ኀልዮት ነው፡፡ ለዓባይ ወንዝ 86 ከመቶ የምታዋጣው ኢትዮጵያም ይህን ያህል መጠን ውኃ ከግዛቷ ስለሚወጣ እንደ አንድ ባለንብረት ያሻትን የማድረግ መብትና ሥልጣን ይኖራታል ብሎ እንደመሞገት ነው፡፡  ሁለተኛው ኀልዮት፣ ‹‹ፍፁም የግዛት አንድነት›› (absolute territorial integrity) የሚባለው ሲሆን፣ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ለቆጠራው መነሻ ጊዜ ከሌለው ዓመት ጀምሮ የአገሪቱ አካል የሆነው ወንዝና ውኃ የአገሮች አንድ አካል እንደሆነ የሚያትት ነው፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃውን ፍሰት ካደናቀፉት የግዛት አንድነቱ እንደተጣሰ  ይቆጥሩታል፡፡

ሱዳንና ግብፅም ዓባይ (በእነሱ አጠራር ናይል) የግዛታቸው አካል ስለሆነ በዓባይ ወንዝ አዛዥና አዛዥ እኛ ነን የሚሉትን አቋም የሚደግፍ ኀልዮት ነው፡፡ ታሪካዊ መብትም (Historical right) የሚለው የዚሁ ቅጥያ ሐሳብ ነው፡፡ ሦስተኛው፣ ‹‹ገደብ ያለው ሉዓላዊነት›› (Limited territorial sovereignty) የሚባለው ነው፡፡ በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አጠቃቀም ውኃው የሚነሳት አገር ፍፁም ሉዓላዊነት በሚል፣ ውኃውን ሲጠቀሙ የኖሩ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችም ፍፁም የግዛት አንድነት በሚል ላይ ሳይቸነከሩ ሁለቱንም ወደ መሀል በማምጣት፣ ሁሉንም ተጠቃሚና ተገልጋይ መሆን እንዳለባቸው የሚሰብክ ኀልዮት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ኀልዮት ‹‹ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት›› (Equitable and reasonable utilization) እየተባለ እየተጠራ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የራሱ የሆኑ መለያዎች አሉት፡፡ በሉዓላዊነት ስም ሌላ ወሰንተኛና ወንዙ የሚያካልለውን አገር ከሚጎዳ አድራጎት መቆጠብ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም የመልካም ጎረቤትነት መርህን ማክበር እንደሚያስፈልግ ይህ ኀልዮት ያሳስባል፡፡ በተለይ ደግሞ በወንዙ ተጋሪ አገሮች ላይ ‹‹ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ›› (No significant harm principle) አሠራርና መርህም ቢሆን፣ የዚሁ ገደብ ያለው ሉዓላዊነት መርህ ክትያ ነው፡፡

በመሆኑም ይህ ኀልዮት በአንድ በኩል በዚህ ወቅት በመተግበር ላይ ያሉ የዓለም አቀፍ ወንዞች የውኃ ግልጋሎት አጠቃቀምን የያዘ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሥሩ የተለያዩ ንዑስ መርሆችን ያቀፈ መሆኑ ነው፡፡ የመጀመርያዎቹ ሁለቱ ኀልዮቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነታቸው እየኮሰመ በመሄድ ላይ ሲሆን የሦስተኛው ደግሞ እየጨመረ ነው፡፡

የሁለት መርሆች ፍጥጫ

በድንበር ዘለል ወንዝ ውኃ አጠቃቀም አሁን ላይ ሁለት ተገዳዳሪ መርሆች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ከላይ የተገለጸው ገደብ ያለው ሉዓላዊነት መርህ አካል መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ዓብይ ጉዳት ያለማድረስና ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት የሚባሉት ናቸው፡፡ ዓብይ ጉዳት አለማድረስ የሚለው ቀድሞ በጥቅል አጠራር ‹‹ጉዳት አልባ መርህ›› (No harm principle) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡

እየተሻሻለ ሄዶ ምንም ጉዳት አለማድረስ የሚለው ቀርቶ ጉዳት ቢኖርም እንኳን የጉዳቱ መጠን ጉልህ ወይም ዓብይ ሊባል የሚችል መሆን እንደሌለበት ነው የመርሁ ማዕከላዊ ማጠንጠኛ፡፡ ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ መርህ ምንነቱንም ሆነ መለኪያውን ቁርጥ አድርጎ ማስቀመጥ አዳጋች ነው፡፡

እንደየጉዳዩ እየታየ ሊወሰን የሚችል ዓይነት ነው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች የሚመርጡት መርህ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ውኃውን የፍሰት መጠን የሚቀንስ፣ ቀደም ሲል የተሠሩ መስኖ፣ የኃይል ማንጫ፣ ለፋብሪካና ለመጠጥ የሚውለውን የውኃ መጠን መቀነስን ሊያመለክት ይችላል፡፡

 በተጨማሪም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ተግባር በታችኞቹ ላይ ብክለትና የሥነ ምኅዳር መዛባትን የሚያስከትልም በሚሆንበት ጊዜ ይህንኑ የዓብይ ጉዳት ያለማድረስ መርህ በማንሳት ይከራከራሉ፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የሚያደርጓቸው የመስኖም ይሁን ሌላ ግልጋሎት የጉዳቱ መጠን ከፍና ዝቅ ማለቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ጉዳት ማድረሳቸው የሚቀር አይደለም፡፡ ግን ዓብይ ጉዳት የሚለው ላይሆን ይችላል፡፡

በበርካታ ድርሳናት ውስጥ የሚቀርበው፣ ታችኞቹ ተጎጂ፣ ላይኞቹ ጎጂ ሆነው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው የሚሆንበትም ጊዜ እንዳለ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የታችኞቹ አገሮች በታሪክ አጋጣሚ ቀድመው የመስኖና ሌላም ግልጋሎት ከጀመሩ፣ የላይኞቹ አገሮች በወንዙ የመገልገግ መብታቸውን እየተጋፋና እያጣበበ ስለሚሄድ ይህ መርህ ለላይኞቹም ይሠራል፡፡ ግብፅ አስቀድማ የአስዋንና የናስር ግድብን መሥራቷ፣ ሌሎች የመስኖ ፕሮጀክቶችን ዕውን ማድረጓ፣ ኢትዮጵያ የምትሠራቸው የመስኖም ይሁን የኃይል ማመንጫ ግድቦች ግብፅ ላይ ዓብይ ጉዳት ስለሚያደርሱ እየተባለ መከራከሪያ ናቸው፡፡

የጉዳት መጠኑን ለመለካት ግብፅ ከኢትዮጵያ ቀድማ የገነባቻቸው ፕሮጀክቶች መለኪያ ስለሚሆኑ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ቀድመው የሚሠሯቸው ለላይኛው ተፋሰስ አገሮች እንቅፋት በመሆን ጉዳት ማድረሳቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድብ የውኃ አሞላልም ይሁን ሌላ እንቅስቃሴ ላይ ድርድር እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ ግብፅና ሱዳን በዓባይ ውኃ ላይ በሚያከናውኗቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን፣ ቀድመው በተጠናቀቁትም ላይ ጭምር ድርድር ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ለአብነት ግብፅ የአስዋን ግድብን በሰሃራ በርሃ ውስጥ በመገንባቷ በዓመት ከአሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያላሰነ በትነት ብቻ ይባክናል፡፡ የሚተነው የውኃ መጠን ከተከዜ እስከ አትባራ የሚፈሰውን ውኃ መጠን ያህላል፡፡ ሰሃራ ውስጥ ግድብ ገንብቶ በትነት ብቻ የሚጠፋውን ውኃ ማስቀረትና ጥቅም ላይ በማዋል የተፋሰስ አገሮችን የውኃ ድርሻ ከፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

እዚህ ላይ ማንሳት የተፈለገው የታችኛው ተፋሰሶች ቀድመው የሚሠሩት የላይኞቹን ተፋሰሶች በውኃው መገልገል ሊጀምሩ ሲሉ እንቅፋት እየሆነ ጉዳት ሊያደርስ የመቻሉን ጉዳይና ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ መርህም ለእነሱም የሚሠራ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡  

ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት ከላይ ካየነው መርህ ጋር እየተዛመደም፣ እየተቃረነም፣ ይቀርባል፡፡ በበርካታ የአማርኛ ‹‹ፍትሐዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት›› በሚል ይጠቀሳል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጽሑፍ “ፍትሐዊ” ሳይሆን “ርትዓዊ” የሚለውን ቃል መጠቀምን ተመርጧል፡፡ ርትዕ፣ ፍትሕን ለማስፈን የሚያገለግል፣ ቀድሞ በሕግ በግልጽ የታወቀና የተቆረጠ ደንብ ማስቀመጥ በሚያስቸግርበት ጊዜ እንደሁኔታው ትክክልና ተገቢ የሚባሉ ነጥቦችንና ተለዋዋጮችን ከግምት በማስገባት ፍትሕ መስጠትን ስለሚያመለክት ነው፡፡ ፍትሕ ለሚያሰፍኑ አካላትም ሰፋ ያለ ሥልጣን ይሰጣል፡፡

ይህ የርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት መርህ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ በመምጣት ላይ ነው፡፡ ወንዞቻቸውን በጋራ ለማስተዳደር ተቋማትን የፈጠሩ አገሮችም፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ደንቦችም ለዚሁ መርህ ቅድምና ሰጥተውታል፡፡ በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ. በ1966 በዓለም አቀፉ የሕግ ማኅበር አማካይነት የወጣውና በስፋትና በአጭር አጠራር ‹‹የሔልሲንኪ ደንብ›› በሙሉ ስሙ ‹‹ስለዓለም አቀፍ ወንዞች አጠቃቀም የሔልሲንኪ ደንብ›› (The Helsinki rules on the uses of waters of international rivers) በመባል የሚታወቀው አንዱ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት አሳሳቢነት በዓለም አቀፉ የሕግ ኮሚሽን አማካይነት ለሰላሳ ዓመታት ገደማ ጊዜ ፈጅቶ እ.ኤ.አ. በ1997 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የፀደቀው ‹‹ከመጓጓዣ በስተቀር ዓለም አቀፍ የውኃ ተጋሪዎች ስምምነት››ም (The convention on the law of non-navigational uses of international watercourses) ይህንኑ መርህ ዋና ዓምድ አድርጎታል፡፡

የሔልሲንኪ ደንብ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ዓለም አቀፍ ወንዞች ውኃቸውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የሚያሳይ፣ ከፈለጉም እንዲጠቀሙበት አወንታዊ ተፅዕኖ በማድረግና ኋላም ላይ የ1997ቱ ስምምነት ላይ የተካተቱ ደንቦችን አበርክቷል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተረፈ አስገዳጅነትም የለውም፣ ልማዳዊ ሕግነት ደረጃም አልደረሰም፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎትን ከእነ አመልካቾቹ፣ የአንቀጹም ቁጥር ሳይቀየር ጭምር በስምምነቱ ተካትተዋል፡፡

የስምምነቱ አንቀጽ አምስት ስለዚሁ መርህ ሲገልጽ አገሮች ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰስን በግዛታቸው ውስጥ ሲጠቀሙ በርትዓዊና በሚዛናዊ ግልጋሎት መርህ  መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም ሲጠቀሙም፣ ሲያለሙትም ሆነ ጥበቃ ሲያደርጉ በእዚህ መርህ መሠረት መሆን እንዳለበት ያሳስባል፡፡ ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት መኖሩን ለማመልከት የሚረዱ ተለዋዋጭ ነጥቦችን በምሳሌነት መልኩ በስምምነቱ አንቀጽ ስድስት ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም፣

 መልክአ ምድር፣ ሃይድሮግራፊ፣ የውኃው መጠን (ሃይድሮሎጂ)፣ የአየር ፀባይና የአካባቢው ሌሎች ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች፣ በወንዙ ተፋሰስ አገሮች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፍላጎቶች ያሉበት ሁኔታ፣ የወንዙን ሀብት በመጠቀም የሚተዳደረው የሕዝብ ብዛት፣ በአንዱ አገር የሚከናወነው በሌላው አገር ላይ የሚያስከትለው ውጤትና ተፅዕኖ መጠን፣ በወቅቱም ሆነ ለወደፊት ሊፈጸሙ የታቀዱ ግልጋሎቶችና ፕሮጀክቶች፣ የወንዙን ውኃ ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስከትለው ወጭና ወንዙ የሚሰጠውን ግልጋሎት በሌላ አማራጭ ሊተካ የሚችል መሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡

አንድን የወንዝ ግልጋሎት የሚጋሩ አገሮች ርትዓዊና ሚዛናዊ በሆነ አሠራር ለመጠቀም ሲሉ ከግምት ሊያስገቧቸው የሚችሉ አመላካቾችን፣ በነቂስ ሳይሆን በናሙናነት፣ ስምምነቱ አመላክቷል፡፡ ሌሎች ተለዋዋጮችን ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡

ይኼው ስምምነት በአንቀጽ ሰባት ሥር፣ ከርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት መርህ በክትያነት በሚመስል አቀማመጥ ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ መርህን አካትቷል፡፡ አገሮች በግዛታቸው ውስጥ የጋራ ተፋሰስ የሆነን ሀብት በሚጠቀሙበት ጊዜ በሌላኛው ላይ ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ፣ መድረሱ የማይቀር ከሆነ ደግሞ ጉዳት ከሚደርስበት አገር ጋር በመመካከር የሚቀነስበትንና የሚቀረፍበትን ይህ ካልተሳካና ሁኔታው አመቺ ከሆነም ለጉዳቱ ካሳ የሚከፈልበትን አሠራር እንዲዘይዱ የሚያሳስብ አንቀጽ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ሆነች ግብፅ የዚህ ስምምነት ፈራሚ አይደሉም፡፡ ለግብፅ ርትዓዊና ሚዛናዊ የሚለው መርህ ቅድምና ሊሰጠው አይገባም፣ ዓብይ ጉዳት ያለማድረስ የሚለው ተቀዳሚ ወይም እኩል ደረጃ ሊኖረው ይገባል ባይ ናት፡፡ የኢትዮጵያ አቋም ደግሞ የግብፅን በተገላቢጦሹ ነው፡፡

ከዚህ በላይ የቀረቡት በዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰስ ግልጋሎት መሠረት የሆኑ መርሆችን ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ እንደ ዓባይ ድንበር ዘለል የሆኑ ወንዞችን በጋራ፣ በትብብር፣ ርትዓዊና ሚዛናዊ በሆነ አሠራር፣ አንዱ ሌላው ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሳያደርሱ የሚጠቀሙበትን የሕግና ተቋማዊ ማዕቀፍ በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ሲሆኑ፣ የላይኛውና የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ግን ኀልዮቶቹን እንደ አቋም የሙጥኝ ከማለት እምብዛም ፎቀቅ ሊሉ አልቻሉም፡፡

በተቋም ረገድ ሃይድሮሜት፣ ኡዱንጉ፣ ቴኮናይልና የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የሚባሉትን በማቋቋም ሙከራ ቢደረግም፣ ዓባይን በጋራ የሚያስተዳድር ተቋም ሊኖራቸው አልቻለም፡፡ የጋራ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችል የመተባበሪያ የስምምነት ማዕቀፍን (Cooperative framework agreement) ግብፅ ባለመፈረም አሻፈረኝ እንዳለች ናት፡፡

ዓባይ የአንድ አገር ወንዝ ባለመሆኑ ሁሉም በፍትሐዊነት ለመጠቀም መተሳሰብ፣ መተባበር፣ መተማመን፣ መተዛዘን ሲጠበቅባቸው በመተሳሰብ ፋንታ በመጨካከን፣ በመተባበር ምትክ በየፊና መጓዝ፣ ከመተማመን ይልቅ መጠራጠር፣ ከመተዛዘን መስገብገብን እንደመረጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፍትሐዊ አጠቃቀም መርህ ሆኗል፡፡ ለዓባይ ማስተዳደሪያ ሕግና ሥርዓት ማበጀት አልተቻለም፡፡ አስተዳዳሪ ተቋምም ማቆምም እንደገደዳቸው ነው፡፡

ይባስ ብሎ፣ ቅኝ ገዥ አገሮች በሱዳንና በግብፅ ስም፣ ዓባይን የሁለቱ አገሮች ሀብት ብቻ እንደሆነ አስመስለው እ.ኤ.አ. በ1929 በውል ለሁለት አካፈሏቸው፡፡ በዚህ ስምምነት የተበረታቱት ሱዳንና ግብፅ ከሰላሳ ዓመት በኋላ ሌላ ስምምነት አደረጉ፡፡ በእነዚህ ስምምነቶች ላይም የሙጥኝ እንዳሉ ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሪና አስገዳጅ ሕግ አለመኖር፣ የዓባይ ተጋሪ አገሮችም በጋራ ለመገልገል የሕግ ማዕቀፍ አለማውጣት፣ አስተዳዳሪ ተቋም አለማቆማቸው፣ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሕ እንደጎደለ ነው፡፡ ፍትሕ እንዳይሰፍን እንቅፋት የሆኑትን ሕግጋትንና የህዳሴው ግድብን በሚመለከት ድርድር ማድረጉ የሚኖሩትን ሕጋዊ አንድምታ በሚቀጥለው ክፍል ይቀርባል፡፡

አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...