Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከሕገ መንግሥቱ ጋር ስለሚጣረሱ ሊፀድቁ አይገባም ተብሎ ክርክር የቀረበባቸውን ሁለት አዋጆች ፓርላማው...

ከሕገ መንግሥቱ ጋር ስለሚጣረሱ ሊፀድቁ አይገባም ተብሎ ክርክር የቀረበባቸውን ሁለት አዋጆች ፓርላማው አፀደቀ

ቀን:

ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸው ሊፀድቁ አይገባም የሚል ክርክር የቀረበባቸውና ፓርላማውም የማፅደቅ ሥልጣን የለውም ተብሎ ጥያቄ የቀረበባቸው ሁለት ረቂቅ አዋጆችን፣ ፓርላማው በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።

 ከየካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር የመንፈቅ እረፍት ተበትኖ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለየካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ በተደረገለት ጥሪ ሁለቱን ረቂቅ አዋጆች ጨምሮ በጥቅሉ በቀረቡለት ስምንት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጣረሳሉ የሚል ክርክር የተነሳባቸው ረቂቅ አዋጆች የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበለት፣ እንዲሁም የኒውዮርክ ኮንቬንሽን ተብሎ የሚታወቀውን በውጭ አገሮች ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ዕውቅና የመስጠትና የመፈጸም ስምምነትን ለማፅደቅ የቀረበለት ረቂቅ የሕግ ሰነድ ናቸው።

- Advertisement -

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የተረቀቀው አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 6 እና ኢትዮጵያ አፅድቃ የሕገ መንግሥቷ አካል ካደረገችው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብት ኮንቬንሽን (ICCPR) አንቀጽ 20 (2) እና አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌዎች ጋር ይጣረሳል የሚል ክርክር ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ከባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ቀላል ከማይባሉ የፓርላማው አባላት ቀርቦበት ነበር። ‹‹በመናገርና በፕሬስ ነፃነት ላይ ገደብ ሊጣል የሚችለው የሐሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም፤›› በማለት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 (6) ላይ የሚደነግግ ሲሆን፣ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን ከዚህ የሚቃረን እንደሆነ አዋጁ በዝርዝር በታየባቸው መድረኮች ላይ የተገኙ ባለሙያዎችና የመብት ተሟጋቾች ተከራክረው ነበር።

ሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 29 (6) በታች ባስቀመጣቸው ድንጋጌዎች ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ልዩ ገደብ ሊጣል የሚችለው የጦርነት ቅስቀሳዎችን፣ የወጣቶች ደኅንነትን፣ ሰብዓዊና የሰውን ክብር የሚነኩትን ለመካላከል ብቻ እንደሆነ የሚደነግግ ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁ ግን ይህንን እንደማያሟላ ትችት ቀርቦበት ነበር።

ከወራት በፊት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለመገምገም አዲስ አበባ ተገኝተው የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ልዩ ራፖርተር ዴቪድ ኬይ፣ ተመሳሳይ ትችት በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰንዝረው ነበር።

ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አካል የሆነው ዓለም አቀፉ ሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን በአንቀጽ 20(2) ላይ ካስቀመጠው ድንጋጌ የሚጣረስ መሆኑንም ተናግረው ነበር። በዚህ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ድንጋጌ መሠረት መንግሥታት በብሔር፣ በዘርና በሃይማኖት ላይ መገለልን፣ እንዲሁም ግጭትን የሚያነሳሱ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን (አድቮኬሲ) በሕግ መከላከል እንዳለባቸው የሚገልጽ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የተረቀቀው ሕግ ግን ከዚህ በተቃራኒ ሁሉንም ዓይነት የጥላቻ ንግግሮች በወንጀል የሚቀጣ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል በማለት ማሻሻያ እንዲደረግበት በይፋ ደብዳቤ ጽፈው ነበር።

ረቂቅ አዋጁ ባለፈው ሐሙስ ለፓርላማው በቀረበበት ወቅትም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት የቀረበ ቢሆንም፣ ረቂቁን የመረመረው ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢና አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ከሕገ መንግሥቱ አይቃረንም የሚል ምላሽና ከሕግ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ የጎላ ክርክር ተደርጎበት በ23 ተቃውሞና በሁለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል ለጥላቻ ንግግርና ለሐሰተኛ መረጃ የተሰጡ ትርጓሜዎች ላይ የተደረጉ መጠነኛ ማሻሻያዎች ይገኙበታል።

በዚህም መሠረት የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ ብሔር፣ ብሔረሰብንና ሕዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ፆታን ወይም አካል ጉዳተኞችን መሠረት በማድረግ ሆን ተብሎ ጥላቻን፣ መድልኦን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር ማለት ነው የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

በተመሳሳይ ሐሰተኛ መረጃ ለሚለው ሐረግ መረጃው ሐሰት የሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነቱን በሚያውቅ ወይም መረጃውን የሚያሠራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር፣ የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳይደረግ የሚሠራጭ ሁከትን ወይም ግጭትን የሚያነሳሳ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የሚያደርግ የሐሰት መረጃ መሆኑን የሚያመለክት ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

ሌላው ከሕገ መንግሥቱ ይጣረሳል የሚል ክርክር ቀርቦበት የነበረው በውጭ አገሮች ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ዕውቅና የመስጠትና የመፈጸም ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፣ ይህንንም አዋጅ ምክር ቤቱ በሁለት ተቃውሞና በሁለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

ይህንን ስምምነት ማፅደቅ በኢትዮጵያ ላይ ከሚያስከትላቸው ግዴታዎች መካከል ዋነኛው በውጭ አገር የግልግል ዳኝነት የተሰጡ ውሳኔዎችን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ የማስፈጸም ግዴታ አንዱ ሲሆን፣ በውሳኔው ላይ በኢትዮጵያ የሕግ ሥነ ሥርዓት መሠረትም ሆነ ውሳኔውን ባሳለፈው የውጭ አገር የዳኝነት አካል ላይ ይግባኝ ማለት የማይቻል መሆኑ ሌላው ግዴታ ነው።

 በዚህም ምክንያት ስምምነቱን ማፅደቅ የኢትዮጵያን የዳኝነት ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው የሚል ክርክር ቀርቦበት ነበር። ነገር ግን በምክር ቤቱ የዳኝነት ሉዓላዊነትን አይጋፋም የሚል ምላሽ ተሰጥቶ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱም ሕጎች ላይ ከሕገ መንግሥቱ የሚጣረሱ ናቸው የሚል ክርክር የቀረበባቸውን ድንጋጌዎች ፓርላማው ለብቻ በጭብጥነት ይዞ በገለልተኛ ባለሙያ ለማጥራት ያደረገው ሙከራ የለም፡፡ በተመሳሳይም በዚሁ ነጥብ ላይ ብቻ የምክር ቤቱ አባላት ድምፅ እንዲሰጡ አላደረገም።

በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ በዚሁ ዕለት ካፀደቃቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል የኤክሳይስ ታክስ ይገኝበታል፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ መጠነኛ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን፣ እነዚህም እስከ 1,300 ሲሲ ጉልበት ባላቸው አዳዲስ አውቶሞቢሎች ላይ እንዲጣል ቀርቦ የነበረው የታክስ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ሲደረግ፣ በሲጋራ ምርቶች ላይ ደግሞ ከፍ ያለ ታክስ እንዲጣል ተሻሽሎ ፀድቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ