Sunday, May 19, 2024

የሕግ ማስከበር ፈተናዎችንና ፖለቲካዊ ቀውሶችን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሥልጣን ዘመኑ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ የሚገኘው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ወር (በየካቲት ወር) ዕረፍት ከመውጣቱ አስቀድሞ ወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በአባላቱ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ በተጠራው ልዩ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/)፣ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የፀጥታናሕግ ማስከበር ችግሮችን በተመለከተ ሰፊ ጊዜ ወስደው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በተካሄደው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካካል በርካቶቹ በሕግ ማስከበር ችግሮች የተነሳ የዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ መውደቁን የተመለከቱና መንግሥት ሕግን በማስከበር በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ያልቻለበትን ምክንያት የተመለከቱ ነበሩ፡፡

በዚህም ስለታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችበደምቢዶሎና አካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ኃይል እየፈጠረ ያለውን ችግር በፍጥነት ለመፍታት ለምን እንዳልተቻለ፣ እንዲሁም ስለቀጣይ መፍትሔውበዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎችን ሕይወት እያጠፋ ስላለው ግጭትናአጠቃላይ የአገሪቱን ሰላም በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል፡፡ ለቀረቡላቻው ጥያቄዎች በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ እሳቸው ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት በአገሪቱ ነበሩ ያሏቸውን ችግሮችን ማሳወቅ ጠቃሚ የችግሩን ሁኔታ ከእነ ምሉ ሥዕሉ ለመረዳት ጠቃሚ እደንደሆነ በመግለጽ ዘለግ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እንደ አገር መቀጠል በማትችልበት፣ አገረ መንግሥቱም እስከ ታችኛው መዋቅር በግለሰቦች እጅ ወድቆ፣ መደበኛ ያልሆነውና በጥቅም፣ በዝምድናና በትውውቅ የተሳሰረ ጥልፍልፎሽ ውስጥ ተዘፍቃ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ሥልጣን ስንረከብ የነበረውን መንግሥታዊ ጥልፍልፍ ኔትወርክ ለመፍታት የሚያስችል ቁልፍ ለማግኘት ይቅርና ኔትዎወርኩን ለማወቅ እንኳ ጊዜ ወስዶብናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይህ ያልተገባ ትስስር በዘር፣ በጓደኝነት፣ በጥቅምና በዝምድና መንግሥትን ወርሶ መንግሥታዊ ሥራን አዳጋች አድርጎ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ይህ መዋቅር ከላይኛው መንግሥት አካል እስከ ታችኛው አስፈጻሚ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀና እርስ በእርሱ የሚናበብ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መዋቅሩ ሲፈልግ ሥራዎችን ማስቆም ሲፈልግ ደግሞ የማስኬድ አቅም እንደነበረውም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጊዜያት የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ሁኔታዎች እንደነበሩና አገሪቱን ማንኮታኮት የሚቻለውም በዚህ ጊዜ ነው በማለት የተለያዩ ጥረቶች መካሄዳቸውን አስታውሰው፣ ለአብነትም አልሸባብ ሲፈጽመው የነበረውን ጥቃት መከላከል መቻሉንና ይህ ባይሆን ግን አደጋው የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር አብራርተዋል።

 ከእነዚህ የውጭ የጥፋት ኃይሎች ጋር የአገር ውስጥ ኃይሎችም ተባብረው ሲሠሩና አሁንም እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ ሊያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች ዝርዝር በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ ኔትወርኩም ሆነ አጠቃላይ ሁኔታው ሥራዎችን ለማስተጓጎል ቢሞክርም፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና እንዲታገሉ ከማድረግ፣ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ፣ አፋኝ ሕጎችን ከመቀየር፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ከማስቻል፣ እንዲዘጉ ተደርገው የነበሩ በርካታ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ከመፍቀድና ሌሎችንም ዕርምጃዎች ከመውሰድ መንግሥታቸው እንዳልተቆጠበ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን እየተስተዋሉ ያሉ የፀጥታ ችግሮችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ በአገሪቱ ያልተለመዱ አስነዋሪ ነገሮች ባህል እየሆኑ መምጣታቸውን አውስተዋል፡፡

ሙስሊሞች መስጊድ በሚሰግዱበትክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያናት በሚያመልኩበት ወቅት ፖሊስ አቁሞ ጥበቃ ማድረግ በኢትዮጵያ አለመለመዱን፣ በጦርነት ወቅት እንኳን ስህተት ካላጋጠመ በስተቀር የአምልኮ ሥፍራዎች ላይ ወታደሮች ጥቃት እንደማያደርሱ፣ ይህንን ማድረግ በሞራልም ሆነ በሕግ ተቀባይነት እንደሌለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ የአምልኮ ሥፍራዎችን የግጭት ማዕከል የማድረግ አስነዋሪ ድርጊት በአገሪቱ እየተለመደ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

 ይህ ሁኔታም ስፖርታዊ ውድድሮችን ለመመልከት ስታዲየም በገቡ ተመልካቾች መካከልም እየተከሰተ በመሆኑ፣ መንግሥት ፖሊስ አቁሞ የመጠበቅ ሥራ ውስጥ እንዲገባ መገደዱን አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን ከውጭ የታጠቀ ኃይል እንዳያጠቃ ፖሊስ ጥበቃ እንዲያደርግ ይመደባል እንጂ፣ በውስጥ ያሉ ጓደኛሞችና የአንድ አገር ልጆች የሆኑ ተማሪዎች በመፀዳጃ ቤትና በዶርሚተሪ (ማደሪያ ክፍሎች) ይገዳደላሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ አስነዋሪ ነገሮች መፈጠራቸውና ልምምድ እየተደረገባቸው መሆኑ አስከፊ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተወሰኑ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ዕገታ ተፈጽሟል መባሉን፣ መንግሥትም ይህንን ተግባር በፍጥነት በመፍታትና መረጃን ለማኅበረሰቡ በማድረስ ረገድ ቸልተኝነት አሳይቷል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ መንግሥት የተባለውን ዕገታ ማን እንደፈጸመው ለማወቅና የታገቱትን ለማስለቀቅ በጥንቃቄ እየሠራ መሆኑንመረጃ ለመስጠት የተቸገረውም ታገቱ የተባሉትን ተማሪዎች በሕይወት ለማስለቀቅ፣ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸውና በማኅበረሰቡ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ስሜት ከግምት በማስገባት መቆጠቡን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማሪዎችን ለፖለቲካ ፍጆታ ሲል ያገተ አካል ዕገታውን ስለመፈጸሙና ኃላፊነቱንም እንደሚወስድ ይፋ እንደሚያደርግ፣ ይህም በተለያዩ አገሮች የተለመደ እንደሆነታግተዋል የተባሉት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በተመለከተ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ታገቱ የተባሉትን ተማሪዎችንም ሆነ ነዋሪዎችን ለማስለቀቅአገር መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው በሚገኙ መላ ቀበሌዎችና ወረዳዎች አሰሳ ቢያደርግም፣ አንድም የታገተ ወይም በዕገታ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት ወይም ሞቶ የተገኘ ሰው ማግኘት አለመቻለሉን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የታገተ ተማሪም ሆነ ነዋሪ የለም እንደይባል ደግሞ ታግተዋል ተብለው ስማቸው ከተገለጹ ተማሪዎች መካከል ቤተሰቦቻቸው ጋር ያልደረሱ በመኖራቸው ምክንያት፣ መረጃ ከመስጠት መቆጠብ እንደሚገባ መንግሥት በማመኑ መረጃዎችን አለመግለጹን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ አሰሳ አድርጎ የታገተ ተማሪ ባለማግኘቱታግተዋል ተብለው ስማቸው ከተዘረዘሩት ውስጥ ተማሪዎች ያልሆኑ ግለሰቦች በመገኘታቸው፣ አንዳንዶቹም ታግተዋል ከተባሉበት ሥፍራ ውጪ መኖራቸውን የሚያስረዳ መረጃ በመገኘቱ ምክንያት፣ መንግሥትን የታገተ ተማሪ የለም ወደሚል ድምዳሜ ገፍቶት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ልጆቹን ያላገኘ ወላጅ በመኖሩ፣ እንዲሁም እያንዳንዱን ወላጅ የሚያሳስብ በመሆኑ ተማሪዎቹ ወደ ሱዳን ተሰደውም ይሁን፣ ታግተውም ይሁን፣ ተደብቀውም ይሁን ምርመራው እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የተከሰተው ከሩቅ በመጣ ጠላት አይደለም፡፡ ችግር ፈጣሪውን እንደ ውጭ ጠላት በቀላሉ ማስወገድ አልተቻለም፡፡ እንክርዳዱን ለመንቀል ብለን ስንዴውን እንዳንነቅል የምናደርገው ጥረት ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ የእኛ ዋነኛ ፍላጎትም የሰው ሕይወት ሳይጠፋ በሕይወት እንዲገኝ ነው፡፡ ይህን ለማድረግም ሁሉም የየበኩሉን እየሠራ ነው፤›› ብለዋል።

የተማሪዎቹ አድራሻ እስኪታወቅ ድረስ መረጃዎች እንዲያዙ ቢደረግም፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያሳተፈ ኮሚቴ ተዋቅሮ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝና ኦፕሬሽኑ የደረሰበትን የመጨረሻ ሪፖርት ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በወለጋ አካባቢ ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ መንግሥት ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

በወለጋ አካባቢ ያለው ችግር በተማሪዎች ላይ ብቻ የተፈጸመ እንዳልሆነ፣ በባለሀብቶችና በአካባቢው አመራሮች ላይም ጉዳት መድረሱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በውጭ ስደት ላይ የነበሩ ፖለቲከኞችን መንግሥት ለለውጡ ሲል በሰላም እንዲታገሉ ቢያስገባም፣ በምዕራብ ወለጋ ግን ያለው ሁኔታ ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ጊዜ ማብቃት ስላለበት በዚህ አካባቢ ያለው ችግር ሊፈታ የሚችለው በሰላም ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምክንያቱምመከላከያ ሠራዊት ዕርምጃ ወስዶ ችግሩን ለመፍታት ቢሞክርሚያኮራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወንድሙን ነው የሚገድለውንፁኃንም ይጎዳሉ፡፡ በመሆኑም በሰላም ለመፍታት ጥረት ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በአንድ አገር ሁለት የታጠቀና ሁለት መንግሥት ስለማይኖር፣ ሕጋዊው መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል፡፡ በሰላም ለመፍታት ፍላጎት ያለው አካል ከመጣ መንግሥት በደስታ እንደሚቀበለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን በአገሪቱ ያለው አካሄድ መንግሥትን በሁለት አጣብቂኞች ውስጥ ከቶ ደካማ ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

አንደኛው ሰላምማስከበር መንግሥት አልቻለም የሚል ትልቅ ድምፅ ማሰማት፣ ያው እንደገና መልኩን ቀይሮ በምዕራብ ወለጋ ሕዝብ ፈጃችሁ የሚል ድምፅ በማሰማት፣ በሁለቱም ጫፍ መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት እየተሞከረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ የፖለቲካ ሥልት ለጊዜው ነው ውጤት የሚያስገኘው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የሚፈጠር ቅራኔ ወደ ከፋ ጫፍ የሚወስድ ነው፡፡ ለጊዜው ብልጽግና ፓርቲ የገጠመው ፈተና ሊመስልችላል፡፡ በኋላ ግን ሀለቱን ሕዝቦች ወደ ከፍተኛራኔ የሚያስገባ ስለሆነ፣ ይህንን ፖለቲካ ብለው የሚጫወቱ ኃይሎች በማስተዋልና በጥበብ የሚሠሩበትን መንገድ ቢከተሉ ጥሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከግብፅና ሱዳን ጋር እየተደረገ ያለውን ድርድር በተመለከተ ማብራርያ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጠያቄ በሰጡት ምላሽ፣ እስካሁን በተላለፈው ውሳኔ አበረታች ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። ‹‹የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ባለበት ሁኔታ በተለይ በድርድር ሒደት የኢትዮጵያ መሪዎች ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡ ወደ ፊትም የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ስምምነት ፈፅሞ አይደረግም፡፡ ሌላው ሳይጎዳ እኛ የምንጠቀምበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይሠራል፤›› ብለዋል።

ቀጣዩ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድና በአገሪቱ በሚታየው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቀጣዩን ምርጫ እንዴት ማካሄድ እንደሚቻል የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምርጫው የሚካሄድበትን ወቅት በትክክል እንደማያውቁና ምክር ቤቱ መረጃውን ከምርጫ ቦርድ መጠየቅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሥራ ላይ ያለ የተመረጠ መንግሥት የምርጫ ዘመኑ ከመጠናቀቁ ከአንድ ወር በፊት መከናወን እንዳለበት ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ፣ ከዚህ ውጪ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ አያስችልም ተብሎ የቀረበ ጥያቄን አስመልከቶ በሰጡት ምላሽ ደግሞ፣ ‹‹እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም በዚህ ጊዜ ይረጋገጣል ብሎ ዋስትና መስጠት የሚችል አንድ ሰው የለም፡፡ ስድስት ወር፣ ዓመትም ይሁን ሁለት ዓመት ከዚያ በኋላ የተሟላ ሰላም ይፈጠራል ብሎ መናገር የሚያስችል ምንም መሠረት የለም፤›› ብለዋል፡፡

ምርጫው ዛሬም ሆነ ነገ ቢደረግ ገጽታው ይለያያል እንጂ ችግር እንደሚኖር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ቦርድን በማገዝ፣ ፓርቲዎች በፈረሙት ሰነድ መሠረት በዲሲፕሊን ተገዝተው ተባባሪ በመሆን፣ ምርጫው የዜጎች ድምፅ ማሰሚያ እንጂ መጋደያ እንዳይሆን ጥበቃ በማድረግ፣ መንግሥት አስፈላጊውን ሎጂስቲክስ፣ ጥበቃና ድጋፍ በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከተባበሩና ምርጫ ቦርድን ካገዙ ፈታኝ ቢሆንም፣ ምርጫው ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -