Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኦነግ በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ ለተፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ነው አለ

ኦነግ በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ ለተፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ነው አለ

ቀን:

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና በደቡብ ዞኖች እየተፈጸመ ላለው ‹‹እሮሮና ሰቆቃ›› ተጠያቂ ነው ሲል፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከሰሰ፡፡

‹‹ይኼ ችግር በአስቸኳይ ካልተገታ በስተቀር ከዚህም ወደ ባሰ ሁኔታ አድጎ ከማንም ቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታችን እየጨመረ መሆኑን፣ በድጋሚ አስረግጠን ልንገልጽ እንወዳለን፤›› ሲል በመግለጫው ያተተው ኦነግ፣ ‹‹ሆን ተብሎ በዶ/ር ዓብይ አህመድ በሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላማዊ ሕዝባችን ላይ እየፈጸመ ያለውን ይኼንን እሮሮና ሰቆቃ እጅግ አጥብቀን እናወግዛለን፤›› በማለት እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡

መንግሥት በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን አቋርጧል ያለው ኦነግ፣ ‹‹የመንግሥት ወታደሮችና ታጣቂዎች በሰላማዊ (ትጥቅ አልባ) ዜጎች ላይ እያካሄዱ ባሉት ግድያ የሰዎች ሕይወት እንደ ቅጠል እየረገፈ መሆኑ›› መረጃ እንደ ደረሰው የሚያትተው ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የወጣው የኦነግ መግለጫ፣ በተለይ በምራብና በቄለም ወለጋ እየተፈጸመ ያለው ‹‹ግድያና ጭፍጨፋ›› በቃላት መግለጽ አዳጋች ነው ብሏል፡፡ በዚህ ሳቢያም ድርጊቶቹን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የጦር ወንጀል የሚሉ ሐረጎች ሊገልጿቸው አይችሉም ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ስለዚህም የተጠቀሱት ችግሮች ተቀርፈው መፍትሔ ይመጣ ዘንድ ‹‹በግድያና ጭፍጨፋ፣ በእስራትና በማንኛውም መንገድ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በመንግሥት እየተካሄደ ያለው ይኼ እሮሮና ማሰቃየት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ይኼንን እያካሄዱ ያሉት የመንግሥት ኃይሎች ወደ ካምፕ እንዲመለሱ፣ ያሉት ችግሮች በውይይትና በሰላም መፍትሔ የሚያገኙበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያመቻች፣ ከዚህ ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲኖሩ፣ ከደረሰባቸው ጉዳት የሚያገግሙበት ዕገዛም እንዲደረግላቸው፣ እንዲሁም እየደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ በነፃና ገለልተኛ አካል አስፈላጊ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግ፤›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይኼንን ጉዳይ በሚመለከት ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ በምዕራብና በጉጂ ኦሮሚያ ዞኖች እየተካሄዱ ያሉ የመንግሥት ዘመቻዎችን አረጋግጠው፣ በጉጂ ዞን ያለው ከአካባቢው አባ ገዳዎች ጋር በተደረገ ውይይት ቀንሷል ብለዋል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ደግሞ ኢንተርኔትና ስልክ መቋረጡን ገልጸው፣ መንግሥት በአካባቢው እየተደረገ ካለው ዘመቻ ጋር እንደሚገናኝና በቅርቡ መፍትሔ እንደሚያገኝም አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ የኦሮሚያ ዞኖች በተለይ ክልሉ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ የበርካታ ዜጎችና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሚገደሉባቸው ሥፍራዎችም ናቸው፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ ታግተዋል የተባሉ ነገር ግን መንግሥት በማን፣ የትና መቼ እንደታገቱ ሊገልጽ ያልቻለው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይም የዚህ አካባቢ አንዱ የቅርብ ክስተት ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...