Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሦስት ኢትዮጵያውያንና አንድ ቻይናዊ ክትትል እየተደረገላቸው ነው

በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሦስት ኢትዮጵያውያንና አንድ ቻይናዊ ክትትል እየተደረገላቸው ነው

ቀን:

በኖቭል ኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ባይኖርም ከቻይና በቅርቡ የመጡ አራት ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በበሽታው ከተጠረጠሩት አራት ሰዎች መካከልም ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንደኛው ግን ቻይናዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በቦሌ ጨፌ፣ ቻይናዊው ደግሞ በአክሱም ለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡ የሁሉም ተጠርጣሪዎችን ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የላቦራቶሪ ናሙናዎቻቸው ግን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ቀደም ሲል በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩ አራት ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

ኢንስቲትዩቱ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ወቅታዊ መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ አጋሮች ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትና በ27 የድንበር ኬላዎች የሚካሄደው የማጣራት ምርመራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

እስከ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለ47,162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ መደረጉን ጠቁመው፣ ከእነዚህም ውስጥ 1605 ተጓዦች የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገሮች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የአንድ ሰው የሙቀት መጠን ከ38 ዲግሪ ሴሊሽየስ በላይ ከሆነ፣ እንዲሁም ጉንፋን መሰል ምልክቶችን የሚያሳዩና የቻይና የጉዞ ሰነድ ያለው ከሆነ ለኅብረተሰቡ፣ ለተጓዡና ለቤተሰቡ ደኅንነት ሲባል የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው አግባብ መሠረት ለ14 ቀናት ያህል በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን ብሔራዊ ታክስ ፎርስና በኢንስቲትዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጥ ማዕከል ተቋቁሞ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ ከኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከሌሎችም የግልና የመንግሥት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎችና ለሆስፒታል አመራሮች በቫይረሱ ዙሪያ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ በተዘረጋው የባቡር ትራንስፖርት የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች ሲጠቀሙበትና በዚህም የበሽታው ቫይረስ ሊገባበት የሚችል መስመር ሆኖ በመገኘቱ፣ በድሬዳዋ ባቡር ጣቢያና በኤርፖርቱ የልየታ ሥራ ተጀምሯል፡፡ የልየታ ሥራውንም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እያከናወነ ያለው ከኢንስቲትዩቱ የተላከው ቡድን እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቦሌ ጨፌ ያለው የሕክምና ቦታ፣ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ለሕክምና መስጫነት እንደተመደቡ፣ ከእነዚህም መካከል የሕክምና መስጫ ቦታዎቹ የወረርሽኝ ሥርጭትን ለመቀነስ የሚታከሙበትን ያማከለ ሲሆን፣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ግን በጽኑ ሕሙማንና በሳንባ ሕመም ዘርፍ የአርቲፊሻል የሳንባ ሕክምና መርጃ መሣሪያ ሕክምና ለመስጠት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ  ውስጥ እስካሁን በበሽታው የተጠቃ ሰው እንደሌለ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ኤባ አገላለጽ፣ የኖቬል ኮሮና ማረጋገጫ ምርመራ ሪኤጀንት በዓለም ጤና ድርጅት ትብብር አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንደሚገባ፣ ሪኤጀንቱም በቫይረሱ የተጠቁ ታካሚዎችን በመለየትና አስፈላጊውን ዕርዳታ በመስጠት ለወረርሽኙ ቁጥጥር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው፣ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በቻይና ዉሃን ከተማ ከተከሰተበት ታኅሣሥ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 24 ቀን ድረስ 14,557 ቻይናውያን በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 304 ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡

ሌሎች የመረጃ ምንጮች (የጀንሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ) በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 17,373 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ 362 ታካሚዎች ደግሞ ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡

‹‹የሌሎች  አገሮች አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ አቋርጠዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን አላቋረጠም?›› ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኤባ አባተ (ዶ/ር) ሲመልሱ፣ ‹‹አየር መንገዱ የሚበርባቸው አምስት የቻይና ከተሞች ናቸው፡፡ በእነዚህም ከተሞች የሚታየው የበሽታው ሥርጭት ምጣኔ በጣም አነስተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች አገሮች ያደረጉትን የበረራ ማዕቀብ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውንና ሁሉም አገሮች የተቀበሉትን ኢንተርናሽናል ሔልዝ ሪጉሌሽን (አይኤችአር) 2005ን የጣሰ ነው በሚል ኮንኖታል፡፡ በረራውን ማቆም በሽታውን ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደናቅፍና እንደሚያውክም ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መግለጹን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ስለዚህ አገሮች በረራውን ከማቆማቸው በፊት ቆም ብለው ማሰብና በኤችአይአር 2005 የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ታሳቢ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰቡን ከዋናው ዳይሬክተር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ