ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ መንግሥት እየሠራባቸው እንዳለ ከገለጻቸው የሪፎርም (ማሻሻያ) ሥራዎች አንዱና ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲሆን፣ ፉክክርንና ትብብርን በማጣጣም ለሦስት ዓመታት የሚተገበር ‹‹የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ›› በማለት በጥቅል ኢኮኖሚውና በተናጠል ዘርፎች ሊያደርጋቸው ያሰባቸውን ለውጦች ነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነ መርሐ ግብር ላይ ነበር ይፋ ያደረገው፡፡
በዚህ ‹‹አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ›› ከተዳሰሱ ዘርፎች አንዱ የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ግብርናው ‹‹ለአጠቃላይ አገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ 70 በመቶ የሚሆነው የሰው ኃይል ነው በዚሁ ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይኼም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች 40 በመቶ አማካይ ድርሻ አንፃር በጣም ከፍተኛ ነው፤›› በማለት ሰነዱ ይገመግማል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአምራች ዘርፎች ችግሮችን በሚዘረዝርበት ክፍል፣ የግብርናው ዘርፍ ማነቆ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ይዘረዝራል፡፡ እነዚህም የተለዩ ችግሮች በደካማ የግብርና ግብዓትና አገልግሎት አቅርቦት ምክንያት ዝቅተኛ ምርታማነት መኖር፣ የመሬት ሊዝ አጠቃቀም መኖር፣ በግብርና አምራቾችና በሸማቾች መካከል የጠበቀ የገበያ ትብብር አለመኖር፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት በግብርና ምርምርና ጥናት እንዲሁም የመስኖ ልማት ተሳትፎ አናሳ መሆን፣ የገበያና የሎጂስቲክስ ችግር መኖርና ግብርና ተኮር የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት አለመኖር ናቸው ይላል፡፡
‹‹አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው›› በግብርና ዘርፍ ለሚታዩ ዝርዝር ችግሮች መፍሔ ያላቸውን ምላሾችም ያስቀመጠ ነው፡፡ እነዚህ መፍትሔዎች አነስተኛ የመሬት ባለቤት የሆኑ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብና ሌሎች የግብርና አገልግሎቶችን በመስጠት ምርታማነትን ማሳደግ፣ አነስተኛ ገበሬዎች መሬትን በሊዝ መብት ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ገበሬዎች በሰፋፊ እርሻዎች በአክሲዮን መልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል፣ የእንስሳት ሕክምና አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ ምርምርና የተሻሻለ አሠራርን በመዘርጋት፣ እንዲሁም ዘርፉ ከሌሎች ጋር የሚኖረውን ትስስር በማጎልበት የእንስሳት ሀብት ልማትን ማዘመን፣ በግብርና አምራቾችና ምርት ገበያ መካከል ውጤታማ የገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለት መፍጠር፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት በግብርናው ምርምርና ጥናት ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ የመካከለኛና ከፍተኛ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት እንዲቻል የግሉና የመንግሥት ዘርፍ ጥምረት የሚጎላበትን መንገድ ማመቻቸት፣ በተለየ ሁኔታ ለግብርናው ዘርፍ የሚያገለግሉ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለምሳሌ አነስተኛ የብድር ሥርዓት፣ የአዝርዕት ኢንሹራንስ፣ እንዲሁም የቅድመ አቅርቦት ኮንትራት ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት የሚሉ ሲሆኑ፣ የግብርናን ምርታማንት በማሳደግና አነስተኛ ማሳ ላይ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ገቢ ማሻሻል ግቦቹ እንደሆኑ የማሻሻያው ሰነድ ያስቀምጣል፡፡
ይኼ አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስቀምጠው የችግር ልየታ ትንታኔና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ወደ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች በመሄድ በዝርዝር እንደሚሠራባቸው በተገለጸው መሠረት፣ የግብርና ሚኒስቴር የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ ረቡዕ ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀው ወርኃዊው ‹‹አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ›› መርሐ ግብር ላይ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አማካሪ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር አማካሪና የአገር በቀል የግብርና ማሻሻያ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አንተነህ ግርማ (ዶ/ር) ባለፉት 15 ዓመታት ግብርናው በምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ዕድገት እንዳለው በማስታወስ፣ ግብርናው ግን በሚጠበቅበት ልክ ማደግ አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት የአገራዊ ሰብል ምርት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል እንደማይበልጥ በመግለጽ፣ አሁን ወደ 325 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉን፣ የስንዴ ምርታማነት በሔክታር ከ18 ኩንታል ወደ 25 ኩንታል፣ በቆሎ ደግሞ በሔክታር ከ19 ኩንታል ወደ 42 ኩንታል አድጓል ብለዋል፡፡ ወተት ከነበረበት 3.7 ሚሊዮን ሊትር ወደ አራት ቢሊዮን ሊትር ምርት መድረሱንም አስታውቀዋል፡፡ የግብርናው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ ከ19 ቢሊዮን ብር ወደ 27 ቢሊዮን ብር አድጓል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሆኖም ‹‹እነዚህ ለውጦች የመጡት መንግሥት መር በሆነ ርብርብ ነው፤›› ያሉት አንተነህ (ዶ/ር)፣ ከግብርናው ከዚህ በላይ እንደሚጠበቅና ለኢንዱስትሪው ግብዓት በማቅረብና ለውጪ ንግድ አሁን ካለው የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም ጥራት፣ ዘላቂ አቅርቦትና ምርታማነት ላይ በማተኮር አዳዲስ የግብርና ምርቶች ላይ መሥራት፣ የሥራ ዕድል መፍጠርና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣመ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
‹‹የአገር ኢኮኖሚ ሽግግር እንደፈጠረ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ምርታማነት ለመሄድ ግብርና መደገፍ አለበት፤›› የሚሉት አንተነህ (ዶ/ር)፣ እስካሁን ግብርናው በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ማነቆ የሆኑ ችግሮች ነበሩ ሲሉ ዘርዝረዋል፡፡
የመጀመርያው መሬት ሲሆን፣ ያልተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት መኖሩ፣ የግብርና መሬት ለሌላ ተግባር፣ የሌላ ተግባር መሬት ደግሞ ለግብርና መዋሉ፣ እንዲሁም የተበጣጠሰ መሬት ያለው አርሶ አደር ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሆኑን ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡
በሁለተኛነት የቴክኖሎጂና ሌሎች የግብርና ግብዓት አገልግሎቶች አቅርቦት ቀጣይነት የሌለውና በአብዛኛው በመንግሥት የተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሦስተኛው የግብርና ዘርፍ ማነቆ የፋይናንስ አቅርቦት መሆኑን፣ ግብርናው 33 በመቶ ለኢኮኖሚ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ዘርፍ ቢሆንም ከባንኮች ከሚሰጠው ጠቅላላ ብድር ግን አሥር በመቶ ብቻ እንደሚያገኝ በመጠቆም፣ መወዳደር ከማይገባው ዘርፎች ጋር እየተወዳደረ እንደሚገኝና በፋይናንስ እንዳልተደገፈ አስረድተዋል፡፡
በአራተኛ ደረጃ ያነሱት ማነቆ ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጠው የመድን (ኢንሹራንስ) ሽፋን ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ አምስተኛው ማነቆ የምርት ሥርዓቱ ያልዘመነ መሆኑና የተመረተው ደግሞ አርሶ አደሩን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የማያበረታታው እንደሆነ ነው፡፡
በስድስተኛነት ያነሱት ማነቆ ግብርናው በዝናብ ላይ ጥገኛ በመሆኑ መስኖ መስፋፋት ነበረበት ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተሠሩ ግን ጥቅም ላይ ያልዋሉ የመስኖ መሬትን የማበላሸት ሚና ነበራቸው ሲሉም ግምገማቸውን አስረድተዋል፡፡
ሰባተኛው ማነቆ በግብርናው ዘርፍ የግል ዘርፉ እንዲሳተፍ የሚያበረታታ ሥርዓት አለመኖሩን በመግለጽ፣ ስምንተኛውና የመጨረሻ ተብሎ በቴክኒክ ቡድኑ የተለየው ማነቆ የመንግሥት የማስፈጸም አቅም ደካማነት ነው ብለዋል፡፡
ስለዚህም ይላሉ አንተነህ (ዶ/ር)፣ የግብርናውም ሆነ የጠቅላላ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ዘግይቷል ሲሉ ይደመድማሉ፡፡
እነዚህን ማነቆዎች ለማስወገድ የአስተሳሰብ፣ የሥርዓትና የአሠራር ለውጥ ለማምጣት መሥራት እንደሚገባና ትኩረት እየተሰጠው እንደሚገኝም በመጠቆም፣ ‹‹ይኼንን በመለወጥ የተሻገረ ግብርና ማየት አለብን ይኼም ውስጣዊና ውጫዊ መዋቅራዊ ሽግግር የሚያመጣ ሲሆን ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
‹‹በዘርፉ ተዋንያን ድርሻ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ብቻውን ችግሮቹን መወጣት አይቻልም፤›› በማለት ያከሉት አማካሪው፣ የመንግሥት ተቋማትን ትኩረት መከለስና አቅርቦት ላይ ብቻ የነበረን ትኩረት ምርትና ምርታማንትን ከማሳደግ በዘለለ፣ በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ግብርና የገጠርና የከተማን ትስስር አስቦ መሥራት ይኖርበታል፣ የገጠር ከተሞችን አስቦ መሥራት ለግብርና ዕድገት ወሳኝ ነው በማለት ያስገነዘቡት አንተነህ (ዶ/ር)፣ እነዚህን የአስተሳሰብ ለውጦች ለማምጣት ደግሞ ሕግና ሥርዓት ያስፈልጋል በማለት፣ መንግሥት መሬትን የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም እንዲኖርና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ለማውጣት እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የተበጣጠሰ መሬትን፣ እንደ ኩታ ገጠም ያሉ እርሻዎችን በሕግ በመደገፍና ግብርናውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ እንዲሁም የግብዓት አቅርቦት በግል ድርጅቶች እንዲቀርብ ማድረግ፣ ባንኮች ከብድራቸው ከ30 እስከ 40 በመቶ ለግብርና እንዲሰጡ ማድረግና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳደግ የግብርና ባንክ፣ የኅብረት ሥራ ባንኮችን ማስፋት፣ እንዲሁም ሌላ የፋይናንስ አማራጮችን ማመቻቸት መንግሥት የሚሠራባቸው ትኩረቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በአሠራር ረገድ ዘላቂና አሳታፊ ግብርናን መፍጠር፣ እንዲሁም በአጭርና በረዥም ርቀት ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር አቀናጅቶ መሥራትና የልማት ፋይናንስ አማራጮችን መፈለግ ሊሠራባቸው የታሰቡ የማሻሻያ ዘርፎች ናቸው ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ሐሳብ አቅራቢ የነበሩት ወርቅነህ አያሌው (ዶ/ር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሪፎርም ሐሳቦች ተጠናክረው መሄድ እንዳለባቸው በማሳሰብ፣ የመሬት አጠቃቀምን የተመለከተ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑ እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቱን ወደ ግብርና ለመሳብ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በማተኮር መሥራትና የከተማ የእንስሳት ዕርባታን አስቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የእንስሳት ሀብት ልማት ሲታሰብ ትርፋማነቱና ምርታማነቱ እኩል ሊታሰብ ይገባል በማለት፣ እስካሁን በምርት ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ መቆየቱን በመተቸት አዋጭነቱና ትርፋማነቱ ከግንዛቤ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የማሻሻያው የበጀት ድጋፍ ከፍላጎት ጋር መጣጣም አለበትና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ቢደረግ ብለዋል፡፡
ሌላው በመድረኩ ሐሳብ አቅራቢ የነበሩት ዓለማየሁ ሥዩም (ፕሮፌሰር) የግብርናው ጥያቄ የተወሳሰበ ነውና ዘለቄታዊ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ሥራ ይጠይቃል ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
ስለዚህ በቀናነት መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ላይ እንዲያተኩር፣ የመሬት መራቆት ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት እንዲሁም የፖሊሲ ቀረጻና ትግበራ አቅም ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ድርጅት የሆነው የሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፣ የግል ባለሀብቱ ችግሩ ተፈትቶለት ወደ ሥራው በትጋት እንዲሰማራ ሦስት ችግሮች መፈታት አለባቸው ይላሉ፡፡ እነዚህም ተሰሚነት ማጣት፣ የግንዛቤ እጥረትና አላስፈላጊ ቁጥጥሮች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከውይይቱ ጎን ለጎን ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የመሬት ዘርፍ አጥኚውና ተመራማሪው አቶ ደሳለኝ ራህመቶ መሬትን የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ተቋም እንዲኖር መታሰቡ መልካም ዕርምጃ ነው በማለት፣ ዋናው ጉዳይ ግን ተቋሙ ገለልተኛ መደረጉና በበጀትና በመሳሰሉ ጉዳዮች ከተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን ማድረጉ ነው ይላሉ፡፡ የዚህ ተቋም ዋና ተግባርም አገልግሎት መስጠት ስለሚሆን መረጃንና ቴክኖሎጂን፣ እንዲሁም የመሬት ላይ ተግባራትን መመዝገብ ሥራው ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ገለልተኛነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ፡፡