የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል መንፈቅ ላልሞላ ጊዜ የአክሲዮን ሽያጭ ሲያካሄድ የቆየው አማራ ባንክ፣ በአክሲዮን ሽያጭ እያሰባሰበ ያለውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉ ተገለጸ፡፡
የአማራ ባንክን የአክሲዮን ሽያጭ የሚያመላክቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ ችሏል፡፡ የተፈረመ ካፒታሉም ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህም በአገሪቱ ባንኮች ታሪክ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ የሚገባ ብቸኛ ባንክ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለት ጊዜ የአክሲዮን ሽያጭ ያራዘመው ባንኩ የአክሲዮን ሽያጩን ከጀመረ ስድስት ወራት ገደማ ቢሆንም፣ እስካሁን ማሰባሰብ የቻለው የካፒታል መጠን የግል ባንኮች ወደ ሥራ ሲገቡ ይዘው ከተነሱት ካፒታል መጠን አንፃር ሲታይ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ የአክሲዮን ሽያጩን እስከ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ፣ አሁን ካሰባሰበው ካፒታል በላይ ማሰባሰብ የሚያስችለው ዕድል ይኖራል ተብሏል፡፡
አማራ ባንክ በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ በተለይ ሊታይ የሚችልበት ሌላው ገጽታ፣ እስካሁን የደረሰበት የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ እስካሁን የባንኩን አክሲዮኖች የገዙ ግለሰቦችና ተቋማት ቁጥር ከ70 ሺሕ በላይ መድረሱ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በባንክም ሆነ በሌሎች የቢዝነስ ተቋማት ውስጥ በዚህ ያህል ቁጥር ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበ ኩባንያ እንደሌለ ይነገራል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል የያዙዋቸው ባለአክሲዮኖች ቁጥራቸው ወደ 180 ሺሕ አካባቢ እንደሚደርስ መረጃዎች የሚያሳዩ ስለሆነ፣ ይህም አማራ ባንክን በአገሪቱ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖችን የያዘ ብቸኛ የፋይናንስ ተቋም ያደርገዋል፡፡
በሥራ ላይ ካሉ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባያዎች ውስጥ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ይዘዋል ተብለው ከሚታወቁት ውስጥ እናት ባንክና ብርሃን ባንክ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ የባለአክሲዮኖቻቸው ቁጥር ከ18 ሺሕ ያልዘለለ ነው፡፡
የአብዛኞቹ ባንኮች ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከሰባት ሺሕ ያነሰ ሲሆን፣ በተለይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ቀድመው የተቀላቀሉት ባንኮች የባለአክሲዮኖቸው ቁጥር እምብዛም የጨመረ ባለመሆኑ፣ ከ3,500 እስከ 7,000 ባለአክሲዮኖችን ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት ከግል ባንኮች የተፈቀደ ካፒታሉን 12 ቢሊዮን ብር በማድረስ ቀዳሚ የሆነው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ የተፈቀደ ካፒታላቸውን ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረስ ከወሰኑ ባንኮች መካከል አቢሲኒያ፣ ንብ ኢንተርናሽናልና ዳሸን ባንኮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሆኖም የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ያደረሰ አንድም የግል ባንክ የለም፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች አሁን ያላቸው የተከፈለ ካፒታል ከ1.5 ቢሊዮን ብር እስከ 3.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ ግን የተከፈለ ካፒታሉ ወደ 4.2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ አማራ ባንክ አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ ለመግባት ዕቅድ አለው፡፡ ባንኩ ለመሥራት የሚያስችለውን የተከፈለ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል የአክሲዮን ሽያጩን ያሟላው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ወደ ሥራ ለመግባት የሚችልበትን ካፒታል ቢይዝም ሥራ ለመጀመር የዘገየውና ሁለት ጊዜ የአክሲዮን ሽያጩን ያራዘመው፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሕግ ስለተፈቀደላቸው ባለአክሲዮን ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
አማራ ባንክን ለመመሥረት በአደራጅነት ከሚጠቀሱት መካከል የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ አንዱ ሲሆኑ፣ የአደራጅ ኮሚቴውንም በሰብሳቢነት እየመሩ ነው፡፡