Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወጋገን ባንክ እስከ 150 ሚሊዮን ብር የሚገመት የብድር ወለድ ቅናሽ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወጋገን ባንክ በብድር ወለድ ምጣኔው ላይ እስከ ሦስት በመቶ የሚጠጋ ቅናሽ እንዳደረገ አስታወቀ፡፡ ዕርምጃው እስከ 150 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ቅናሽ በገቢው ላይ እንደሚያስከትልበት ገልጿል፡፡

 ባንኩ የብርድ ወለድ የሚያስከፍልበት መጠን ላይ ለውጥ ማድረጉን ይፋ ባደረገበት መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ በሚሰጣቸው ብድሮች ላይ ከ0.5 እስከ ሦስት በመቶ የወለድ ማስከፈያ ምጣኔ ማሻሻያ አድርጓል፡፡

ሐሙስ፣ ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ወቅት የባንኩ የብድርና ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በሪሁን ደስታ ‹‹በአገር ደረጃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው መቀዛቀዝ በማሳየቱ በብድር አከፋፈል ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሄዱ ነው፤›› በማለት፣ የብድር ወለድ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ካስፈለገበት ምክንያት ውስጥ አንዱ ዕርምጃ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

 ከዚህ ባሻገር መንግሥት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታትና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እንዲሁም አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለመሥራት ያለውን ምቹ ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እያደረገ በመሆኑ፣ የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ኢንቨስትመንቱን ከማበረታታት አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማመን ቅናሽ ለማድረግ እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔን ለመቀነስ ባንኩ ከውሳኔ የደረሰበት ሌላው ነጥብ ደግሞ፣ የተወዳዳሪ ባንኮችንም አካሄድ በማየት በጋራ ለመራመድ በማሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 እንዲህ ባለው ዕርምጃ የተለያዩ የኢኮኖሚ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸው ብቻም ሳይሆን፣ በባንክ ኢንዱስትሪው አብዛኛው ሀብት ያለው በብድር ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ በሪሁን፣ ይህንን የብድር ሀብትን ጥራት ወይም የጥራት ችግር ሳይገጥመው በዘላቂነት አስጠብቆ መጓዝ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ የተበላሹ ብድሮች እንዳይፈጠሩም ይረዳል ብለዋል፡፡ የብድር አመላለስን በተገቢው መንገድ ለማስጠበቅ እንዲሁም ተበዳሪዎች ወለድ ሲቀንስላቸው የመክፈል ፍላጎታቸው እንዲጨምር ለማድረግ ያግዛል ተብሏል፡፡ በቅርቡ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ በመነሳቱ ባንኩ ለወሰደው ዕርምጃ ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የወለድ ምጣኔው ላይ የተደረገው ቅናሽ እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 1 ቀን 2020 ጀምሮ እንደሚተገበር የገለጹት የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንትና ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ክንዴ አበበ ናቸው፡፡ ባንኩ እስካሁን ካፈራው 35 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ውስጥ 22 ቢሊዮን ብሩ የብድር እንደሆነና ሰባት ቢሊዮን ብርም ለ27 በመቶ የቦንድ ግዥ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ 29 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው የባንኩ የፋይናንስ ሀብት ከብድርና ከተያያዥ ንብረቶች የተመዘገበ ሆኖ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር ገንዘብ በየቀኑ ለመመለስ መስማማቱና ከዚህ በኋላ ተጨማሪ የቦንድ ግዥ በባንኮች ላይ እንደማይጥል በማስታወቁ፣ ባንኩ የወለድ ቅናሽ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ባንኩ የ22 ቢሊዮን ብር ብድር ለደንበኞች በማቅረቡ ይህን ያህል ገንዘብ ላይም ባለው የኢኮኖሚ ጫና ምክንያትና ባንኩም ተበዳሪዎችን ለማገዝ ካለፈው ፍላጎት በመነሳት የትርፍ ህዳጉን ቀንሶ የወለድ ማስከፈያ ለውጥ እንዳደረገ ተብራርቷል፡፡ ባንኮች የአገሪቱን የኢኮኖሚ ጫና መጋራት ስላለባቸው ወለድ መቀነስም ስለሚገባ ይህንኑ አድርገናል ብለዋል፡፡ ባንኩ የብድር ማስከፈለያ ወለድ ላይ ቅናሽ በማድረጉ፣ በዓመት ከ100 እስከ 150 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያሳጣው ተገልጿል፡፡

በተለይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ዘርፎች የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ  እስከ ሦስት በመቶ የሚደርስ እንደሆነም የገለጹት ኃላፊዎች፣ ይህ ማለት ግን የተጠቀሰው መጠን ላይ ድርድር አይኖርም ማለት እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡

ባንኩ በብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ካደረገው ማሻሻያ በተጨማሪ የ2012 ዓ.ም. የስድስት ወራት አፈጻጸሙን በተመለከተ ለመረዳት እንደተቻለው ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ነው፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ ተመላሽ ብድር አሰባስቧል፡፡ ይህ የብድር አሰባሰብ በባንኩ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ስለመሆኑ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች 5.2 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጠ ሲሆን፣ ይህ በ2011 የሒሳብ ዓመት በሙሉ ዓመቱ ለብድር ከዋለው ገንዘብ ጋር ተቃራኒ በመሆኑ በሒሳብ ዓመቱ የተሻለ የብድር አቅርቦት እንደነበረው አመላክቷል፡፡

ከዚህም ሌላ ወጋገን ባንክ የተቀማጭን ገንዘብ መጠኑን 27.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደቻለ ተጠቁሟል፡፡ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ ትርፍ ከ300 ሚሊዮን ብር ላይ ዝቅ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት የመጀመርያ ግማሽ ዓመት የትርፍ ምጣኔውም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በሦስት በመቶ አድርጎ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱም ጠቁሟል፡፡ የግማሽ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ 176.9 ሚሊዮን ዶላር መሆኑም ተገልጿል፡፡

ወጋገን ባንክ አክሲዮን ማኅበር ከ23 ዓመታት በፊት፣ 60 ሚሊዮን ብር የተፈረመ መነሻ ካፒታልና በ30 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ የተከፈለ ካፒታሉ ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ጠቅላላ ካፒታሉም (መጠባበቂያውን ጨምሮ) 4.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ባንኩ አስታውቋል፡፡ ባንኩ በ2011 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠኑ ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ ማሳየቱ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች