‹‹በየአካባቢው ተሽከርካሪ በቆመበት ተሰረቀ››፣ ‹‹መኪናውን አስቁመው ዘረፉት››፣ ‹‹ሾፌሩን ደብድበው መኪናውን ወሰዱበት››፣ ‹‹መኪናውን ሰርቀው አረዱበት››፣ የመሳሰሉትን የስርቆት ዘዴዎች መስማት ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡
በትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት ላይ የተሰማራው ኃይብሪድ ዲዛይን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ራይድ በሚለው የንግድ ምልክትና ስያሜ ይታወቃል) የዚህ ዘረፋ ሰላባ እንደሆነ የድርጅቱ ባለቤት ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ ይገልጻሉ፡፡
‹‹እስካሁን በደኅንነት ዙሪያ ከተገልጋዩ ምንም የቀረቡ አቤቱታዎች የሉም፣ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በራይድ አሽከርካሪዎች ላይ የደኅንነት ሥጋቶች እያስተዋልን ነው፤›› በማለት፣ ችግር መፍትሔን ይወልዳልና እኛም ለዚህ መፍትሔ ይሆናል ብለን ያሰብነውን ‹‹ዱካ ሁሉ›› የተሰኘ የተሳፋሪ፣ የአሽከርካሪና የመኪና ደኅንነት ማስጠበቂያ መሣሪያ ይዘን ቀርበናል ብለዋል፡፡
ሐሙስ ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ኃይብሪድ ዲዛይንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሆራይዘን ኤክስፕረስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ እንዲሁም ለፋይዳ ብድርና ቁጠባ ተቋም አክሲዮን ማኅበር ‹‹ዱካ ሁሉ›› የተሰኘውን መሣሪያ አገልግሎት ላይ ለማዋል በሸራተን አዲስ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ይህ ዱካ ሁሉ የተሰኘው መሣሪያ ሁለት አገልግሎት እንዳለው የጠቆሙት አቶ ዮናስ አምደጽዮን የቴክኖሎጂው ባለቤት የሆነው ሆራይዘን ኤክስፕረስ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ‹‹የመጀመርያውና ዋነኛው የመኪናንና የአሽከርካሪን ዘረፋ የሚያስቆም ሲሆን፣ በአደጋ ወቅትም እንዲሁ የድረሱልኝ ጥሪ ለተለያዩ የባለድርሻ አካላት (ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ለራይድ የኦፕሬሽን ማዕከል) ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የመኪና ባለንብረቶች ለቅጥረኛ ወይም ለተከራይ ያለ ሥጋት መኪናቸውን እንዲሰጡ ያስችላቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
መኪናው ላይ በሚገጠም የድረሱልኝ መጥሪያ (Panic Button)፣ የአሽከርካሪ ስልክ ላይ በሚጫን የሞባይል መተግበሪያ፣ እንዲሁም በጥሪ ማዕከል አማካይነት በዘረፋ ወይም በአደጋ ወቅት አሽከርካሪው መረጃ ወደሚመለከታቸው አካላት መላክ እንደሚችል አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የዱካ ሁሉ›› ሲስተምም ይህንን የመጣውን ጥቆማ በተመሳሳይ ሰዓት ይበትናል፡፡ በዚህም መሠረት የመኪናው ክላክስ ያለማቋረጥ ስለሚጮህ በአካባቢው የሚገኙ ለኅብረተሰቡ ክፍሎች ይጠቁማል፣ በአካባቢው የሚገኙ የራይድ አሽከርካሪዎች ችግር ደረሰበትን መኪና በካርታ ላይ ተከታትለው እንዲይዙት አቅጣጫ መጠቆሚያ ይደርሳቸዋል፣ ወደ ራይድ የጥሪ ማዕከል የሚመጡትን ጥቆማዎች ባወጣው መሥፈርት መሠረት ፈትሾ ለፀጥታ አካላት ያስተላልፋል፣ የፀጥታ አካላትም የተሰጣቸውን የተጣራ ጥቆማ በመቀበል እንቅስቃሴ ይጀምራሉ፡፡
የቁጥጥር መሣሪያውን በተመለከተም አቶ ዮናስ እንደገለጹት፣ የመኪና ጉዞ ክትትል፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ጠቋሚ፣ የነዳጅና የመኪና እድሳት ጊዜ መከታተያ፣ የሥራ ክልል መገደቢያ፣ እንዲሁም ኮረኮንች ላይ የመኪና መናጥ ጠቋሚን መሣሪያው አኳቷል፡፡
ይህንን አገልግሎት ለመስጠት የአጠቃላይ ወጪውን 40 በመቶ ወይም ከ2.6 ሚሊዮን ብር በላይ ራይድ መሸፈኑ የገለጹት የድርጅቱ ባለቤት ወ/ሪት ሳምራዊት፣ የጠቅላላ ምርቱን ቅድመ ክፍያ ለፋይዳ የተባለ ብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲሸፍን አሠራር መንደፋቸውንም አክለዋል፡፡
አቶ አበበ ደሳለኝ የለፋይዳ ብድርና ቁጠባ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጹት፣ ለማስገጠሚያ አንድ መኪና 6,500 ብር የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ሙሉ ወጪ መክፈል የማይችሉ አሽከርካሪዎች በስድስት ወራት የሚከፈል ብድር ከለፋይዳ ያገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተሽከርካሪ እድሳት በሚያደርጉ ወቅትም የብድር አገልግሎት እንደሚያመቻቹላቸው ገልጸዋል፡፡
በሆራይዘን ኤክስፕረስ የቴክኒክ ኦፊሰር አቶ ሶፎንያስ እንቢበል በበኩላቸው፣ የመኪናው ሞተር ቢጠፋም ባይጠፋም መኪኖቹ በተገጠመላቸው መሣሪያ መሠረት ዳታዎችን ይልካሉ ያሉ ሲሆን፣ ጥቃት ለማድረስ የመጣው አካል ፊት ለፊት ያለውን የሚገጠመውን የድረሱልኝ መጥሪያ ቢነቅለውስ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ ‹‹እሱ ቢነቀል እንኳን በሞተር ውስጥ የሚገጠም በቀላሉ የማይፈታ ሌላ መሣሪያ ስለሚኖር አንደኛው መሣሪያ በሚነቀልበት ጊዜ ሌላኛው መሣሪያ ስለሚያውቀው በቀጥታ መረጃውን መላክ ይጀምራል፡፡ በጂፒኤስ አማካይነት ቶሎ ማግኘት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ የአከፋፈል ሁኔታውን በተመለከተ ለሌሎች ድርጅቶች አገልግሎቱን በመስጠት በወር 650 ብር እንደሚያስከፍሉ ገልጸው፣ ከራይድ ጋር ግን በ350 ብር መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡
የትግበራ ቀጠሮ ረድፍ ከሚቀጥሉት ሳምንታት ጀምሮ እንደሚጀመርና ከሁለት ወራት በኋላ በተያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት አባላት የሚፈልገውን ፎርም እየሞሉ ማስገጠም እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡