Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክለዜጎች ነፃነትና ደኅንነት የሕግ የበላይነትን ማስፈን

ለዜጎች ነፃነትና ደኅንነት የሕግ የበላይነትን ማስፈን

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የሕግ የበላይነት ዓለም አቀፋዊ ዕሴት ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያዩ ሰነዶችና ውሳኔዎቹ ላይ የሰብዓዊ መብት፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ ሁሉን አቀፍና የማይነጣጠሉ ቁልፍ ዕሴቶችና መሠረታዊ ዕሳቤዎች እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጸው እናገኛለን፡፡

ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ መግቢያ ላይ ለሰብዓዊ መብት መከበርና መጠበቅ መነሻ የሚሆኑትን የሞራል መሠረቶችን ከዘረዘረ በኋላ የሰብዓዊ መብት የሚጠበቀው በሕግ የበላይነት መሆኑን በግልጽ አስፍሯል፡፡ አኅጉራዊዎቹ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት፣ እንዲሁም የየአገሮቹ ሕገ መንግሥቶች የሰብዓዊ መብቶችን ዕውቅናና ጥበቃ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያቶች ሲያስቀምጡ ከሕግ የበላይነት ጋር አያይዘውታል ወይም የሞራል ምርኩዝ አድርገውታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሕግ የበላይነት ዓብይ ዓላማው ፍትሕ ማስፈን ነው፡፡ በመንበረ ሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ውሳኔያቸው ራሳቸውን ለመጥቀሚያ እንዳያደርጉትም መድኅን በመሆን ያገለግላል፡፡ በመሆኑም ሊሰፍን የሚገባው “Imperium legume/ The empire of laws and not of men” ነው ይላል ጀምስ ሐሪንግተን የተባለ ሊቅ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በጻፈው ድርሳኑ፡፡ የሕግ እንጂ የሰው ኢምፓየር (ንጉሠ ነገሥት እንደማለት) መኖር አስፈላጊነትን ለመጠየቅ የተጠቀመበት አገላለጽ ነው፡፡

 በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥቱን ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለማፋጠን እንዲሁም በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት›› ሲባል በተወካዮቻቸው ያጸደቁት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እንዲሁም ሕግ ተርጓሚው የመንግሥት አካላት በሕግ መሠረት ብቻ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውና ከሕግ በታች መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡

አስፈጻሚው አካል፣ በሕግ አውጪ አካል በሚወጡ ሕግጋት አማካይነት የተለያዩ መንግሥታዊ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚቋቋሙ የአስተዳደር አካላትም የተቋቋሙባቸውን ሕግጋት ሳይተላለፉ መሥራት  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም ቢያንስ ከመርሕ አንፃር የሕግ የበላይነት ተቀብለው መሥራት ግድ ይላቸዋል፡፡

የሕግ የበላይነት፣ በመልካም አስተዳደር መርሕ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ሰዎች መብታቸውን የሚያገኙትም ሆነ የሚያጡት በሕግ መሆንና ልዩነት ሳይደረግ ማንንም የሚገዛው ሕግ ሆኖ ሰዎች ከሕግ በታች በመሆን ለሕግ ተገዥ ሲሆኑ የሕግ የበላይነት አለ ማለት ነው፡፡ በሕገ መንግሥት ሥልጣኑ ገደብ ባልተበጀበት ንጉሣዊና አምባገነን መሪዎች ባሉባቸው አገሮች መሪዎቹ ራሳቸው ሕግ ይሆናሉ፡፡ሕጉም የበታቻቸው ይሆናል፡፡ የፈለጉትን ዓላማ ለማሳካት ግን ሕግን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ሕግ ያወጣሉ፣ እሱን ያስፈጽማሉ፡፡ እነሱ ግን ከሕጉ በላይ ስለሆኑ ሕጉ አይመለከታቸውም፡፡ ‹‹ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ›› እንዲሉ፡፡

የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ግን ንጉሡ፣ የበላይ የሚሆነው ሐሪንግተን እንዳለው ሕግ እንጂ ሰው አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው (ንጉሥም ቢሆን) ለሕግ ይገብራል፣ ይገዛል እንጂ ሕግ ለሰው አይገብርም፣ አይገዛም፡፡ የበላይ የሚሆነው ሕግ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ‹‹ንጉሥ›› ሲባል እንደዘመኑ፣ አስተዳደር ይትባሃሉ ሊቀያየር የሚችል ትዕምርታዊ ቃል መሆኑን ነው፡፡ ግለሰብም ብቻ ሳይሆን ቡድንንም ያመለክታል፡፡ በመሆኑም፣ የፖለቲካ ፓርቲ ቁንጮ ላይ ያሉትን ወይም ሌሎች አይነኬ ሹማምንትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቁምነገሩ፣ በሕግ የማይነካ ሰው እንዳይኖር የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነው፡፡

ከላይ ስለሕግ የበላይነት የቀረቡት ሐሳቦች በዋናነት የሥነ ሥርዓት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በርካታ የሕግ ምሁራንም የሚጋሯቸው እነዚሁኑ ሥነ ሥርዓታዊ የሕግ የበላይነት አላባውያንን ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተወሰኑ ምሁራን ደግሞ የሕግ የበላይነት ሲባል ተራ የሥነ ሥርዓት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲንም ያካትታል ይላሉ፡፡ የዓለም ባንክም፣ በየአገሮቹ የሕግ የበላይነት እንዲከበር በሚያደርገው ጥረት የተቀበለው ብያኔ የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲን ያካተተውን ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተጠቀምነው ሁለቱንም ነው፡፡

የሕግ የበላይነት ጥቅል የሆነ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት እንጂ አንድ ነጠላ ሐሳብ አይደለም፡፡ በአንድ አገር ወይም ክልል አሊያም ዞን ወይም ወረዳ ወዘተ የሕግ የበላይነት የተከበረ መሆን ወይም አለመሆኑን አፍን ሞልቶ ለመናገር ብዙ መሥፈርቶችን በመውሰድ፣ ያሉበትን ሁኔታ መገምገም አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የሕግ የበላይነት ይዞታ ናሙናዎችን በመውሰድ በጥቅል ማሳየት ቢቻልም ከክልል ክልል፣ ከዞን ዞን፣ ከወረዳ ወረዳም የሚለያይበት ሁኔታና አጋጣሚም የታወቀ ነው፡፡ በጥልቅና በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ችግሮቹን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ ለአብነት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ዜጎችን ማገት፣ በደቦ ንብረትና የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ማድረስ እየጨመረም የዘወትር ዜናም መሆኑን ቀጥሏል፡፡ የሕግ የበላይነት ሁኔታው በተለይ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እየተባባሰ መምጣቱ ‹‹አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው›› ሐቅ ሆኗል፡፡

ስለ ሕግ የበላይነት ሲነሳ ብዙዎችን ያስማሙ አራት አላባውያን አሉት፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ ዕሴቶችም ይወሰዳሉ፡፡ እነዚህም ፡

. ተጠያቂነት

በመንግሥትም ይሁን በግል ችሎታ በማናቸውም ጉዳይ ላይ ተዋናይ የሆኑ ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት መኖርን ይመለከታል፡፡

. ፍትሐዊ ሕጎች

ግልጽ፣ ለሕዝብ ይፋ የሆኑ፣ በፍጥነት የማይለዋወጡ (የተረጋጉ)፣ ትክክለኛ (ፍትሐዊ)፣ በሁሉም ላይ በወጥነት ሥራ ላይ የሚውሉ፣ መሠረታዊ መብቶችን የሚያስከብሩ መሆናቸው ሌላው መለኪያ ነው፡፡

. ግልጽ መንግሥት

ሕጎች የሚወጡበት፣ የሚተዳደሩበትና ተግባራዊ የሚደረጉበት ሁኔታ ተደራሽ፣ ፍትሐዊና ውጤታማነት ይመለከታል፡፡

. ተደራሽና ገለልተኛ አለመግባባትን የመፍቻ ዘዴ

ፍትሕን የሚሰጡ አካላት በጊዜውና በብቃት፣ በጎ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ሰዎች (ባለሙያዎች) ያሉት፣ ተደራሽና በበቂ ቁሳቁስና ሀብት የተደራጀ ሆኖ የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ ሥሪት ነጸብራቅ መሆናቸውን በሚመለከት ለመለካት የተመረጠ መሥፈርት ነው፡፡

ከላይ በአራት ቡድን ተከፋፍለው የቀረቡት ዕሴቶች ወይም የሕግ የበላይነት አላባውያን በራሳቸው ሰፊ ሐሳብን ያየዙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ስለ ሕግ የበላይነት ይዞታ ሲነሳ በእነዚህ ምድቦች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል ማለት ነው፡፡

በተጨማሪም፣ የሕግ የበላይነት ይዞታ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለመለካት ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያገኙ መሥፈርቶችን ያስተዋወቁም ጥቅም ላይ ያዋሉም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ፡፡ የዓለም ባንክን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕግ የበላይነት ይዞታ ምን እንደሚመስል በየዓመቱ የዳሰሳ ጥናት በማከናወን ይፋ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ‘ወርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት’ (World Justice Project) አንዱ ነው፡፡ ይህ ድርጅት የሕግ የበላይነት ይዞታን ለመለካት በስምንት ምድብ የተከፋፈሉ አርባ አራት መሥፈርቶችን ይጠቀማል፡፡  እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡

የመንግሥት (የአስፈጻሚው አካል) ሥልጣን ገደቦች (Constraints of Government Power)

በዚህ ምድብ ሥር ሌሎች ስድስት ንዑስ አመልካቾች የተለዩ ሲሆን እነዚህም የመንግሥት ሥልጣን በሕግ አውጭው፣ የመንግሥት ሥልጣን በዳኝነት አካሉ፣ የመንግሥት ሥልጣን በነፃና ገለልተኛ የኦዲት አሠራር ቁጥጥር በማድረግ የተገደበ መሆኑ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋዊ ያልሆኑ ተግባራት ሲፈጽሙ ዕርምጃ መወሰዱ፣ የመንግሥት ሥልጣናት መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ክትትል (ቁጥጥር) መደረጉ፣ ከአንድ (ፓርቲ) መንግሥትዊ ሥልጣን ወደ ሌላ መንግሥት (ፓርቲ) ሥልጣን የሚተላለፈው ሕጋዊ በሆነ መንገድ መሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡

የሙስና አለመኖር (Absence of Corruption)

በዚህ ጥቅል አመላካች ሥር ደግሞ አራት ጠቋሚዎች ያሉ ሲሆን እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡ በአስፈጻሚው አካል ውስጥ ያሉ ሹመኞች፣ ዳኞች፣ ፖሊስና መካላከያ ሠራዊቱ እንዲሁም ሕግ አውጭው (የምክር ቤት አባላት) ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው ማዋል ወይም አለማዋላቸውን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

  1. የመንግሥት ለዜጎችና ለሌሎች አካላት ክፍት መሆን (Open Government)

በዚህ ዘርፍም ሦስት አመልካቾች ተደልድለዋል፡፡ እነሱም መረጃ ማግኘት መቻል፣ ሰላማዊ የሕዝብ ተሳትፎ መኖርና ቅሬታ የማቅረቢያ ሥርዓት መኖር ናቸው፡፡

  1. መሠረታዊ መብቶች (Fundamental Rights)

ስምንት መለኪያዎችን በመጠቀም ነው የመሠረታዊ መብቶችን ይዞታ ለማመልከት የተሞከረው፡፡ እነዚህም በእኩል መስተናገድና አድልኦ አለመኖር፣ በሕይወት ለመኖር መብትና ለአካላዊ ደኅንነት መንግሥት ተገቢ ጥበቃ ማድረግ፣ በሕግ መሠረት ብቻ መሥራት (Due Process of Law)  እና የተከሳሾችን መብት ማክበር፣የአመለካከትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በአግባቡ መከበር፣ የእምነትና የሃይማኖት ነፃነት በአግባቡ መከበር፣ የግላዊነት መብትን (Privacy Right) መንግሥት በዘፈቀደ ጣልቃ በመግባት አለመጣስ፣ የመሰብሰብና የመደረጃት ነፃነት የተረጋገጠ መሆንና መሠረታዊ የመሥራት መብት (Labour Right) የተከበረ መሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡

  1. ሥርዓታዊነትና ደኅንነት (Order and Security)

ይህ ጥቅል መለኪያ ሦስት አመላካቾችን ይጠቀማል፡፡ መንግሥት የወንጀል ድርጊትን በአግባቡ የመቆጣጠር ችሎታ፣ የእርስ በርስ ግጭትና ሰላም መደፍረስን መከላከልና ማስወገድ፣ እንዲሁም ሰዎች የግል ቅሬታንና ቅያሜን በኃይል የመፍታት (የማስወገድ) አዝማሚያና አካሄድን መምረጥ ወይም ያለመምረጥ አዝማሚያ የሚሉት ናቸው፡፡

  1. የሕግ ማስከበር (Regulatory Enforcement)

የመንግሥት ሕግ የማስከበር ፍላጎትና አቅም ለሕግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን ለማመልከት አምስት ጠቋሚዎችን ጥቅም ላይ ያውላሉ፡፡ እነዚህም የመንግሥት ደንብና መመርያዎች በአግባቡ መተግበር፣ የመንግሥት ደንብና መመርያዎች ያለምንም ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ ሥራ ላይ መዋል፣ አስተዳደራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቱ ያለ አጥጋቢ ምክንያት አለመዘግየት፣ በአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥም በሕግ መሠረት መሥራት (Due Process of Law) መከበር፣ እንዲሁም መንግሥት የሕግ ሥርዓቱን ተከትሎና በቂ ካሳ ከፍሎ ብቻ የግል ንብረት የሚወሰድ መሆን ወይም አለመሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡

  1. የፍትሐ ብሔር የፍትሕ አስተዳደር (Civil Justice)

የፍትሐ ብሔር የፍትሕ አስተዳደሩ ለሕዝብ ተደራሽና አቅምንም ያገናዘበ መሆን፣ አድልኦ አለመኖሩ፣ ከሙስና መጽዳቱ፣ ተገቢ ካልሆነ የመንግሥት ተፅዕኖ መላቀቁ፣ ፍትሕ አሰጣጡ ያለ አጥጋቢ ምክንያት አለመዘግየቱ፣ የፍትሕ አስተዳደሩ እንደ ሕጉ በአግባቡ መፈጸሙ፣ አማራጭ የፍትሕ መስጫ ተቋማት (የግጭት መፍቻ ዘዴዎች) ተደራሽ፣ ገለልተኛና ውጤታማነት፣ የሚሉት ሰባት አመላካቾች ናቸው የፍትሐ ብሔር የፍትሕ አስተዳደሩን ይዞታ ለማሳየት ጥቅም ላይ የዋሉት፡፡

  1. የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር (Criminal Justice)

የወንጀል ፍትሕ አስተዳሩን በሚመለከት ደግሞ ሰባት ጠቋሚዎች ተካትተዋል፡፡ እነሱም የወንጀል ምርመራ ሥርዓቱ ውጤታማነት፣ የወንጀል ጉዳዮች የሚዳኙበት ሁኔታ ቅልጥፍናና ብቁነት፣ የማረሚያ ሥርዓቱ የወንጀለኞችን ባሕርይ ከመለወጥ አንፃር ውጤታማነት፣ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ገለልተኛ መሆን፣ ከሙስና መጽዳቱ፣ተገቢ ካልሆነ የመንግሥት ተፅዕኖ መላቀቁ፣ እንዲሁም ሕግን መሠረት አድርጎ መሠራቱና የተከሳሾች መብት መከበራቸው የሚሉት ናቸው፡፡ 

ከላይ ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ስምንት ድረስ የተዘረዘሩት፣ ከሕግ የበላይነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን መሥፈርቶች በመውሰድ በኢትዮጵያ ያለውን የሕግ የበላይነት ይዞታ ለመረዳት ያግዛል፡፡ በአንድ በኩል የሕግ የበላይነት ሲባል ምን ምን ጉዳዮችን እንደሚያካትት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በጥቅል የሕግ የበላይነት ተከብሯል ወይም አልተከበረም የሚል መደምደሚያ ያሉትን ችግሮች አንጥሮ ለማውጣትና መፍትሔ ለማበጀት ፋይዳው ዝቅተኛ ስለሆነ ከላይ በቀረበው አኳኋን ነጣጥሎ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ 

ከዚህ ባለፈም በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የሕግ ማዕቀፍና ተቋማት መኖር፣ ሕጉን ብቻ አክብሮ፣ ለሕግ ገብሮ (ከሕግ በታች ሆኖ) መሥራት ወይም እንደ ሕግ መፈጸምን ስለሚጠይቅ ሕግና ተቋማት መኖራቸው አንድ ነገር ሆኖ የሚፈጸሙበት ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ይጠይቃል፡፡

ከላይ የቀረቡትን መሥፈርቶች በመለኪያነት በመውሰድ፣ ወርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት በየዓመቱ ባከናወናቸው ጥናቶች በሕግ የበላይነት የኢትዮጵያንም ደረጃ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በ2018/2019 አገሮች የሕግ የበላይነት ይዞታቸው ምን እንደሚመስል መረጃ በሰጠበት ዘገባው በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን ገደብ ለመኖሩ 0.33 አግኝታለች፡፡  የሙስና አለመኖር 0.46፣ እኩል አገልግሎት ማግኘትና አድልኦ አለመኖር 0.34 አግኝታለች፡፡ የመንግሥት ግልጽነት (Open government) በተመለከተ ደግሞ 0.28 ነው፡፡ መሠረታዊ መብቶች መከበርን በሚመለከት ደግሞ 0.29 አግኝታለች፡፡ ሥርዓታዊነትና ደኅንነት መከበር 0.64፣ የሕግ ማስከበር ረገድ 0.36፣የፍትሐ ብሔር ፍትሕ አሰጣጥ 0.41፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ደግሞ 0.33 ነው፡፡ በድምር ውጤት ደረጃዋ 0.39 ሲሆን 118 ከ126 አገሮች ሆናለች፡፡

ከላይ በቀረቡት አኃዞች ትምህርቱ ብዙ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ይዞታ ሰላሳ ሦስት ከመቶ ብቻ ማግኘት ወደ ከሕግ የበላይነት ይልቅ ወደ ‹‹የሕግ የበታችነት›› የቀረበ ነው፡፡

የሕግ የበላይነትና የሰላም ቁርኝት

ሰላምንና የሕግ የበላይነት እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ብሎም ሰላምን ለማስፈንና ዘለቄታ እንዲኖረው የሕግ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ሰላም በታጣበት ሰብዓዊ መብት አይከበርም፡፡ ለሰብዓዊ መብት መከበር ሰላም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሰላም ሳይኖር ልማት የመኖሩ ነገር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሰላም ሲታጣ የሚከተለው ጥፋት እንጂ ልማት አይሆንም፡፡ ሰላም በሌለበት ልማት በነጠፈበት ሁኔታ ዴሞክራሲም የመኖር ዕድሏ መንማና ነው፡፡ ሰላም በራቀበት ሁኔታ የሚኖር ልማት የጥቂቶችን ኪስ ብቻ ከማድለብ የሚዘል አይሆንም፡፡

ብዙኃኑ በሰላም ዕጦት እየተሰቃየ ጥቂቶች ግጭት የሀብት ምንጫቸው በሚሆንበት ጊዜ ይዋል ይደር እንጂ አህያ የጅብ ናት እንዲሉ በግጭት ሀብታም የሆኑ ሰዎች ንብረታቸውም መልሶ በአመጽ ብዙኃኑ ይቀራመታቸዋል ወይም በሌሎች ሕጋዊ ዘዴዎች መንግሥት መውረሱ አይቀርም፡፡ ያው ዞሮ ዞሮ ከጥቂቶች ኪስ ይወጣና ለሕዝቡ ይሆናል፡፡ በበርካታ አገሮች የሆነው አስረጂነቱ ይህንን ነው፡፡ ስለሆነም በጊዜያዊነት ሰጥ ለጥ በማድረግ የሚፈጠርን ዝምታ እንደ ሰላም መውሰድ አይቻልም፣ዘለቄታ አይኖረውምና፡፡

የሳንቲያጎው የሰላም ሰብዓዊ መብት መግለጫ፣ ሰላም የሰብዓዊ መብት ቅድመ ሁኔታም ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ሲከበር ደግሞ የሰው ልጅ መብቱን በነፃነት ስለሚያጣጥም ውጤታማ ይሆናልና ነው ይህንኑ መግለጫው ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ ቅድመ ሁኔታም ውጤትም ነው ማለት ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመቋቋሙም ዓቢይ ምክንያት ሰላምን በምድር ላይ ማስፈን ነው፡፡ የድርጅቱ መቋቋሚያ ቻርተር መግቢያው ላይም ሆነ በጥቅሉ ከሌሎች አንቀጾች መረዳት የሚቻለው ሰላም ዓለም አቀፋዊ ዕሴት መሆኑን ነው፡፡ ለዓለም አቀፋዊነቱም ቻርተሩ ዕውቅና ችሮታል፡፡

በሕገ መንግሥቱ በመግቢያው ላይ ማሳካት የሚፈለግውን ግብ ሲገለጽ ዘላቂ ሰላም ማስፈንን እንደ አንዱ አድርጎታል፡፡ በተወሰነ ጊዜ ብቻ ሊሰፍን የሚችልን ፀጥታ፣ ጦርነትና ግጭት አለመኖርን ሳይሆን ዘለቄታዊ እንዲሆንም ጭምር ነው ምኞቱ፡፡

ሰላም በግልጽ ስሙ ተጠቅሶ እንደ መብት ዕውቅናም ጥበቃም በሕገ መንግሥቱ አልተሰጠውም፡፡ ይሁን እንጂ በራሱ በሕገ መንግሥቱም ይሁን በሌሎች ዝርዝር ሕጎች ውስጥ ሰላም የሚፈጠርበትንም የሚጠበቅበትንም ሥርዓት አብጅቷል ማለት ይቻላል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በጥቅል አገላለጽ በአገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ዋስትና ያለው ሰላም ማረጋገጥ እንደ አንድ ማሳካት ስለሚፈልገው ራዕይ በመግቢያው ላይ አስቀምጧል፡፡ የሰላም መስፈን በተራው ደግሞ (እንደ ነገሩ ሁኔታ በተገላቢጦሹም) ዋስትና ያለው የፀና ዴሞክራሲ ለመገንባት መሠረት እንደሆነ ስለሚታወቅ ይህንን ራሱን አስችሎ ሕገ መንግሥታዊ ራዕይ አድርጎታል፡፡

ሰላምም ለማስፈን ዋስትና ያለው የፀና ዴሞክራሲም ለመገንባት ዜጎችም ሆኑ የተለያዩ ቡድኖች እርስ በራሳቸው ሊኖራቸው የሚችለው ግንኙነትና መስተጋብር እንዴት መሆን እንዳለበት መስማማት ስለሚጠበቅባቸው በራሳቸው ወይም በወኪሎቻቸው አማካይነት በሚወጣ ሕግ ሥርዓት ይዘረጋሉ፡፡

የዚህ ሥርዓት ተከብሮ መኖር ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ የሕግ የበላይነት (rule of law) መከበርና በሕግ መሠረት (due process of law) ሁሉን ነገር ከመፈጸም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር ጋር በተያያዘ የወንጀል ሕግ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በጥቅሉ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማ፣ ቀልጣፋ እንዲሁም ፍትሐዊ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

ፍትሐዊነቱ ሲዛነፍ፣ ውጤት ከራቀው፣ ቅልጥፍና ሲጎድለው ተመልሶ ፍትሕ ይጠፋል፣ ርትአዊነት ይጎድላል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሰላም ይታወካል፡፡ በዜጎች መካከል መጠራጠርና ፍርሃት (fear) ይነግሳል፣ መጠቃቃት ወይም ነውጥ (violence) መርሕ እየሆነ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ፍርሃትና ነውጥ ሲጨምር ሰላም ይቀንሳል፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎች (ማንኛውም ሰውም) የተረጋጋ፣ የታወቀና የሚገመት፣ ፀጥታ የሰፈነበት ሕይወት መምራት ያዳግታቸዋል፡፡

በፍርሃት፣ በመጠቃቃትና በነውጥ የተናጠ ማኅበረሰብን በእነዚህ አሉታዊ ባሕርያት እንዲላቀቅ ቢያንስ ሁለት ዓይነት ዘዴዎችን ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡

 አንዱ፣ ግለሰቦችም ይሁኑ ማኅበረሰቡ ከፍርሃቱ፣ ከመጠቃቃትና ከነውጥ ስሜት እንዲላቀቅ፣ በጎ አመለካከት እንዲኖረው ማድረግ ዕርቅና ትብብር መተማመን ወዘተ እንዲፈጥር የሚደረጉ የእርቅና ስምምነት ተግባራት ማከናወንን ይመለከታል፡፡

ሁለተኛው፣ ደግሞ ፍትሐዊ ሕግጋትን በማውጣት በጥብቅ እንዲተገበሩ በማድረግ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ሰላምን የሚነሱ አሠራሮች እንዲወገዱ፣ ሰላምን ለማስፈን ምቹ መደላድሎችን በመዘርጋት መጠበቅን ይመለከታል፡፡

 የመጀመሪያውን በዋናነት የሲቪክ ማኅበራት (civil societies)፣ ሁለተኛው ደግሞ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡

ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ (Global Peace Index) የሚባለው ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋም እ.ኤ.አ የ2018ን የአገሮች የሰላም ሁኔታ በርካታ መለኪያዎችን በመጠቀም ለክቷል፡፡ ደረጃም አውጥቷል፡፡ በጥቅሉ የሰላምን ሁኔታ ለመለካት ልኬት አሰጣጡም እንደሚከተለው ነው፡፡ ከ1.0 ጀምሮ ከ2.0 በታች ያሉት ጥሩ በሚባል ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ከ2.0 እስከ 3.0 ደግሞ ዝቅተኛ በማለት ሲያስቀምጠው ከ3.0 እስከ ከ4.0 ደግሞ በጣም ዝቅተኛ የሚል ደረጃ ይዘዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ፣ አገሮች ያሉበትን የውስጣዊም ይሁን የዓለም አቀፋዊ ግጭት ወይም ጦርነት ውስጥን መሆንን በሚመለከት ኢትዮጵያ 2.695 አግኝታለች፡፡ ይኼ ዝቅተኛ ውስጥ ለዚያውም ጥግ ላይ የደረሰ ነጥብ ነው፡፡

ማኅበረሰባዊ ደኅንነትና ፀጥታ ሁኔታን 2.909 ያገኘች ሲሆን፣ ይህም ያው በዝቅተኝነት የመጨረሻው ጠገግ ላይ መሆኗን ነው የሚሳየው፡፡

 የመጨረሻው ምድብ በግጭት ምክንያት የደረሰባት የኢኮኖሚ ተፅዕኖ 19,094,100,000 ዶላር፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ደግሞ 15,225,700,000 ዶላር ሆኖ፣ይህም  ዓመታዊ የግለሰብ ገቢ ላይ  141.6 ዶላር ጉዳት ሲያደርስ ከጥቅል አገራዊ ገቢው ላይ ዘጠኝ በመቶ እንዲታጣ ምክንያት ሆኗል፡፡

የሕግ የበላይነት የማስከበር ይዞታችን በዚህ መጠን ዝቅ ብሎ የሰላም ሁኔታው የተሻለ ሊሆን አይችልም፡፡ የባለፈው ዓመትም ቢሆን ያው ነው፡፡ አልተሻሻለም፡፡  የሰላም ዕጦትም ይሁን የሕግ የበላይነት አካባበሩ ዝቅተኛ ሲሆን በጥቅል የሰብዓዊ ልማት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፡፡

ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት ብሎም ሰብዓዊ ልማት እርስ በራሳቸው የተቆራኙ ስለሆነ እያንዳንዳቸውን ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ተገቢነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ የመንግሥት መፈጠርም መኖርም የመጀመሪያው ምክንያት የዜጎችን/የሰዎችን ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡ ዜጎች ከነፃነታቸው ላይ ቆርሰው ለመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነት መስጠታቸው ለጋራ ደኅንነታቸው ዋስትና በመሻት ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...