Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከቻይና የመጡ አራት ተማሪዎች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ስለመሆናቸው እየተጣራ ነው

ከቻይና የመጡ አራት ተማሪዎች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ስለመሆናቸው እየተጣራ ነው

ቀን:

በቻይና ኩቤት ግዛት ውሃን (Wuhan) ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አራት ተማሪዎች በኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሚገኘው ልየታ ማዕከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ተጠርጣሪዎቹ በልየታ ማዕከል ክትትል እንዲደረግላቸው ያስፈለገው ከመካከላቸው አንደኛው ተጠርጣሪ ጉንፋን መሰል ምልክት ስለታየበት ነው፡፡

ይህም ሆኖ ግን በአሁኑ ጊዜ የአራቱም ተጠርጣሪዎቹ ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ፣ የላቦራቶሪ ምርመራ ተሠርቶላቸው ለጉንፋን መሰል በሽታ ኔጌቲቭ መሆናቸው እንደተረጋገጠ፣ ይህም ውጤት ለከፍተኛ ምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደተላከ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህም በተጨማሪ ከቻይና ጓንዡ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሁለት ቻይናውያን መንገደኞች በአውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የምርመራ ቦታ ለሁለት ሰዓታት ያህል አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ፣ ቫይረሱ ካሉበት አካባቢ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌላቸውና በሙቀት ልየታ መሣሪያውም የተገኘ ምልክት ስለሌለ፣ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ተገልጾ፣ በመንገደኞቹ ላይ የማጣራት ሥራ የተከናወነው በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ በሰጠው ጥቆማ መሠረት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተገኘው መረጃ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የቫይረሱ መነሻ በሆነው ውሃን ከተማ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ ለማድረግ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ ክትትልና ጥንቃቄ እያደረገ ነው ተብሏል፡፡

እንደ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ (ዶ/ር) ማብራሪያ ከሆነ፣ በውሃን ከተማ የተከሰተውና ኖቭል ኮሮና ቫይረስ 2019 በሚል ስያሜ የሚጠራው ይህ በሽታ፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ አስፈላጊው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ እስካሁንም በተካሄደው እንቅስቃሴ ስለበሽታው መረጃ መስጠትና በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ሥራ መጀመር ይገኝበታል፡፡

የሙቀት ልየታ ሥራ የተጀመረው በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሐሳብ መሠረት ሲሆን፣ በሙቀቱ መለየት ሥራ ላይ እስካሁን ያጋጠመ ችግር እንደሌለና መረጃ የመስጠቱም ተግባር የሚካሄደው በማንኛውም አየር መንገድ በኩል የሚጓዙ መንገደኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በማሰብ እንደሆነ፣ ከዚህም በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ለክልሎችና ለባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራዎች እንዲያከናውኑ የቅድመ ዝግጅት መልዕክት እንዳሠራጩ ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ትስስር የምታደርግ በመሆኑ፣ በሽታውን ሪፖርት ካደረጉት አገሮች ጋርም በአየር መንገዷ አማካይነት በርካታ በረራዎች አሏት፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይና ብቻ በአምስት መዳረሻዎች ማለትም ቤጂንግ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሻንግሃይ፣ ቸንዱና ጓንዡ በረራዎችን ያደርጋል፡፡ በዚህም የተነሳ ቫይረሱ የሚገባባቸው ዕድሎች ሰፊ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

በሽታው ወይም ወረርሽኙ ያለባቸው ሰዎች ድንገት ቢገኙና ተጨማሪ ምርመራና መታየት የሚያስፈልጋቸው ከሆነ፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጊዜያዊ የማቆያ ማዕከል ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ቦታ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሐኪሞች እንደተመደቡ ተገልጿል፡፡

ለረዥም ጊዜ እየታዩ መታከም የሚያስፈልጋቸው በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታልና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን፣ ከኤባ (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡ በሽታው በጠናባቸው ታማሚዎች ላይ ደግሞ እንደ ሳንባ ምች (ኒሞኒያ)፣ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ሕመም የሚያሳይ ሲሆን፣ የኩላሊት ሥራን ማቆም ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ በሽታው ባልበሰሉ ምግቦች፣ በሳልና በማስነጠስ ወቅትና ከታማሚ ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ፣ ባልታጠበ እጅና በመሳሰሉት ይተላለፋል፡፡

በሽታውን ሪፖርት ወደ አደረጉ አገሮች የሚጓዙ መንገደኞት እጅን በሳሙናና በ መታጠብ አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ከታመሙ ሰዎች ወይም ከአካባቢያቸው ጋር ንክኪ አለመፍጠር፣ ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችን ከመመገብ መቆጠብ፣ በሕይወት ካሉም ሆነ ከሞቱ ከቤትና ከዱር እንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሕክምና ተቋማት፣ ከጉዞ ማኅበራት፣ ከአየር መንገድ፣ ከመዳረሻ ቦታዎች ወይም ከሌሎች የጤና መረጃ ምንጮች ስለበሽታው በቂ መረጃ ማግኘትና ራሳቸውን ከበሽታው መከላከል እንደሚጠበቅባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ 2019 በሚል ስያሜ የሚጠራው በሽታ ከታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ መከሰቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ በዚሁ በሽታ በቻይና 106 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ሌሎች 400 ያህል ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተጠቅተው በከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ከ5,700 የሚበልጡ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ በበሽታው ተይዘው የነበሩ 51 ሰዎች በተደረገላቸው ሕክምና አገግመው ተነስተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከቻይና ውጪ ባሉ እንደ አሜሪካ፣ ታይላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ ከቻይና በተነሱ መንገደኞች አማካይነት መሠራጨቱን ዘገባዎች ጠቁመው፣ በእነዚህም የሞተ ሰው ባይኖርም እንኳን 44 የሚደርሱ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...