Wednesday, June 7, 2023

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ራስ ምታት የሆነው የሰንደቅ ዓላማ ውዝግብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሰንደቅ ዓላማ በበርካታ የዓለማችን አገሮች ከስሜትና ከማንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ምልክት ነው፡፡ በሁሉም አገሮች ሰንደቅ ዓላማ ከአገር ፍቅርና ከጀግንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን፣ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ከአገር ክብርና ከድል ጋርም በእጅጉ የተገናኘ ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማ አንድ አገር ማንነቱን በዓለም መድረክ የሚያሳይበትና የሚወክልበት፣ የተለየ ቀለምና ዓርማ እንዲሁም አደራደር ያለው ሥሪት ሲሆን፣ ምልክትነቱና ወካይነቱ ግን ከጨርቅ እጅግ ከፍ ያለና የሰፋ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህም ይመስላል አገሮች በጦር ዓውድማ ከተዋደቁ በኋላ ድል ሲገኝ፣ ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ ማውለብለብን ቀዳሚ ተግባር የሚያደርጉት፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ወካይነት ግን በታሪክና በአጋጣሚዎች የሚገራና የሚወሰን ሆኖ ሳለ፣ በሁሉም ዘንድ ባይሆንም በአብዛኛው ማኅበረሰብ ተቀባይነት ያለው ሰንደቅ ዓላማ እንዲኖር ማድረግ፣ በተለይ በቅኝ ግዛት እንዳለፉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የነፃነት ተምሳሌትነት ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያም ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ የነበሯቸው ሰንደቅ ዓላማዎች የጎላ ለውጥ ሳይደረግባቸው ለረዥም ጊዜ በጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ረዥም የአስተዳደርና የመንግሥት ሥርዓት ልምድ ባላቸው አገሮች ሰንደቅ ዓላማ በተለያዩ ሥርዓቶችና ተያያዥ ሁነቶች የተቃኘ ሲሆን፣ አንፃራዊ የሆነ ረዥም ዕድሜ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ሲኖራቸው ይታያል፡፡ ምንም እንኳን እያንዳንዱ ሥርዓት የየራሱን አሻራ ያሳረፈበት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሠረታዊ የሚባል የቀለምና የአቀማመጥ ልዩነት ሳይታይበት ለረዥም ጊዜ የቆየ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡

ኢትዮጵያ አውሮፓውያን ለቅኝ ግዛት ወረራ ባደረጉበት ወቅትም ወራሪዎችን በብቃት መመከትና ድል መንሳት እንደሚቻል ለጥቁሮች ምሳሌ በመሆኗ ሳቢያም፣ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ሲወጡ በተለያዩ ሥሪቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንደቀዱ በርካታ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ስለዚህም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ሆኖ በወቅቱ የነበረው ሰንደቅ በጥቅም ላይ ውሏል፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለሞች ላይ የአንበሳ ምሥልና መስቀል ተደርጎበት ሲያገለግል የነበረው ባንዲራ (ሰንደቅ ዓላማ)፣ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ዓርማው ተቀይሮ በጥቅም ላይ ሲውል ነበር፡፡ በተመሳሳይ ምንም ዓርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማው ያለ ምንም ክልከላ ሲውለበለብም ነበር፡፡

ከ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢትጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በ1987 ዓ.ም. ሥራ ላይ ባዋለው ሕገ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባለ ሦስት ቀለም አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሆኖ በቢጫው ቀለም ላይ በሰማያዊ መደብ በወርቃማ/ቢጫ ቀለም የተሳለ ኮከብ እንደሚኖር በመደንገግ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው አድርጓል፡፡

በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሦስት መሠረት በ2001 ዓ.ም. የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ከዚህ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ ያሉ ሰንደቆችን ማውለብለብ የከለከለ ሲሆን፣ በአዋጅ የ2006 ዓ.ም. ማሻሻያ ደግሞ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በጥቅምት ወር የመጀመርያው ሰኞ እንዲከበር ደንግጓል፡፡ የአዋጁ ድንጋጌዎች ሲጣሱም እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣትን የሚያስከትል ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል፡፡ ሆኖም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለይ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በሚፈጸሙበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስርቲያን ልሙጡንና ምንም ዓርማ የሌለበትን ስትጠቀም ይስተዋላል፡፡

በተለይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ የተለያዩ ሐሳቦች በተለያዩ መንገዶች ሲንፃባረቁ የተስተዋለ ሲሆን፣ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችም ግዘፍ አግኝተው የሚስተዋሉበት ጊዜ መሆኑን በርካታ ፖለቲከኞችና ታዛቢዎች ይስማማሉ፡፡ በዚህ ወቅት በተለያዩ አገራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክስተቶች ላይ እንደ ተሳታፊዎች ስብጥር ይወክለናል የሚሏቸውን የተለያዩ ዓርማዎችና ሰንደቅ ዓላማዎች ሲያውለበልቡ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከዚህ ባለፈም የእነዚህን ዓርማዎችና ሰንደቆች ቀለሞች በተለያዩ ቋሚ ንብረቶች ላይ መቀባትም በተደጋጋሚ ይታያል፡፡

እነዚህ የተለያየ አመለካከቶችን ተከትለው በዓርማዎችና በሰንደቆች የሚንፀባረቁ ሐሳቦች ግን ሐሳብ በማንፀባረቅ ብቻ የሚያበቁ ሳይሆኑ፣ አንዴንደም ወደ ጥፋት የሚመሩ ግጭቶችንና ብጥብጦችን ሲያስከትሉ ማየትም ከዓርማዎችና ከምልክቶቹ እኩል በዝቶ የሚታይ የሁነቶች አካል ነው፡፡

ይኼ ልምድ በኢትዮጵያ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በውጭ አገሮች የሚታይ፣ የፖለቲካ አመለካከትንና ለኢሕአዴግ ያላቸውን ጥላቻ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚገልጹበት እንደሆነም፣ ይኼንን ጉዳይ በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በመመልከት ጥናት የሠሩት ጎሹ ወልዴና ፒተር ካስትሮ የተባሉ ተመራማሪዎች የሰንደቅ ዓላማ ፖለቲካ በኢትጵያና በኢትዮ አሜሪካዊ ዳያስፖራ በሚለው ጥናታቸው ውስጥ ጽፈዋል፡፡

አጥኚዎቹ በዚህ ጽሑፋቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት በሰንደቅ ዓላማው ላይ ባለው ፖለቲካ እንደሚንፀባረቅ በመጠቆም፣ በአገሪቱ ያለውን የግጭቶች ሁኔታ ተከትሎም በዳያስፖራው መካከል ክፍፍል የሚፈጥርበትም ጊዜ እንዳለ አመላክተዋል፡፡

ስለዚህም በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ያለው ፖለቲካ ሊጤን የሚገባው ነው በማለት፣ ሰንደቅ ዓላማ አንድነትን የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን ልዩነቶችን ሊያመላክት ግፋ ሲልም ሊያሰፋ የሚችል ነው ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በማንነታችን ተጨቁነናል፣ እኛን አይወክልም በሚሉና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት የአገር ዓርማ ነው በሚሉ መካከል ልዩነት ያለበት እንደሆነ በመጠቆም፣ ‹‹ይኼ የአጠቃላይ አገራዊ መግባባትና የጋራ ራዕይ አለመኖሩ ማሳያ ነው፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ልዩነቶች ምንም ሆኑ ምን ወደ ግጭት የሚያመሩና ለሰው ሕይወት መጥፋት ሰበብ ሊሆኑ አይገባም ባይ ናቸው፡፡

ፓርቲያቸው በፕሮግራሙ ላይ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለውን ሰንደቅ እንደሚቀበል በግልጽ ተቀምጧል የሚሉት አቶ ናትናኤል፣ ‹‹ነገር ግን በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚያርፍ ዓርማ ያስፈልጋል ከተባለ በሕዝብ ምርጫ የሚደረግ መሆን እንዳለበት እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ባለው ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለውን ዓርማ ሕዝቡ እንዲቀበለው የተደረገበት መንገድ፣ ብዙዎች አይገልጸንም ሲሉ የሚጨቆኑበትና የሚሰደዱበት ስለነበር የተቃውሞ ምንጭ ሆኗል ሲሉ የሚያስረዱት አቶ ናትናኤል፣ ይኼ የሚያሳየው ዓርማ መደረግ ካለበት በመግባባት ላይ ተመሥርቶ ነው ይላሉ፡፡

ነገር ግን ከአገራዊ ባንዲራ/ሰንደቅ ዓላማ ውጪ ማንም ሰው ይወክለኛል ብሎ የሚያስበውን የመጠቀም መብት ሊኖረው ይገባል በማለት፣ ይኼ ግን የአገሪቱን ሰንደቅ ክብርና የሌላውን መብት እስካልነካ ድረስ ነው መሆን ያለበት ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በዚህ ሳቢያም ምንም ዓይነት ግጭት መፈጠር የለበትም፣ ነገር ግን ግጭቶች ሲከሰቱ ተመልክተናል፤›› የሚሉት አቶ ናትናኤል፣ ‹‹ይህ የሆነው ግን ልዩነትን በውይይት የመፍታት ልምድ ስለሌለ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ስለዚህ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የሌሎችን መብት የሚነኩ መሆን እንደሌለባቸው፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ማለት አግባብ አይደለም በማለትም ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማው ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝበት አግባብ እንዳለ በመጠቆም፣ በአገሪቱ የጋራ የሆነ መሆን እንዳለበትና አንዱ እኔ በባለቤትነት መያዝ አለብኝ የሚለው መሆን የለበትም ባይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ዜጎች ይወክለኛል የሚሉትን ቢጠቀሙ መብታቸው መገደብ የለበትም ሲሉም ያክላሉ፡፡

‹‹ግን እንደ አገር የምንጠቀመው ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ዘውግ ወይም ሃይማኖት ውክልና የሚሰጥና ሌላውን የሚያገል መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም እኩል የሚቀበለው መሆን አለበት፤›› ብለው፣ ‹‹ስለዚህ እንደ ዜጋ ሁላችንም እኩል በመሆናችን እኩል የሚወክለን መሆን አለበት፤›› ይላሉ፡፡

ይኼንን ለመቀየር በቀጣይ አገራዊ ራዕይ የሚታይበት ሕገ መንግሥት ሲሻሻል አብሮ በሚደረግ ውይይት ወቅት፣ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይም የውይይቱ አካል ይሆናል ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይኼንን ማድረግ አገሪቱ ስትረጋጋና ሰላምና ፀጥታ ሲሰፍን፣ እንዲሁም ውይይቱንና ለውጡን የሚያደርገው አካል ትክክለኛ ሕዝባዊ ውክልና ያለው መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ውይይት ከቀጣይ ምርጫ በኋላ ነው መሆን ያለበት ሲሉም ያብራራሉ፡፡

በተመሳሳይ ይኼንን ጉዳይ በሚመለከት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ቶሌራ አደባ፣ የሰንደቅ ዓላማ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ውዝግብ ሲፈጥር መቆየቱን በማመላከት፣ በተለይ ባለፉት ዓመታት ትልቅ ጉዳይ ተደርጎ ችግር ሲፈጥር ታይቷል ይላሉ፡፡

ሰንደቅ ዓላማ በፓርላማ ፀድቆ ለሁሉም እኩል የሚሠራ መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ በመግለጽ፣ በሕግ የተደነገገ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ቢኖርም የኢትዮጵያ ይኼ መሆን አለበት የሚል ፉክክር አለ ሲሉ ምልከታቸውን ያጋራሉ፡፡ አንዱ ባለ ኮከቡን፣ ሌላው ልሙጡን፣ የተቀረው ደግሞ የድርጅት ባንዲራ ይሁን እንደሚል ጠቁመው፣ እያንዳንዱ የፌዴሬሽኑ ክልል ያለውን ሰንደቅ የማይቀበሉ እንኳን በርካታ እንደሆኑ ይጠቁማሉ፡፡

ሆኖም ካለመቀበል አልፎ ግጭቶችን ሲያስከትሉና ጉዳት ሲያደርሱ የሚታዩ ልዩነቶች እንደሆኑ በመጠቆም፣ ይኼም ከግንዛቤ ማነስና ከበስተጀርባ ባሉ የፖለቲካ ዓላማዎች የሚመሩ ናቸው ይላሉ፡፡

‹‹ሰንደቅ ዓላማን እንደ መለያ ነጥብ አድርጎ መውሰድ ልክ አይደለም፡፡ ሕዝብ የፈለገውን ይዞ መውጣት መብቱ ነው፤›› በማለት፣ ለውጥ ካስፈለገም ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያለውና እኩል ይወክለናል የሚባል ሰንደቅ ዓለማ አንዱ ምክንያት፣ መንግሥታት ሲቀያየሩ የሚቀያየር በመሆኑ እንደሆነም አቶ ቶሌራ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ባንዲራ ሕዝቡን የሚወክልና ሕዝቡ የእኔ ነው የሚለው መሆን አለበት፡፡ የሚቀያየር ከሆነ ሕዝቡ ያልተቀበለው በመሆኑ ሊሆን ይችላልና፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

አሁን በተለይ ውዝግብ እየፈጠረ ያለው ባለ ኮከቡና ልሙጡ ሰንደቅ ነው የሚሉት አቶ ቶሌራ፣ ‹‹ልሙጡ የማን ነው?›› ሲሉ በመጠየቅ፣ በዚህ ሁኔታ የአገር ነው ቢባል የሚያገልላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል ይላሉ፡፡

በኦሮሚያ በብዛት አሁን የሚታየው የኦነግ ዓርማ ሕዝቡ በፍላጎቱ ወስዶ እየተጠቀመው ያለ ነው እንጂ፣ የክልሉ ሰንደቅ እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ቶሌራ፣ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ በራሱ ውሳኔ ወስዶታል፡፡ የእኛ ነው የማንልበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ የሕዝብ ሆኗል፡፡ እኛ ግን ውሰዱ አላልንም፡፡ የኦሮሞ ባንዲራ ነው ብለንም አናውቅም፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ግን የኦሮሞ ባንዲራ ይሁን ከተባለ ሕጋዊ ዕውቅና እንደሚያስፈልገውና ቢያንስ በጨፌ መወሰን እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ ይኼ ዓርማ በስፋት ጥቅም ላይ በመዋሉም፣ ኦነግ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ያሉ ውዝግቦችን ለመፍታት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት እንደሚያምኑም ያክላሉ፡፡  

በባንዲራ ዙሪያ ውይይት ቢደረግ ለሕዝብ ግንዛቤና ግጭቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ እንደሚረዳ በመግለጽ፣ መለወጥ ቢኖርበትም በሚመለከተው አካል እንጂ ከሕግ ውጪ መሆን እንደማይገባው ይናገራሉ፡፡

በሰንደቅ ዓላማው ሰበብ የሚፈጠሩ ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱና ሕይወት እየቀጠፉ፣ እንዲሁም ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሁነቶችን እያጨለሙ ሲደጋገሙ የተመለከቱ ባለሙያዎች፣ በርካታ የአፍሪካ አገሮች እንደ መለያ ያደረጉት ቀለም ለኢትዮጵያውያን የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ እንዲያውም ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ያደረጉ የሌላ ጥቁር አገር ዜጎችን ውለታ ለማሰብ ጥቁር ቀለም ቢጨመርበትና አቃፊ እንዲሆን ማድረግ ቢቻል፣ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል ሲሉ የሚከራከሩም አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -