የፋይናንስ ተቋማት በ2012 ግማሽ ዓመት አፈጻጸማቸው ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ብልጫ አስመዝግበዋል፡፡
ከ16ቱ የግል ባንኮች አኃዛዊ መረጃዎች ውስጥ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ጭማሪ አንዱ ሲሆን፣ በግርድፉ ከሚቀርቡ ሪፖርቶች መረዳት እንደተቻለው፣ ተቀማጭ ሒሳባቸው ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በ2011 መጀመርያ ግማሽ ዓመት የተመዘገበው ተቀማጭ ሒሳብ 311.5 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
የብድር መጠናቸውም ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገቡት አጠቃላይ የብድር ክምችት 312 ቢሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ በዓመቱ አጋማሽ ያቀረቡት አዲስ የብድር መጠን 52 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ታውቋል፡፡
ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንደገጠማቸው በሚገልጹበት በዚህ ወቅት ጭማሪ የታየበት የብድር ሥርጭት አስመዝግበዋል፡፡ ወደ ኢኮኖሚው የገባው የገንዘብ መጠን ጭማሪ ከማሳየቱም በላይ የባንኮች እንቅስቃሴ አሁንም ቢሆን በተሻለ አካሄድ እየተጓዘ እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡
ከትርፍ አኳያም የግል ባንኮች የትርፍ ህዳጋቸውን በማሳደግ ውጤታማ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ታክስና ሌሎች ተቀናሽ ሒሳቦች ሳይታሰቡ የሁሉም ባንኮች የትርፍ መጠን ከ9.2 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡
ከ16ቱ የግል ባንኮች መካከል አዋሽ ባንክ በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገበው ግርድፍ ትርፍ 2.04 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ዳሸን ባንክ በበኩሉ 1.16 ቢሊዮን ብር ግርድፍ ትርፍ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ግርድፍ ትርፍ ማስመዝገብ ከቻሉ ባንኮች ውስጥ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ ዘመን ባንክ፣ አንበሳ ባንክና አቢሲኒያ ባንክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ባንኮቹ ከ500 እስከ 900 ሚሊዮን ብር ግርድፍ ትርፍ አስመዝግበዋል፡፡ ይህም በዚህ ዓመት መጨረሻ ከቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ሊያስመዘግቡ የሚችሉ ባንኮች፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩትና በጣት ከሚቆጠሩት ባንኮች የበለጠ ቁጥር ሊመዘገብ እንደሚችል አመላካች ሆኗል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያገኙት የግል ባንኮች፣ አዋሽ ባንክ ዳሸን ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የግማሽ ዓመት አፈጻጸሙን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የ24.6 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደቻለ አስታውቋል፡፡ ዕቅዱ 34.8 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ እንደነበር፣ በውጤቱም የ71 በመቶ አፈጻጸም እንዳስመዘገበ ባንኩ ገልጿል፡፡
የንግድ ባንክ ከግሉ ዘርፍ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት ከ390 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰና የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹ ብዛትም በዓመቱ መጀመርያ ላይ ከነበረው 21.6 ሚሊዮን ግማሽ ዓመቱ ላይ የ1.9 ሚሊዮን አዳዲስ አስቀማጮች ታክለው አጠቃላይ የአስቀማጮች ብዛት ወደ 23.5 ሚሊዮን ሊያድግ መቻሉን ባንኩ ጠቅሷል፡፡ በዚህ ሳቢያም ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ችሏል፡፡
የሞባይልና የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን በማሳደግ፣ በሒሳብ ዓመቱ ስድስት ወራት 1.2 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎችን ለማፍራት በቅቷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢው 3.1 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ ያስታወቀው ንግድ ባንክ፣ ከወጪ ንግድ ዘርፍ 139.4 ሚሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ሐዋላ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ማሰባሰብ በመቻሉና ከብሔራዊ ባንክ 1.2 ቢሊዮን ዶላር በማግኘቱ፣ በጠቅላላው ከ3.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ እንዳስመዘገበ ገልጿል፡፡