Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በታክስ ጉዳይ የተወነጀሉ ነጋዴዎች በከተማ አስተዳደሩ የተነሳላቸው ክስ ሊቋረጥላቸው እንዳልቻለ ገለጹ 

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከታክስ ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው በፍርድ ቤትና በፖሊስ ሲታይላቸው የነበሩ ነጋዴዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ ያስተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ባለመደረጉ ችግር እንደፈጠረባቸው ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ባለሥልጣን አማካይነት ጉዳያቸው ለካቢኔ ቀርቦ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነላቸው ነጋዴዎች፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ መፍትሔ እንዳላገኙ እየገለጹ ነው፡፡ በአስተዳደሩ ውሳኔ መሠረት በፖሊስና በፍርድ ቤት ተይዘው የነበሩ ክሶች እንዲቋረጡላቸው የሚጠይቀው ደብዳቤ ለዓቃቤ ሕግ ቢደርሰውም፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሊሰጥበት ባለመቻሉ ወደ ፍርድ ቤት ለመመላለስ መገደዳቸውን አቤት ባዮች አስታውቀዋል፡፡

በከተማው ካቢኔ መሠረት ለዓቃቤ ሕግ ስም ዝርዝራቸው ከተላኩ ነጋዴዎች መካከል በመጀመርያ ዙር ቁጥራቸው 1,077 የሚሆኑት ክሳቸው እንደሚቋረጥ ተገልጾላቸው በከተማ አስተዳደሩ የምሕረት ውሳኔ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከ3,400 በላይ ነጋዴዎች ግን ተመሳሳይ ዕድል ቢሰጣቸውም ዓቃቤ ሕግ ለጉዳያቸው ምላሽ አለመስጠቱና ክሳቸውም በእንጥልጥል ላይ መቅረቱ አሳስቧቸዋል፡፡

ነጋዴዎቹ መጀመርያውኑ በመንግሥት የቁጥጥር ክፍተትና ደካማ አሠራር ለክስ መዳረጋቸውን በመግለጽና የቀረቡባቸውም ክሶች ቀላል እንደነበሩ በመግለጽ መጉላላታቸውን ተገንዝቦ አስተዳደሩ ያስተላለፈው ውሳኔ ሊፈጸምላቸው እንዳልቻለ ይገልጻሉ፡፡ የ15 ብር ደረሰኝ ባለመቁረጣቸው የተከሰሱ እንደሚገኙበት ተገልጾ፣ እንዲህ ያሉ ክሶች እንዲነሱ የተወሰነው መንግሥትም ነጋዴዎችም የሚያተርፉት ነገር አለመኖሩ ግምት ውስጥ ገብቶ ነው ቢባልም፣ በዓቃቤ ሕግ ዕልባት ሊሰጣቸው አልቻለም ተብሏል፡፡

ይቋረጥ የተባለው ክስ ባለመቋረጡ ለእስር የተዳረጉ እንዳሉ ጭምር ሲገለጽ፣ አንዳንዶችም በፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተጉላሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን ዕልባት ሊሰጥበት ያልቻለው ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ከሆነም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገብተውበት ምላሽ እንዲሰጧቸው ነጋዴዎቹ ተማጽነዋል፡፡  

‹‹በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተደረገ ስብሰባ ክሳችሁ ተቋርጧል ተብለን ነበር፡፡ እስካሁን አለመፈጸሙ ግራ አጋብቶናል፤›› ያሉት ነጋዴዎቹ፣ ጉዳዩ ከዓቃቤ ሕግ በላይ ነው የሚል ጭምጭምታ በመስማታቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለዓቃቤ ሕግ መመርያ እንዲሰጡላቸው በማሰብ አቤት ለማለት ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ጠቁመዋል፡፡

ነጋዴዎቹ በግንባር ቀርበው ለዓቃቤ ሕግ አቤት ማለታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግ በነጋዴዎቹ ላይ የተከፈቱትን ክሶች ለማቋረጥ ፈቃደኛ ቢሆንም፣ ክሶቹን ለማቋረጥ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ባለማየታቸው ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ጉዳያቸውን ለምን እንዳዘገየው ግልጽ እንዳልሆነላቸው አክለዋል፡፡

እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ በተመሠረተባቸው ክስ መሠረት እንዲከፍሉ የተወሰነባቸውን የታክስ መጠን ከእነመቀጫው ከፍለውም ፍርድ ቤት ከመመላለስ ያልተረፉ አሉ፡፡ ይህም ሳያበቃ በአንዳንዶቹ ነጋዴዎች ላይ ብይን እየተሰጠ በመሆኑ ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡

ከተከሰሱት ነጋዴዎች መካከል ንግድ ፈቃዳቸው ያልታደሰላቸው ሲኖሩ፣ ታድሶላቸቸውም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ የተደረጉ በርካቶች በመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ያሳለፈው ውሳኔና የሰጣቸው ምሕረት ተፈጻሚ እንዲደረግላቸው አቤቱታ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡላቸውም እየተማጸኑ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች