Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊጥልቅ ግንዛቤ የሚሻው የሥጋ ደዌ

ጥልቅ ግንዛቤ የሚሻው የሥጋ ደዌ

ቀን:

በኅብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ በኖረ የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ በሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ አድልዎና መገለል ሲደርስ በመቆየቱ ኑሮአቸው ቀላል የሚባል አልሆነም። የተሻለ አመለካከት ማስረፅ የተቻለ ቢሆንም ውጤቱ ሲገመገም ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ላይ ግን ብዙ ይቀራል፡፡

ከስድሳ ስድስት ዓመታት በፊት የዓለም የሥጋ ደዌ ቀን እንዲዘከር ሲወሰን፣ በደዌው ተጠቂዎች ላይ የሚደርሰው አድልዎና መገለል ለማስቀረት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድም ስለበሽታው የሚኖረውን ግንዛቤ በማስፋት ሰብዓዊ መብታቸውንማስጠበቅ ታልሞ ነው።

ዘንድሮ የዓለም ሥጋ ደዌ ቀን ‹‹በዕውቀትና በፍቅር በተመሠረተ ሁለንተናዊ አገልግሎት በመስጠት ከሥጋ ደዌ ነፃ የሆነ ማኅበረሰብ እንፍጠር›› በሚል ርዕስ ከጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀን ይከበራል፡፡  

- Advertisement -

ዓመታዊው ቀኑን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ከፍያለው በቀለ እንደተናገሩት፣ ሥጋ ደዌ በሕክምና የሚድንና በማንኛውም ሰው ላይ ሊደርስ የሚችል ቢሆንም የበሽታውን ሳይንሳዊ እውነታ ባለመረዳት ምክንያት ብዙ ወገኖች በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋም አይሄዱም፡፡ ይህም በጊዜ ሒደት ለከፋ የአካል ጉዳት እንዲጋለጡ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡

 በሥጋ ደዌ ሕመምተኞች ላይ የሚደርሰው አድልኦና መገለል የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ከሚደርስባቸው ውስብስብ የጤና ችግር ባልተናነሰ ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ተሳትፎ እንዲርቁ አድርጓቸዋል፡፡

ነባራዊ ሁኔታው ሲገመገም በበሽታው ዙሪያ ያለው የአመለካከት ደረጃ ርቆ የተራመደ ባለመሆኑ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች የተጋለጡ እንደሆኑ የቦርድ ሰብሳቢው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ነገር ግን የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን ሰብዓዊ መብትና ክብር ጥቅምና ማኅበራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት በትንሹ የሚገመት አለመሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡

የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የሚደርስባቸው ድርብርብ ችግር ተወግዶ እምቅ አቅማቸውን ለኢትዮጵያ ልማት እንዲያውሉና ከሚመጣው ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረውን ጥረት የጋራ በማድረግ አጠናክሮ መቀጠል የሁሉም ኅብረተሰብ ኃላፊነት መሆኑን አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ክትትል ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አመዲን፣ የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም ባንክ በጋራ በ2003 ዓ.ም. ባካሄዱት ጥናት መሠረት በዓለም ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከ18 ሚሊዮን በላይ ወይም ከሕዝቡ መካከል 16.7 በመቶ ያህሉ አካል ጉዳተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነኚህን አካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ ራሱን የቻለ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ፣ አሁን ያለው አደረጃጀት በቂ ነው ተብሎ ሊወሰድ እንደማይቻል፣ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽንን በመቀበል በአዋጅ ቁጥር 676/2002 የሕግ አካሉ አድርጎ እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩም የአካል ጉዳተኞች የአሥር ዓመት የድርጊት መርሐ ግብር ማውጣቱን፣ ይሁን እንጂ መርሐ ግብሩ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚያበቃና በቀጣይ ተገምግሞ ሌላ የድርጊት መርሐ ግብር ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ማኅበራት የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ነገር ግን የሥጋ ደዌ ምን ዓይነት በሽታ እንደሆነ ኅብረተሰቡ ባለመገንዘቡ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ አቶ አሳልፈው ተናግረዋል፡፡ 

ቀደም ባለው ጊዜ አብዛኞቹ የአካል ጉዳተኞች ከኅብረተሰቡ ተለይተው ገለል ባሉ ሥፍራዎች ተሰባስበው ሲኖሩ መስተዋሉ፣ ለዚህም አዲስ አበባ ዘነበ ወርቅ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘውንና ሻሸመኔ ኩየራ ሠፈሮችን መጥቀስ እንደሚቻል፣ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ አሰፋፈር እየተቀየረና ከኅብረተሰቡ ተቀላቅለው እየኖሩ እንደሚገኙ በፖለቲካ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ንቁ ተሳትፎም እያደጉ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም የሥጋ ደዌ ተጠቂ ወገኖች በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ፣ ነገር ግን በኅብረተሰቡ ላይ በቂ የሆነ የግንዛቤ ሥራ ባለመሠራቱ የሚደርስባቸው መገለል እንዳልቀረ የተናገሩት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ናቸው፡፡

የሥጋ ደዌ እንደማንኛውም በሽታ በወቅቱ ወደ ሕክምና በመሄድ በቀላል ሕክምና የሚድን መሆኑን በተግባር በማየት በጊዜ ሒደት ለውጥ ቢመጣም አሁንም ግንዛቤ ላይ አጠናክሮ መሥራት ይጠይቃል፡፡

በኢትዮጵያ ከሁለት አሠርታት በፊት በዓመት ከሃያ እስከ ሠላሳ ሺሕ ዜጎች በሥጋ ደዌ እንደሚጠቁ መረጃ የሚያሳይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ቁጥር በዓመት እስከ አራት ሺሕ መቀነሱ ተመላክቷል፡፡ የሥጋ ደዌ በሽታን ለመቆጣጠር መንግሥት፣ ማኅበሩና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡

የዓለም የሥጋ ደዌ ቀን የሚከበረው በኢትዮጵያ 21 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 66 ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ