Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባርና አሠራር ረቂቅ መመርያ እንዲሻሻል ተጠየቀ

የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባርና አሠራር ረቂቅ መመርያ እንዲሻሻል ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባርና ረቂቅ መመርያ፣ የምርጫ ዘገባን የበለጠ ስለሚያከብደው ይስተካክል ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮችና ጋዜጠኞች ጥሪ አቀረቡ፡፡

ቦርዱ ቅዳሜ ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ለውይይት ባቀረበው በዚህ መመርያ ላይ ለመሳተፍ የተገኙ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች፣ መመርያው ሥራን ከማቅለልና ከማቀላጠፍ ይልቅ ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ተገቢ ያልሆኑና ምርጫ ቦርድን የማይመለከቱ ዝርዝሮች ያሉበት ነው ሲሉም ተችተውታል፡፡

መመርያው በአዋጅ ቁጥር 1162/2012 የተሰጠውን ሥልጣን መሠረት አድርጎ ምርጫ ቦርድ ያወጣውና የአዋጁን አንቀጽ 44 (4)፣ አንቀጽ 123 እና አንቀጽ 126 የሚጠቅስ ቢሆንም፣ የሕግ ሥልጣን ስላለው እንጂ የመመርያው አስፈላጊነት ምን እንደሆነ የሚያስረዳ የተቀመጠ መግቢያ የለውም፡፡ የምርጫ ቦርድ መመርያ ተቀምጦለት ዓላማውና አስፈላጊነቱ ቢብራራ የሚል ሐሳብ ከካፒታል ጋዜጣ ተወካይ ቀርቦ ነበር፡፡

ቦርዱ ያረቀቀው መመርያ አላስፈላጊ ዝርዝር ውስጥ ገብቶ ሁሉን ለመጠቅለል ፍላጎት ያለው ይመስል የማያገባውን ሥልጣን ዘርዝሯል የሚል ከፎርቹን ጋዜጣ ትችትም ቀርቧል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ በተለይ የሥነ ምግባርና የጋዜጠኝነት ሙያን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን በመያዙ፣ ቦርዱ ምን ስላገባው ነው እዚህ ሁሉ ዝርዝር ውስጥ የገባውና በተለይ የግል መገናኛ ብዙኃንን ሊገዛ የሚሞክረው የሚል ሙግትም ተሰምቷል፡፡ በተጨማሪም ምንም እንኳን የተዘረዘሩት የሥነ ምግባር መርሆዎች ከሚሠራባቸው መርሆዎች ጋር ተመሳሳይ ቢሆኑም፣ በምርጫ ቦርድ ሲጫን ግን አላስፈላጊ ቁጥጥርንና የበላይነትን ያስከትላል ተብሎም ተተችቷል፡፡ ስለዚህም ይኼንን መመርያ ያዘጋጀው አካል ምን አስቦ ነው የሠራው የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡

መመርያው የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃንን እኩል የሚገዛ መሆን እንደሌለበት፣ በግልጽ ለይቶ አዘጋገብንና አመራርን በሚያቀላጥፍና ሁለቱን የመገናኛ ብዙኃን በመለየት መቅረብ እንዳለበትም ተጠይቋል፡፡ በመመርያው ውስጥ የተቀቀመጡ ዝርዝሮች አሥጊና አላስፈላጊ የሆኑት በሙያው ውስጥ ካሉ ተቋማት ጋር በቅንጅት ባለመሠራቱ እንደሆነ በማመላከትም፣ ከመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጋር በትብብር ቢሠራ ቀላል ይሆን እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መመርያው መገናኛ ብዙኃንን የማስገደድ አዝማሚያ ያለው ስለሚመስልም፣ ለምን ራሱ ምርጫ ቦርድ ዜናውን ጽፎ አይሰጠንም አስብሎናል ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ተደምጠዋል፡፡

መመርያው ለምርጫ ዘጋቢዎች ዕውቅና የሚሰጥ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ለዚህ ዕውቅና የመገናኛ ብዙኃን የተቋሙን ስምና አድራሻ፣ ተቋሙ የሚሸፍናቸው ሥራዎችና መከታተል የሚፈልገውን የምርጫ ሒደት፣ የጋዜጠኞችን  ስም ዝርዝር፣ የጋዜጠኞችን ቡድን የሚመራው ጋዜጠኛ ስምና አድራሻ፣ እንዲሁም ለውጭ ጋዜጠኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ቀን ተጠቅሶ ጥያቄ መቅረብ ይኖርበታል ይላል፡፡

በረቂቁ ተካትቶ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት ማን እንደሆነ ከማመልከቻው ጋር መቅረብ አለበት የሚለው መሥፈርት፣ አስፈላጊነቱ ተመዝኖ እንዲቀር መደረጉ በውይይት መድረኩ ተገልጿል፡፡

መመርያውን ለውይይት ያቀረቡት የምርጫ ቦርድ ተወካዮችና የመመርያው አርቃቂዎች የተሰጡ ግብዓቶች ጠቃሚ እንደሆኑ፣ በአግባቡ መሻሻል ያሉባቸው ጉዳዮች ታይተው ለአሠራር በሚያመች መንገድ ይስተካከላሉ ያሉ ቢሆንም፣ ከተነሱት ነጥቦች ውስጥ የትኞቹ እንደሚሻሻሉና የትኛው እንደማይሻሻሉ አልገለጹም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...