Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስንዴ ግዥ ከጨረታ ውጪ ለማከናወን ዕቅድ ወጣ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣውን የስንዴ ግዥ ከዚህ ቀደም ከነበረው የጨረታ ሒደት በመውጣት ከተለያዩ ስንዴ አምራች አገሮች በቀጥታ ለመግዛት መታቀዱን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ በቅርቡ 400 ሺሕ ቶን ስንዴ ግዥ ለመፈጸም ተከፍቶ በነበረው ጨረታ ውጤት በእንጥልጥል ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

 የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፅዋዬ ሙሉነህ ባለፈው ሳምንት እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ይፈጸም የነበረው የስንዴ ግዥ ይቆማል፡፡ ከስንዴ ግዥ የጨረታ ሒደትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ምክንያት፣ መንግሥት በቀጥታ ከስንዴ አምራች አገሮች መንግሥታት ጋር በመነጋገር ግዥ ለመፈጸም በሒደት ላይ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ያለ ነጋዴዎችና ደላሎች ጣልቃ ገብነት በመንግሥታት መካከል በሚደረግ ስምምነት ግዥውን ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑን፣ የዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ ያስረዳል፡፡

እንዲህ ያለውን አሠራር መተግበር ከዚህ ቀደም ከስንዴ ግዥ ጋር ይፈጠር የነበረውን የጊዜ መራዘምና ስንዴውን ለማስገባት ይወስድ የነበረውን ጊዜ ለማሳጠርና፣ በዋጋም የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያግዝ መሆኑን ወ/ሮ ፅዋዬ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በየዓመቱ የሚያስፈልገውን የስንዴ ግዥ ሲፈጽም የነበረው ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት አሸናፊ የሆኑ ኩባንያዎች እንዲያቀርቡ በማድረግ መሆኑን፣ ከአሁን በኋላ ግን ይኼ አሠራር ይቀየራል ብለዋል፡፡

በተለይ ከጨረታ ሒደት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮች ስንዴው አገር ውስጥ በወቅቱ እንዳይገባ ማድረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸው፣ በዚህም ሳቢ አሠራሩን በመለወጥ በቀጥታ የመንግሥት ለመንግሥት ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል አዲስ አሠራር ለመተግበርም ቀድመው መሠራት ያለባቸው እየተከናወኑ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ የልዑካን ቡድን በስንዴ ምርት ከሚታወቁ አገሮች መካከል ሩሲያ፣ ዩክሬንና አውስትራሊያ በመጓዝ ከእነዚህ አገሮች መንግሥታት በቀጥታ ስንዴ ለመግዛት ያስችላሉ በተባሉ ሁኔታዎች ላይ ስለመምከሩና አንዳንድ ጉዳዮችንም ማመቻቸቱ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ዋና ዳይሬክተሯ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የስንዴ ግዥ መንግሥት ከመንግሥት ጋር እንዲፈጸም የሚኬድበት አዲሱ አሠራር፣ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ስንዴውን ሲያቀርቡ የነበሩ ነጋዴዎች ወይም ደላሎች ስለነበሩ በኮሚሽን የሚወስዱት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ አሁን የታሰበው ዕቅድ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ለመግዛት በወጣው ጨረታ ተሳታፊ የሆኑና በተለያዩ መንገዶች አሸናፊ መሆናቸው የተገለጸው ሦስት ኩባንያዎች፣ ስንዴውን ማስገባት አለማስገባታቸው አለመታወቁ ተገልጿል፡፡

በዚህ ጨረታ ተሳታፊ ከሆኑ መካከል ጨረታው ሲከፈት አነስተኛ ዋጋ ያቀረቡት አግሮ ኮፕና ሃካን የተባሉ ኩባንያዎች በወቅቱ ማሟላት ይጠበቅባቸው ነበር የተባለውንና ከሻጋታ ነፃ የሆነ ማስረጃ ባለማቅረባቸው፣ ቴክኒካዊ መሥፈርት አላሟላችሁም ተብለው ውድቅ ተደርገው ነበር፡፡

ሁለቱ ኩባንያዎች ከቀረበው 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እያንዳንዳቸው 200 ሺሕ ቶን ስንዴ ለማስገባት የተወዳደሩ ነበሩ፡፡ በቴክኒክ መሥፈርቱ ሁለት ኩባንያዎች ሲወድቁ፣ ሦስተኛ ዋጋ የሰጠውና 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማስገባት የተወዳደረው ጄኒ ኮርፕ የጨረታው አሸናፊ ተደርጓል፡፡ ሆኖም በጨረታ ሒደቱ ላይ ቅሬታ ያላቸውና አነስተኛ ዋጋ አቅርበው የነበሩት ሁለቱ ኩባንያዎች፣ ጨረታው ሦስተኛ ዋጋ ላቀረበው መሰጠት የለበትም በሚል አቤቱታ አቅርበው ማሟላት ያለባቸውን ማሟላት ከቻሉ፣ ካቀረቡት ዋጋ አንፃር የጨረታው አሸናፊ መሆን እንደሚችሉ ተገልጾላቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሁለቱ ኩባንያዎች ዋነኛ ቅሬታ አቅራቢው አግሮ ኮፕ፣ አሸናፊ የሆነበትን 200 ሺሕ ቶን ስንዴ እንዲያቀርብ የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉ ታውቋል፡፡ ለሁለቱ ኩባንያዎች ስንዴውን እንዲያስገቡ መፈቀዱ አግባብ አልነበረም ያለው ጄኒ ኮርፕ አቤት በማለቱ፣ ስንዴውን ማቅረብ እንደማይችል እየተገለጸ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ወ/ሮ ፅዋዬ፣ ስንዴውን እንዲያቀርብ አሸናፊ የተደረገው አግሮ ኮፕ ስንዴውን እንዲያቀርብ በደብዳቤ የተጠየቀው ማስጠንቀቂያ ሲሆን፣ የማያቀርብ ከሆነ ጉዳዩ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን የ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጨረታው ጉዳይ ዕልባት ያላገኘ በመሆኑ ውጤቱ በቅርቡ ይታወቃል ተብሏል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ስንዴውን የሚያስገቡ ከሆነ ሌላ ዘዴ እንደሚፈልግ ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ገበያ ለማረጋጋትና በየዓመቱ ዕርዳታ ለሚሹ ወገኖች ለሚያስፈልገው የስንዴ አቅርቦት፣ መንግሥት ከ32.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 5.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ መግዛቱ ታውቋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች