Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለተሳፋሪ ደኅንነት ከቀበቶ ባሻገር ይታሰብ!

ከሰሞኑ የጦፈ ገበያ ከደራላቸው ዕቃ መካከል አንዱ የቱ ነው ከተባለ፣ የተሽከርካሪ የደኅንነት ቀበቶ ተወዳዳሪ አይገኝለትም፡፡ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ዋጋውም በዚያው ጣሪያ ላይ ወጥቷል፡፡

ያገለገለውም አዲሱም የደኅንነት ቀበቶ ዋጋ ሰማይ ነክቷል፡፡ ይህ የሆነው ተሽከርካሪዎች ለተሳፋሪዎች ደኅንነት መጠበቂያ ቀበቶ እንዲኖራቸው በመደንገጉና ይህን በሚተላለፉት ላይ ቅጣት መጣሉን የሚገልጽ ትዕዛዝ መንግሥት በማስተላለፉ ነው፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች ከወትሮው በተሻለ ሥራዬ ብለው በመቆጣጠራቸው በርካታ አሽከርካሪዎች ዞር ብለው ያላዩትን ቀበቶ ለአገልግሎት ሲያበቁ፣ የሌላቸው እንደ አቅማቸው አዲሱን፣ ያልቻሉት አሮጌውን ቀበቶ ለመግዛት ተሯሩጠዋል፡፡ አሮጌ ተራ በመሄድ በተጠየቁት ዋጋ ገዝተው የደኅንነት ቀበቶ በየወንበራቸው አስረዋል፡፡

በታክሲም ሆነ በሌሎች ተሽከርካሪዎች የፊት መቀመጫ የሚሳፈሩ ተጓዦች የደኅንነት ቀበቶ በግዴታ ታጥቀው መጓዝ ጀምረዋል፡፡ ቀበቶ የመታጠቅ ልምድ የሌላቸው ተጓዞች እየተጎተጎቱ ቀበቶ ማሰርን ሲላመዱ እየተመለከትን ነው፡፡ በግዴታ እየተለመደ የመጣው የደኅንነት ቀበቶ የማሰር ጉዳይ፣ ከሰሞኑ ግርግር አኳያ ሊያሳየን የሚችላቸው አንዳንድ ነገሮች አልጠፉም፡፡

ለጉዞ ደኅንነት ሲባል ቀበቶ አስሮ የመጓዝን አስፈላጊነት ያልተገነዘቡ አሊያም ቸልተኛ የሆኑ ሁሉ ትቀጣላችሁ ሲባሉና ሲቀጡም ጭምር ቀበቶ ማሰርና ማስተሳሰር መጀመራቸው ሳያስተዛዝበን አልቀረም፡፡

ለራሳችን ደኅንነት በማሰብ ልናደርገው የሚገባንን ቁምነገረኛ ተግባር፣ ቅጣት ስለተጣለብንና በየመንገዱ ቁጥጥር ስለጠበቀብን ቀበቶ ማሰራችን፣ ያሳፈርናቸውንም ‹‹እንዳታስቀጡን ቀበቶ እሰሩ፤›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ስንሰጥ መዋላችንን ያየ አጃኢብ ሳይለን አያልፍም፡፡

ምልከታና ዕይታችን ላይ ብዙ የለውጥ ሠራዊት ማዝመት እንደሚያስፈልገን ይጠቁመናል፡፡ እየሞትንም ቢሆን ስለደኅንነታችን ሌላ አካል እየነገረና እየተቆጣጠረን ካልሆነ በቀር፣ እኛው ለእኛው ቀድመን የሚጠበቅብንን በማድረግ ከነጋሪና ከአዋጅ በፊት ለደኅንነታችን አለመጨነቃችንን ያሳበቀ ዕርምጃ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ለጋራ ደኅንነታችን ሲባል ይህንን እስካሁን አለመፈጸማችን ያውም በዓለም ላይ በተሽከርካሪ አደጋ ስማቸው ጎልተው ከሚጠቀሱ አገሮች ተርታ ተሠልፈን ሳለ፣ የደኅንነት ማስጠበቂያ ሥልቶችን ቀድመን አለመተግበራችን ሊያስቆጨን ይገባል እንጂ፣ ጭራሹኑ መንግሥት መዓት እንዳመጣብን፣ ‹‹ባንገደድ ኖሮ አናደርገውም፤›› ነበር የሚያስመስልብንን  ሰሞንኛ ሁኔታ በሠለጠነ ዘመንና ከተማ እንደሚኖሩ ቂሎች ያስቆጥረናል፡፡

በእርግጥ በርካቶችን ያማረረው ይህ ሥርዓት በፈቃደኝነትና በይሁንታ መተግበር ነበረበት፣ ያለ ወትዋች፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነቱ ተነሳሽነትና ልምድ ስለሌለ፣ አስገዳጅ ሆኖ በሚመጣበት ወቅት በርካታ ተሽከርካሪዎች ለተሳፋሪ የሚውል ቀበቶ ስላልነበራቸው ወይም የነበራቸውን አውልቀው በመጣላቸው ለግዥ ሲንጋጉ ዓይተናል፡፡ በዚህ ሰበብ ዋጋው ጣራ በመንካቱ ተጠቃሚው ሊማረር ይችላል፡፡ ይህ መሻሻል አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ቀበቶ አልባ ተሽከርካሪ ቀድሞውኑ ለምን እንደምናሽከረክር፣ ለምንስ በዚያ ተሽከርካሪ እንደምንሳፈር ቆም ብለን ማሰብ ነበረበን፡፡ እርግጥ 88 በመቶው ተሽከርካሪ እስኪበቃው አገልግሎት ከሰጠ በኋላ፣ ከአዲስ ተሽከርካሪ በላይ ዋጋ በመክፈል በምታስገባ አገር ውስጥ የደኅንነት ቀበቶ የሌለው ተሽከርካሪ መኖሩ አያስገርምም፡፡ ሕጉ ግን መከበር አለበት፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአንዳንዶቹ ቀበቶ አደጋ ሊቀንስ ይቅርና ለባሰ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ይታያል፡፡ የደኅንነት ቀበቶ ከውጭ ሲታይ መጠለቁ እንጂ ትክክለኛ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ለምልክት ጣል የሚደረጉ ሲታዩ፣ ትራፊክ ፖሊስ ይህ ይጠፋዋል ብለን አናስብም፡፡ ስለዚህ አጠራጣሪ ሆነው ሲገኙ ጠጋ ብሎ መፈተሹ ይበጃል፣ ተልዕኮው አደጋ መቀነስ እስከሆነ ድረስ፣ ተሳፋሪም ግድ የለሽ ሆኖ ሲገኝ፣ ተቆርቋሪው ይጨነቅለት እንደማለት ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ የአገር ነውና መቆጣጠሩ ይበል እንላለን፡፡

እንዲያው ሰሞንኛ ጉዳይ ሆነና የደኅንነት ቀበቶን አነሳን እንጂ፣ የተሽከርካሪዎችን አጠቃላይ ይዘት እንመልከት ብንል፣ የተሽከርካሪ ቀበቶ ከሚታየው ጉድለት አኳያ ኢምንት ሆኖ የምናገኝበት ጉድ ስንት እንደሚሆን መገመት አይቸግርም፡፡

ሕዝብ የሚገለገልባቸው ታክሲና የሕዝብ ማመላለሻ የመሳሰሉትን ተሽከርካሪዎች ይዘት ብንፈትሽ ከአቅመ ተሽከርካሪነት የወጡ፣ ተስካራቸው ሊወጣላላው የሚገባቸውና  በአደጋ የተከበቡ በርካታ ተሽከርካሪዎች በየጎዳናው ሲርመሰመሱ እያየን፣ ለደኅንነት ቀበቶ መበርታታችን ቢያጠያይም ከምንም ይሻላልና ይህ ክትትልና ቁጥጥር ይሰንብት ማለት ሳይሻለን አይቀርም፡፡ ለነገሩ በየዓመቱ ለመሽከርከር እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ዓመታዊ ፍተሻና ምዘና ተደርጎላቸዋል የሚባሉ ተሽከርካሪዎች አካላዊ ይዘት ውስጣዊ ብቃታቸው ጎዳና ለመውጣት የማያበቃቸው ቢሆንም ይሁንታ ይሰጣቸዋል፡፡

ስለዚህ ከደኅንነት ቀበቶ ባሻገር አደጋ የሚያብሱ፣ ውስጣዊ ጉድለታቸው የሚያስደነግጡ ተሽከርካሪዎች ችላ እንደሚባሉ እናያለን፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል በግድም ቢሆን ቀበቶ በአግባቡ ማሟላትና መጠቀም ግዴታ እንደተደረገው ሁሉ፣ ቢያንስ የከፋ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ የተሽከርካሪዎችን የቴክኒክ ጉድለቶች በመለየት አስገዳጅ ዕርምጃ የሚወሰድበት አሠራር መምጣት አለበት፡፡

ዓመታዊ የተሽከርካሪ ምርመራ ሲደረግ ሆነ ተብለው በጥቅማ ጥቅም የሚታለፉ፣ ነገር ግን ዕርምት የሚያስፈልጋቸው የቴክኒክ ጉድለቶችን ለመቆጣጠር፣ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አደጋን ለመቀነስ፣ አደጋ ቢደርስ እንኳ የጉዳት መጠኑን ዝቅ ለማድረግ ቀበቶዎችን በአግባቡ መጠቀም ብቻም ሳይሆን፣ ለከፋ አደጋ ሰበብ የሚሆኑ የቴክኒክ ጉድለቶች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ይደረግ፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ከመቀመጫቸው ጀምሮ ምን ያህል ለአደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ እየታየ መታለፋቸው ትልቅ ስህተት ነው፡፡

ለሕዝብ ማመላለሻዎች ፈቃድ የሚሰጣቸው ተሳፋሪዎችን ከደኅንነት በመጠበቅ እንዲያጓጉዙ ቢሆንም፣ በራቸው የማይከፈት፣ መስኮታቸውን ሆን ተብሎ እንዳይከፈት የሚደረጉ፣ በአደጋ ጊዜ ለመውጣት ቀርቶ ለመተንፈስ በሚያስቸግር ሁኔታ የሚዘጉ ተሽከርካሪዎች አይታዩም፣ አይጠየቁም፡፡ ተሽከርካሪ ለማስነሳት የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን የሚያቀጣጥሉ፣ የጎን መስታወት የሌላቸው፣ ለዕይታ አዳጋሽ እስኪሆኑ ድረስ መስታወታቸው የተሰነጣጠቁና እንዲህ ያሉ በርካታ ጉድለት ያለባቸው ላይ እንደ ቀበቶው ያለ ዕርምጃ ያስፈልጋቸዋል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት