Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግዥ ሥርዓቱን ያዛቡ የሕግ ክፍተቶች አላላውስ ያሉት የመንግሥት ተቋም አቤቱታ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁ ግዥዎችን በመፈጸም ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ ሲቋቋም አንዱና ዋና ዓላማው፣ በፌዴራል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ መሥሪያ ቤቶች የሚያስፈልጓቸውን ዕቃዎች በማዕቀፍ ወይም በብዛት በመግዛት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት ነው፡፡

ከመሥሪያ ቤቶቹ በሚቀርቡ የግዥ ጥያቄዎች መሠረት፣ ቁሳቁሶችንና ልዩ ልዩ መገልገያዎችን በማዕቀፍ በመግዛት መንግሥት በተናጠል በእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ግዥ ቢፈጸምባቸው ሊያስከትሉ የሚችሉትን ወጪ፣ በብዛት በመግዛት ሥርዓት የዋጋ ቅናሽ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ በአጭሩ ይህ አሠራር የግዥ ወጪ እንዲቀንስ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ይገለጻል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፅዋዬ ሙሉነህ ሐሙስ፣ ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የድርጅቱ አገራዊ ጠቀሜታ ጉልህ እንደሆነ፣ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነትም የመንግሥትን ወጪ በመቀነስ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ በመሆኑ ይኸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

የድርጀቱ ወጪ ቆጣቢ የግዥ ሥርዓት አስተዋጽኦው ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት፣ በሦስት ዓመታት በማዕቀፍ የተከናወኑ ግዥዎች ያስገኙትን የዋጋ ቅናሽ ከገበያው ዋጋ ጋር በማመሳከር አመላክተዋል፡፡

በዋቢነት ካነሷቸው ግዢዎች መካከል፣ በነሐሴ 2011 ዓ.ም. ለአንድ ካነን ፎቶ ኮፒ ማሽን ይጠየቅ የነበረው ዋጋ በገበያው ሒሳብ መሠረት 13,352 ብር ነበር፡፡ ይሁንና ድርጅቱ በማዕቀፍ ግዥ ሥርዓት መሠረት ይህንኑ ማሽን የገዛው በ8,587 ብር እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በአንድ ፎቶ ኮፒ ማሽን ከ4,765 ብር በላይ የዋጋ ቅናሽ መገኘቱን አመላክተዋል፡፡ በኮምፒዩተሮች፣ በአላቂ ዕቃዎችና በሌሎች መገልገያዎች ረገድ በአንድ ዕቃ እስከ 12,000 ብር የዋጋ ልዩነት በሚያሳይ ቅናሽ ለመግዛት የሚያደርገው እንቅስቃሴና የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡

ይህ ተቋም እንዲህ ባለው ተግባሩ ወደፊት ተራምዶ የሚፈለግበትን ለማከናወን የሚፈታተኑት ጫናዎች እንዳሉበት አስታውቋል፡፡ በተቋቋመበት ዓላማ አግባብ እንዳይሠራ ማነቆ ከሆኑበት ጉዳዮች መካከል የፖሊሲ ማስተካከያ ጭምር የሚያስፈልጋቸው እንዳሉ ኃላፊዋ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ተቋሙ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጭምር አቤት ማለቱ ታውቋል፡፡ ስለገጠሙት ችግሮች ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጻፈው ደብዳቤ፣ መሥሪያ ቤቱ የተቋቋመበት አዋጅና መመርያ እንዲሻሻልለት ጠይቋል፡፡

‹‹የማዕቀፍ ስምምነት የውል አስተዳደር›› የተሰኘው የግዥ ሥርዓት በግዥ አዋጁም ሆነ በግዥ አፈጻጸም መመርያው በተገቢው ጥልቀት ያልተዳሰሰ በመሆኑ፣ አሠራር የሌላቸው ሕጎች የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ግልጽነትና ተጠያቂነትን መፍጠር እንዳላስቻለው አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አስገዳጅ ድንጋጌዎች ቢቀመጡም፣ እነዚህን ባላከበሩት ላይ ስለሚወሰደው ዕርምጃ የተቀመጠ የቅጣት ድንጎጌ ባለመኖሩ የማዕቀፍ ስምምነት ውል አስተዳደርን ለመተግበርና ውል በሚጥሰው አካል ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ለማምጣት አዳጋች በማድረጉ እንዲህ ያለው ጉዳይ ሊስተካከል እንደሚገባው ተቋሙ ጠቅሷል፡፡

የግዥ ተቋሙ አላሠራ ብለውኛል ያላቸውን ሌሎች ነጥቦችም በደብዳቤው በዝርዝር ጠቅሷል፡፡ ካሰፈራቸው ስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡ አቅራቢዎች የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ከፍተው በቀላሉ ዕቃዎችን ማስመጣት እንዲችሉ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አኳያ በማዕቀፍ ስምምነት የሚገዙ ዕቃዎች በአብዛኛው ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ እያጡ፣ ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች አማካይነት የሚመረቱ ዕቃዎችን በውሉ መሠረት እንዲቀርቡለት ማድረግ እንዳልቻለ በመግለጽ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረበትን የአሠራር ችግር በመጥቀስ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታውን አስፍሯል፡፡  

በተቋሙ በኩል በማዕቀፍ ተገዝተው የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚጣለው ታክስ ከፍተኛ መሆን የተቋቋመለትን የዋጋ ቅናሽ ተጠቃሚነት ዓላማ እንደተገዳደረው አስታውቋል፡፡ ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2014 አንቀጽ 90 መሠረት ወደ አገር ለሚገባ ዕቃ የግብይት ዋጋ ተደርጎ የሚታሰበው ለተሸጠው ዕቃ የተከፈለው ወይም የሚከፈለው ዋጋ እንደሆነ ቢመላከትም፣ የቀረጥ አተማመኑ ግን ከዚህ አሠራር ውጪ በመሆኑ ችግሮች እንደሚገጥሙት ያሳያል፡፡  

በማዕቀፍ ስምምነት አማካይነት አቅራቢ ድርጅቶች ለመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሚያስመጧቸው ዕቃዎች ዋጋ ፍትሐዊ በሆነ የገበያ ውድድር ላይ ተመሥርተው ከጥቅል ሽያጭ የሚገኘውን ትርፍ በማስላት ቢያቀርቡም፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ግን በማዕቀፍ ስምምነት አማካይት አቅራቢዎች የሰጡት ዋጋ ሆነ ተብሎ ቀረጥ ለመቀነስ የተደረገና ከተገዙበት ዋጋ በታች እንደገቡ በማሰብ የሚጥልባቸው ቀረጥ እንቅፋት እየሆነበት እንደመጣ አስታውቋል፡፡ በዚህ ሳቢያ በአቅራቢዎች በኩል የሚቀርቡ ሰነዶች የጉምሩክ ፎርማሊቲያቸው ተጠናቆ በተገቢው ጊዜ ግዥ ለሚፈጸምላቸው ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የተገዙ ዕቃዎች እንዳይሰራጩ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩንም የግዥ ተቋሙ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም ምክንያት በማዕቀፍ ስምምነት የገቡ አቅራቢዎች ዕቃዎቹን ካስመጡበት ዋጋ በላይ ቀረጥ እንዲከፍሉ ሲጠየቁ በኪሳራ ሳቢያ ዕቃ ከወደብ ለማንሳት እየተቸገሩ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡ ዕቃዎቹም በውል አግባብ መቅረብ በሚገባቸው ጊዜ እንዳይቀርቡ አድርጓል የሚለው የተቋሙ አቤቱታ፣ ችግሩ ከዚህም በላይ እንደሆነበት አመልክቷል፡፡ ለዚህ በማሳያነት ያቀረበው በቅርቡ በማዕቀፍ ግዥ ወደ አገር የገባ ላፕቶፕ በተጣለበት ቀረጥ ምክንያት ከጉምሩክ አለመውጣቱን ነው፡፡

የሎጀስቲክስ ችግር እንደሚፈታተነው ሲያብራራም፣ ዕቃዎች ተጓጉዘው የሚመጡት በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኩል ቢሆንም፣ በዚህ ችግር ሳቢያ ዕቃዎች ከወደብ ተነስተው ለየመሥሪያ ቤቶቹ በፍጥነት እንዳይከፋፈሉ ጫና ፈጥሯል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ለረጅም ጊዜ በጂቡቲና በደረቅ ወደቦች ተከማችተው ስለሚቆዩ በማዕቀፍ ስምምነት የሚቀርቡ ዕቃዎች በተቋሙና በአቅራቢዎቹ ውል መሠረት እንዳይቀርቡ አድርጓል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ግዥ የሚፈጸምላቸው ተቋማት በተገቢው መንገድ የግዥ ፍላጎታቸውንና ዕቅዳቸውን ገልጸው ያቀርቡለታል፡፡ ይህን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ በሚገጥሙት እንዲህ ያሉ ችግሮች ሳቢያ ለመሥሪያ ቤቶቹ እንደ ዕቅድና ፍላጎታቸው አግባብ ግዥ መፈጸምም ዕቃ ማቅረብም አልቻለም፡፡ በዚህ ሳቢያ መሥሪያ ቤቶቹ ከዕቅድ ውጪ ለመሆን መገደዳቸውን አመላክቷል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ከ189 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ግዥ ሊፈጸምላቸው የቻሉት 40 ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ ለዓቃቤ ሕግ በጻፈው ደብዳቤም፣ የግዥ ሒደት የሚጀምረው ከተቋማት ፍላጎት እንደሆነ ጠቅሶ፣ ፍላጎታቸውን ያላሳወቁ መሥሪያ ቤቶች የማዕቀፍ ስምምነት የግዥ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ቢደረግም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስላመዘነ የግዥ ዕቅድ ቢልኩም ባይልኩም መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ሥርዓት ተጠቃሚ ተደርገዋል ብሏል፡፡ ይህ ደግሞ የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ በአግባቡ የግዥ ዕቅዳቸው ያሳወቁ መሥሪያ ቤቶች በዕቅዳቸው መሠረት ዕቃዎቻቸውን ማግኘት እንዳይችሉ ሰበብ እየሆነ እንደመጣም አብራርቷል፡፡   

ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በግዥ ፍላጎታቸው መሠረት ዕቃ መግዛት አለመቻላቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ያሳሰበው ተቋሙ፣ የንብረት ርክክብና ክፍያ ላይ አለመግባባቶች እንደሚታዩ አመላክቷል፡፡ መሥሪያ ቤቶች በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ያዘዟቸው ዕቃዎች ከቀረቡላቸው በኋላ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ፈትሸው ርክክብ ሲፈጽሙ አይታዩም ከማለቱም ባሻገር፣ በውሉ መሠረት በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያ መፈጸም ሲጠበቅባቸው፣ ክፍያ በማይፈጽሙ መሥሪያ ቤቶች ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በግዥ አፈጻጸም መመርያው ላይ በግልጽ ስላልተመለከተ አፈጻጸሙን አዳጋች እንዳደረገበት አስታውቋል፡፡

በዚህ ምክንያት ተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶች ገንዘባቸው እየተያዘባቸው ሌሎች አቅርቦቶችን ማግኘት እንዳይችሉ እንቅፋት እንደሆነባቸው በመግለጽ፣ በማዕቀፍ ስምምነት የሚቀርቡ ዕቃዎችን በውሉ መሠረት ማቅረብ እንደቸገረው የግዥ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

ተቋሙ ተቸግሬበታለሁና መፍትሔ ይሰጠኝ ያለው ሌላው ጉዳይ፣ ለመግዛት ያቀደውን ዕቃ በሚፈልገው ደረጃና መጠን ለማግኘት አለመቻሉን ነው፡፡ የማዕቀፍ ስምምነት አፈጻጸሙን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገውም የምርት አቅርቦት አለመኖር ወይም እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ነው፡፡ የአቅርቦት እጥረት ሲያጋጥም መሥሪያ ቤቶች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጠር ሲባል የአቅራቢ ለውጥ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የአቅራቢ ለውጥ ተደርጎም ምርቱ መቅረብ ባይችልስ? ምን ያህል ጊዜ ይጠበቅ? ግዥው አስቸኳይ ቢሆንስ? የሚለውን ለመመለስ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ታይተው መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ተጠይቋል፡፡  

በተለያዩ የገበያ ተፅዕኖዎች አቅራቢ ድርጅቶች ውሉ ላይ በተቀመጠው ሁኔታና ድንጋጌ መሠረት ዕቃዎችን ማቅረብ የማይችሉበት አጋጣሚ ሲፈጠርም፣ ወደ ቅጣት ከተገባ የማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ሥርዓቱ በአቅራቢ ዕጦት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳደረበት ተቋሙ ይገልጻል፡፡  

የማዕቀፍ ግዥዎችን ሲፈጸሙ የሦስት ዓመታት ውልና ስምምነት ይታሠራል፡፡ ለሦስት ዓመት የማዕቀፍ ስምምነት የፈጸመ አቅራቢ ድርጅት ግዴታ ገብቶ ከተዋዋላቸው መሥሪያ ቤቶች መካከል ለአንዱ ማቅረብ ባይችል፣ አቅራቢው ምን ዓይነት ቅጣት ይጣልበት ወይም ምን ይወሰንበት በሚሉና በሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መመርያ ካልተዘጋጀ የማዕቀፍ ስምምነት በጥቅል ለሚፈጸም ግዥ የሚተገበር በመሆኑ፣ አቅራቢው ድርጅት ከእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ጋር ግልጽ ስምምነት ሊኖረው እንደሚገባ ተጠይቋል፡፡

በማዕቀፍ ስምምነት ዕቃ የሚቀርብላቸው ተቋማት በወቅቱ ባልቀረበላቸው ዕቃ ልክ የጉዳት ካሳ ክፍያ መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በተግባር የሚገጥመው ችግር ተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶች የግዥ ትዕዛዝ ሰጥተው ዕቃዎችን ውሉ ላይ በተገለጸው የማቅረቢያ ጊዜ ውስጥ ማግኘት ካልቻሉ ምን መደረግ አለበት? ምን ያህል ጊዜ ይጠብቁ? የሚሉ አሻሚ ጉዳዮችንም የግዥ ተቋሙ አንስቷል፡፡ ያልቀረበው ዕቃ ዋጋ አሥር በመቶ እስኪሞላ ድረስ 100 ቀናትን ጠብቀው ዕቃዎችን ማግኘት ያልቻሉ ተቋማት የተጣራ የጉዳት ካሳ ክፍያቸው ከየትና እንዴት ይቀነስ? በተሰጣቸው የግዥ ትዕዛዝ መሠረት ዕቃዎችን ማቅረብ ባልቻሉ አቅራቢዎች ላይ ካስያዙት የውል ማስከበርያ ዋስትና ላይ የተጣራ የጉዳት ካሳ ክፍያ ተቀናሽ ሲደረግ አብሮ ምን ዓይነት ዕርምጃ ይወሰድ? በሚሉትና በሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የተደነገገ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የአቅርቦት መስተጓጎል ሲፈጠር፣ በአቅራቢ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ችግር እንደሚያጋጥመው ተቋሙ አብራርቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱለት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ግልጽ መመርያ እንዲያወጣለት የተጠየቀው የግዥ ተቋሙ፣ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችም ሊፈጽምላቸው የሚፈልጉትን ግዥ በዕቅድና በአግባቡ እንዲያቀርቡለትም ጠይቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች