ዘመን ባንክ የክፍያ ሥርዓቱን በመቀላቀል 17ኛው ሆኗል
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ16 ባንኮች ጋር ከ255 ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀሱን አስታወቀ፡፡ ከዘመን ባንክ ጋር ዘመናዊ የክፍያ አፈጻጸም ስምምነት በመፈራረም አብረውት የሚሠሩ ባንኮች ቁጥር 17 አድርሷል፡፡
ባለፉት 11 ዓመታት ከምርት ገበያው ጋር በአጋርነት በሚሠሩት 16 ባንኮች በኩል ወደ ምርት ገበያው የመግዣ አካውንቶችን የገባው የገንዘብ መጠን 255.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከምርት ገበያው ወጥቶ ለሻጮች የተከፈለው የገንዘብ መጠን 247.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በምርት ገበያውና በዘመን ባንክ መካከል ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎትን ለማስፈጸም ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በተፈራረሙበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ምርት ገበያው ዘመን ባንክን 17ኛ የባንክ አጋሩ በማድረግ የአገልግሎት ስምምነት እንዲጀምር ተደርጓል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራና የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘነበ ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነት ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኘሁ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘረጋው ዘመናዊ የክፍያና ርክክብ ሥርዓት ሻጮች ምርታቸውን በሸጡበት ማግሥት ገንዘባቸወን ወደ ባንክ አካውንታቸው በማስገባት ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት ያለ ምንም መጓደል ስኬታማ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ምርት ገበያና በዘመን ባንክ መካከል በዕለቱ የተደረገው ዘመናዊ የክፍያ አፈጻጸም ስምምነትም ተገበያዮች ክፍያቸውን በተቀላጠፈ መልኩ ማካሄድ እንዲችሉ አማራጭ ከመስጠት በተጨማሪ፣ ተደራሽነትን በማስፋት የግብይት ሥርዓቱን ይበልጥ እንደሚያግዝም አቶ ወንድምአገኘሁ ገልጸዋል፡፡
የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመን ባንክ ወደ ዘመናዊ የምርት ግብይት ሥርዓቱ እንዲገባ ላደረገው ድጋፍ አመሥግነው፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር የተደረገው የአገልግሎት ስምምነት የክፍያ ሥርዓቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረውና ባንኩ በውጭ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞችና በአጠቃላይ በግብይት ሥርዓት ውስጥ የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያደርገው ጥረት ያሳድግለታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምርት ገበያና በዘመን ባንክ መካከል በዛሬው ዕለት የተፈራረመው የክፍያ አጋርነት ስምምነት የክፍያ ሥርዓቱን ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ተገበያዮችም የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ምርት ገበያው ዘመናዊ የክፍያ አፈጻጸም ሥርዓትን የጀመረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከዳሸን ባንክ ጋር ባደረጉት ስምምነት እንደነበር ሲታወስ፣ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉም ባንኮች ጋር ስምምነት በማሰር፣ በምርት ገበያው የሚከናወኑ ግብይቶች ክፍያቸው በባንኮች በኩል እንዲፈጸም አድርጓል፡፡