Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለህዳሴ ግድቡ በሚደርሰው የውኃ መጠን ላይ ስምምነት ተደረሰ

ለህዳሴ ግድቡ በሚደርሰው የውኃ መጠን ላይ ስምምነት ተደረሰ

ቀን:

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የነበራቸውን ልዩነት ለማጥበብ ሰሞኑን በአሜሪካ ሰብሳቢነት ባካሄዱት ውይይት ስምምነት ላይ ደረሱ። በስምምነቱ መሠረትም ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከሆነ፣ የድርቅ ወቅት ሁኔታን የሚያመላክት ጣሪያ (ድራውት ትሬሾልድ) አድርገው ተቀብለውታል።

ይህም ማለት ወደ ግድቡ የሚደርሰው የውኃ መጠን የተጠቀሰውን መጠንና ከዚያ በታች በሚሆንበት ጊዜ ኢትዮጵያ የመጣውን ውኃ እንደማትይዝና የግድቡን ተርባይኖች መትቶ ወደ ታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች መልቀቅ እንደሆነ የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ሐሙስ ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋሽንግተን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ድርድሮች የድርቅ ወቅት አመላካች የውኃ መጠን ተብሎ በኢትዮጵያ በኩል ይቀርብ የነበረው 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲሆን፣ በግብፅ በኩል ደግሞ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነበር።

- Advertisement -

በሱዳን በኩል ደግሞ 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የውኃ መጠን የድርቅ ሁኔታ አመላካች ሆኖ ቀርቦ ነበር። በመቀጠል ኢትዮጵያ በሱዳን የቀረበውን አማካይ አኃዝ በመቀበል የድርቅ ሁኔታ አመላካቹ መጠን 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ሐሳብ ብታቀርብም፣ በግብፅ በኩል ግን ተቀባይነት አላገኘም። ግብፅ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በየዓመቱ እንዲለቀቅላት አቅርባ የነበረውን ሐሳብ እንዳነሳች በኢትዮጵያ ኃላፊዎች በኩል ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ የግብፅ ባለሥልጣናት ካይሮ በሚገኙ የሚዲያ ተቋማት በኩል አስተባብለዋል።

ከሰኞ ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. አንስቶ ለሦስት ቀናት በዋሽንግተን በተካሄደው ስብሰባ ግን የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትሮች በ37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ጣሪያ ላይ ስምምነት ማድረጋቸውን፣ ሚኒስትር ስለሺ (ዶ/ር) ገልጸዋል። በእርጥብ የአየር ሁኔታ ወደ ግድቡ የሚወርደው አማካይ የዓባይ ውኃ መጠን 49 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንደሆነ የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች አስረድተዋል።

በመሆኑም በአየር ንብረት ሁኔታ ለውጥ የውኃ መጠኑ ቀንሶ ግድቡ ጋር የሚደርሰው መጠን ወደ 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እስካልወረደ ድረስ በ37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና በ49 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መካከል ያለውን ልዩነት፣ ኢትዮጵያ በዋናው ምዕራፍ የግድቡ ሙሌት ወቅት መያዝ ትችላለች።

በዋናው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ወቅትና ሙሌቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ግድቡ የሚደርሰው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ በግድቡ ከያዘችው ውኃ ላይ ለግብፅና ለሱዳን እንድትለቅ ስምምነት መደረሱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ወቅት የሚለቀቀው የውኃ መጠን ላይ በቀጣይ በሚደረገው ውይይት እንደሚወሰን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ሌላው ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ የግድቡ የመጀመርያ ሙሌት ሲሆን፣ ይኸውም ከዘንድሮ ክረምት ወቅት አንስቶ በሁለት ዓመት ውስጥ የሚከናወን ነው፡፡ ግድቡ ከሚገኝበት 500 ሜትር የባህር ወለል እስከ 595 ሜትር የባህር ወለል ድረስ በፍጥነት የሚከናወን የውኃ ሙሌት እንዲሆን ተወስኗል፡፡

በዚህም መሠረት 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን አሁን ያለው የግድቡ ግንባታ ደረጃ የተጠቀሰውን መጠን ለመያዝ እንደማያስችል ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የመጀመርያዎቹ ሁለት ተርባይኖች በሚቀጥለው ዓመት ከየካቲት ወር በኋላ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችላቸው 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ፣ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ እንደሚያዝ ገልጸዋል፡፡

የግድቡ የግንባታ ደረጃ የሚፋጠን ከሆነ ደግሞ ከዚህ መጠን በላይ እንደሚያዝ አስታውቀዋል፡፡ በግድቡ የሚከናወነው የውኃ ሙሌት በክረምቱ ወቅት ብቻ እንደሚሆን፣ ነገር ግን እንደ ዝናቡ ሁኔታ በመስከረም ወርም ውኃ ለመያዝ እንደሚቻል ሌላው ስምምነት የተደረሰበት ነጥብ ነው፡፡

በዚህ በመጀመርያ ሙሌት ወቅት አስከፊ ድርቅ ከተከሰተ ማለትም የውኃ መጠኑ ከ31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ሙሌቱን እንደምትገታና የመጣውን ውኃ እንደምትለቅም ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስምምነቱ የተደረሰው ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶች አስተዳደርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሠረት አድርጎ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከዚህ አልፎ የተሰጠ፣ አንሶ የመጣም ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

ስምምነቱ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ወደ ሕግ ማዕቀፍነት የመቀየር ተግባር ከሦስቱም አገሮች የሚወከሉ ሦስት የሕግ ባለሙያዎች በሚቀጥለው ሳምንት በሱዳን ተገናኝተው የማርቀቅ ሥራ እንደሚጀምሩ፣ በሚረቀቀው የሕግ ማዕቀፍ ላይም የሦስቱ አገሮች ተወካዮች ጥር 19 እና 20 2012 ዓ.ም. በአሜሪካ ዳግም እንደሚገናኙ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...