የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ረቡዕ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የምርጫ 2012 ጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳ ለውይይት አቅርቧል፡፡ ቦርዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ስለቀጣዩ ምርጫ ዕቅድና መርሐ ግብር ውይይት እያደረገ ሲሆን፣ ጊዜያዊ የምርጫ 2012 ዋና ዋና ቀናትና ተግባራትን ይፋ አድርጓል፡፡
በምርጫ ቦርድ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ማደራጀት ከታኅሳስ 22 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚከናወን ሲሆን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ከጥር 16 እስከ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡ የምርጫ ክልል ካርታ ይፋ የሚደረገው የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ ለመራጮች ምዝገባ ትምህርትና መረጃ መስጫ ጊዜ ደግሞ ከመጋቢት 14 እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሆናል፡፡
የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲደረግ፣ የመራጮች ምዝገባ ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ የዕጩ ምዝገባ ሒደት መረጃ የሚሰጥበት ጊዜ ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረቢያና መወሰኛ ጊዜ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ የዕጩ ምዝገባ ጊዜ ከሚያዝያ 13 እስከ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚደረግ ሲሆን፣ የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ ከሚያዝያ 27 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡
የዕጩ ምዝገባ ቅሬታና የአቤቱታ ጊዜ ከሚያዝያ 13 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚደረግ ሲሆን፣ የድምፅ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተልን አስመልክቶ ፓርቲዎች ዕጣ የሚያወጡበት ቀን ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሆናል፡፡
የዕጩዎች ዝርዝር ሰኔ 7 2012 ቀን ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ ቦርዱ አስታውቋል፡፡ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ያስታወቀው ቦርዱ፣ የድምፅ መስጫ ቀንና ውጤት ሒደትን አስመልክቶ ለመራጮች መረጃ የሚሰጥበት ጊዜ ከሰኔ 24 እስከ ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ በመሆኑም ዘመቻ ዘመቻ የተከለከለበት የምርጫ ጊዜ ከነሐሴ 6 እስከ ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሆናል፡፡
ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ቀን ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚሆን ገልጾ፣ የምርጫው ውጤት በምርጫ ጣቢያዎች ይፋ የሚደረግበት ቀን ከነሐሴ 10 እና 11 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚሆን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት በምርጫ ክልል ደረጃ ቅድመ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ከነሐሴ 11 እስከ ነሐሴ 15 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ከነሐሴ 11 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚሆን ታውቋል፡፡