Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ በግማሽ ዓመት ግብይቱ ከ17 ቢሊዮን በላይ አስመዘገበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአንድ ወር ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጡ ምርቶችን አገበያይቷል

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት 17.46 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን አገበያየ፡፡ በታኅሳስ ወር ብቻም የ5.12 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 101,948 ቶን ምርቶችን አገበያይቷል፡፡

በአምስት ተከታታይ ወራት ውስጥ ከተከናወኑ ግብይቶች ይልቅ በታኅሳስ ወር ብቻ የተካሄደው የግብይት መጠን ብልጫ መያዙ ታይቷል፡፡ እስከ ኅዳር መጨረሻ በነበሩት አምስት ወራት ምርት ገበያው እንደ ወቅቱ ከ2.7 እስከ 4.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያወጡ ምርቶች ሲያገበያይ ቢቆይም፣ በታኅሳስ ወር ግን ከፍተኛውን የግብይት መጠን ለማስመዝገብ በቅቷል፡፡

ከሐምሌ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩት አምስት ወራት ውስጥ አማካይ ወርኃዊ የግብይት መጠኑ 2.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር የምርት ገበያው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  ይሁንና በታኅሳስ ወር ምርት ገበያው ካገበያያቸው ምርቶች ውስጥ 52,598 ቶን ሰሊጥ፣ 30,416 ቶን ቡና፣ 8,565 ቶን ነጭ ቦሎቄ፣ 8,100 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 1,876 ቶን አኩሪ አተርና 394 ቶን ቀይ ቦሎቄ፣ በ5.12 ቢሊዮን ብር ሲያገበያይ ሰሊጥ ከአጠቃላይ ግብይት 51 በመቶ በመጠንና 44 በመቶ በዋጋ በማስመዝገብ የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡

በታኅሳስ ወር የተካሄደው የጥራጥሬና የቅባት እህሎች የግብይት መጠን ከኅዳር ወር፣ እንዲሁም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር መሻሻል እንደታየበት መረጃዎች አሳይተዋል፡፡ በወሩ ለግብይት የቀረበው 52,598 ቶን ሰሊጥ ለብቻው በ2.24 ቢሊዮን ብር ሲገበያይ፣ የሑመራ ጎንደር ሰሊጥ 90 በመቶውን የግብይት መጠንና የዋጋ ድርሻ በማስመዝገብ ከፍተኛ ድርሻ ይዟል፡፡ የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ34 በመቶ፣ እንዲሁም የግብይት ዋጋው በ26 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ አማካይ ዋጋው በአምስት በመቶ ቀንሷል፡፡ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም የግብይት መጠኑ በ79 በመቶ፣ ዋጋው በ85 በመቶ ከፍ ማለቱንም መረጃው ያመለክታል፡፡  

በተመሳሳይ ሁኔታ 8,565 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ176 ሚሊዮን ብር፣ 8,100 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ270 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ የቦሎቄ ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ171 በመቶና በዋጋ የ183 በመቶ ጭማሪን ሲያስመዘግብ፣ አጠቃላይ ዋጋውም በሦስት በመቶ አድጓል፡፡ የአረንጓዴ ማሾ ግብይትም ካለፈው ወር ጋር ሲተያይ በመጠን 49 በመቶና በዋጋ 63 በመቶ፣ በአማካይ የግብይት ዋጋውም በዘጠኝ በመቶ እንደሆነም ይገልጻል፡፡

በተጠቀሰው ወር ለግብይት የቀረበው 30,416 ቶን ቡና በ2.47 ቢሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና 59 በመቶ የግብይት መጠንና 58 በመቶ የግብይት ዋጋ ሲያስመዘግብ ስፔሻሊቲና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ ቡና ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል፡፡ የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ10 በመቶ፣ የግብይት ዋጋው ደግሞ በ31 በመቶ፣ እንዲሁም አማካይ ዋጋው በ24 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ የቡና ግብይት ካለፈው ኅዳር ወር ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ40 በመቶ የግብይት ዋጋው በ78 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

22 የገበያ ቀናትን ያካተተው የታኅሳስ ወር ግብይት፣ 1,876 ቶን አኩሪ አተር ለግብይት ቀርቦ በ22 ሚሊዮን ብር ግብይት ተፈጽሞበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 42 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ የጎጃም አኩሪ አተር ቀዳሚውን ድርሻ ወስዷል፡፡ ካለፈው ወር አፈጻጸም አኳያ ሲተያይ፣ የአኩሪ አተር ግብይት በመጠን 73 በመቶ፣ በዋጋ 36 በመቶ እንደጨመረ አመላክቷል፡፡  

የምርት ገበያው በየወሩ ይፋ ካደረጋቸው መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው በግማሽ በጀት ዓመቱ ከ17.46 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከ338 ቶን በላይ ምርቶች ማገበያየት መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡     

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበቆሎ ምርትን ከ11 ዓመታት በኋላ ዳግም ለማገበያየት የግብይት ስምምነቱን በማሻሻልና የመጋዘን ብድር አገልግሎት በማቅረብ ዝግጅቱን በማጠናቀቁ፣ የመጀመርያውን ምርት ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በቡሬ ቅርንጫፍ እንደተቀበለ አስታውቋል፡፡

ምርት ገበያው በቆሎን ዳግም ወደ ግብይት ማዕከላቱ ለማስገባት በወሰነው መሠረት፣ ሁለት አቅራቢያዎች 100 ኩንታል በቆሎ ለቡሬ ቅርንጫፍ ማቅረብ ችለዋል፡፡ የምርቱ ናሙና በላቦራቶሪ ተመርምሮ ደረጃ አንድ ምርት እንደቀረበለት  ማረጋገጡን ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡ መበደኛው የበቆሎ ግብይትም በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡ የበቆሎ አቅርቦት እየተሻሻለ ግብይቱም እየተስፋፋ ከመጣ፣ ወደ መጋዘን ገቢ ለተደረገው ምርት በደረሰኝ የብድር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ምቹ አሠራር እንደሚዘረጋለት ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች