Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከሰባት ሺሕ በላይ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ለቀዶ ሕክምና ወረፋ እየተጠባበቁ ነው›› አቶ ሳላዲን ከሊፋ፣ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማኅበር ፕሬዚዳንት

አቶ ሳላዲን ከሊፋ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በማኅበሩ አመሠራረትና በልብ ሕሙማን ሕፃናት ሕክምና ማዕከል እንቅስቃሴ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የልብ ሕሙማን ሕፃናት ሕክምና ማዕከል ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አመሠራረቱን በተመለከተ ማብራሪያ ቢሰጡን?

አቶ ሳላዲን፡- ከማዕከሉ አመሠራረት በፊት ስለ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማኅበር እንቅስቃሴ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተ 30 ዓመት ሆኖታል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለ20 ዓመት ያህል የሠራው ዘውዲቱ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በሚገኘው ኮንቴይነር ውስጥ ነው፡፡ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ደግሞ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ የሚገኘውን የልብ ሕሙማን ሕፃናት ሕክምና ማዕከልን ለማቋቋም በቅቷል፡፡ ማዕከሉ ሊቋቋም የቻለው ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› በሚል መርህ ማኅበሩ ኅበረተሰቡንና አጋር ድርጅቶችን አሰባስቦ ባካሄደው የድጋፍ ወይም የገንዘብ አስተዋጽኦ ዘመቻ ነው፡፡ በዚሁ ዘመቻ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተሠራው ይህ የሕክምና ማዕከል ዓለም የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የተከተለ፣ የወቅቱ ቴክኖሎጂ ባፈራቸውና እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የልብ ቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች ተደራጅቷል፡፡ እያንዳንዱም የመኝታ ክፍል ደረጃውን የጠበቀ ነው፡፡ ማዕከሉ በዓመት ለ1066 የልብ ሕሙማን ሕፃናት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም አለው፡፡ አሁን ግን እየሠራ ያለው ከአቅሙ በታች በዓመት ለ450 ሕፃናት የተጠቀሰውን ሕክምና በመስጠት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአቅሙ በታች አገልግሎት የሚሰጥበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ሳላዲን፡- አቅሙን አሟጥጦ ለመሥራት የተሳነው ወይም ከአቅሙ በታች እንዲሠራ ያደረገው በቀዶ ሕክምና ግብዓቶች አጥረት ሳቢያ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ግብዓቶች በጣም ውድ ከመሆናቸውም በላይ ማዕከሉ እየገዛ ለመጠቀም ደግሞ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ችግር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ የገጠመው ችግር በጣም ከባድ መስሎ ነው የሚታየው ለመሆኑ ይህን ችግር ለመወጣት ምን ዕርምጃ ነው የተወሰደው?

አቶ ሳላዲን፡- ችግሩን ለመወጣት ልዩ ልዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከተደረጉትም ጥረቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከውጭ አገር የሚመጡ በጎ ፈቃደኛ የሕክምና ቡድኖች ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንታት ያህል ነፃ አገልግሎት ከሰጡ በላይ ወደየመጡበት ሲመለሱ የተረፋቸውን የቀዶ ሕክምና ግብዓቶችን ለማዕከሉ ትተው ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች የተረፉትን ግብዓቶች በቁጠባ መልክ እየተጠቀሙ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡ የጤና ሚኒስቴርም የተጠቀሱትን ግብዓቶች አልፎ አልፎ በመጠኑም ቢሆን ከመለገስ ወደኋላ አላለም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነት አካሄድ እስካሁን ስንት የውጭ አገር የበጎ አድራጎት ሕክምና ቡድኖች መጥተው አገልግሎት ሰጡ?

አቶ ሳላዲን፡- እስካሁን የእሥራኤል፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የህንድና የግብፅ ሕክምና ቡድኖች መጥተው ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ከመርዳታቸውም በላይ የተረፋቸውን ግብዓቶች ማዕከሉ እንዲጠቀምበት ተባብረዋል፡፡ ወደፊት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የሕክምና ቡድኖችን ለመጥራት ታስቧል፡፡ በተረፈ ማዕከሉ ሥራውን እንደጀመረ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በውጭ አገር ሐኪሞች ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ መቀጠል እንደሌለበትና የውጪዎቹ በኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች መተካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ 12 ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ወደ ውጪ አገር በመላክ በልብ ሕክምና ስፔሻላይዝድ አድርገው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ 16 አፓርትመንቶች ተገንብተው እንዲከራዩ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ኪራይ የሚገኘው ገቢ ለባለሙያዎች ደመወዝና ለልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች እየዋሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን እንዳወጣችሁ ይነገራል፡፡ ስትራቴጂክ ፕላን ምን ዓይነት ተግባራትን አካትቷል?

አቶ ሳላዲን፡- የተጠቀሰውን ስትራቴጂክ ፕላን ለማስጠናት ስድስት ወራት ፈጅቶብናል፡፡ አሁን ግን ጥናቱ አልቆ ወደ ትግበራ ገብተናል፡፡ በዚህም ፕላን ውስጥ ተካተው በመተግበር ላይ ከሚገኙት መካከል የካርዲያክ ክፍሉን ማጠናከር፣ ተጨማሪ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የማዕከሉን ራዕይና ተልዕኮ በማስቀመጥ ጠንካራ የሆነ የምርምርና ሥልጠና ተቋም እንዲሆን ማድረግ፣ ተመሳሳይ የሆኑ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ሕክምና ማዕከላትን በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እንዲቋቋሙ ማድረግ ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ አገር ሕክምና ቡድኖች አመጣጥ እንዴት ነው? ይህም ማለት ሲፈለጉ ወይም ሲጠሩ ነው የሚመጡት ወይስ በዓመት የተወሰነ ጊዜ አላቸው?

አቶ ሳላዲን፡- የማዕከሉ ሐኪሞች በተለያዩ አገሮች ካሉት ሐኪሞች ጋር ግንኙነት ይፈጥራሉ፡፡ አስፈላጊ ሲሆን ይጋበዛሉ፡፡ ቡድኖቹም ግብዣውንም ወይም ጥሪውን አክብረው ይመጣሉ፡፡ ቡድኖቹ ግን አዘውትረው ለመምጣት ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሐኪሞች በሙያው ላይ የረዥም ዓመት ወይም የተካበተ ልምድና ዕውቀት አላቸው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ደግሞ ጡረታ የሚወጡበት ጊዜያቸውም የተቃረበ ስለሆነ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አላቸው፡፡ በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ፕላን ውስጥ ግን ለአገልግሎት የሚመጡ የውጭ ሕክምና ቡድኖችን የመቀበልና ተገቢውን አገልግሎት ከሰጡ በኋላ በክብር የሚመለሱበትን መንገድ የማመቻቸት ተግባርና ግምገማ መካተቱን መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በአጠቃላይ የአቀባበልና የአሸኛኘት ሥርዓትን ያካተተ ፕሮቶኮል እየተዘጋጀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ድረስ ለመጡና ወደፊትም ለሚመጡ የሕክምና ቡድኖች ወጪያቸውን ማን ነው የሚሸፍነው?

አቶ ሳላዲን፡- ይህን ለመሰለ ጥያቄ እኔ ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት አልችልም፡፡ የሚመስለኝን ግን ማስቀመጥ እችላለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር እንግዳው ቡድን የአውሮፕላን ወጪውን ራሱ ይሸፍናል፡፡ በተረፈ መስተንግዶውን (አኮሞዲሽን) በተመለከተ ደግሞ ማዕከሉ የሚሸፍን ይመስለኛል፡፡ ይህም ሆኖ የሚገቡት ባለ አራት ወይም ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ ሳይሆን ለሥራ ቅርብ ወደሆነው ግዮን ሆቴል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማዕከሉ ቁልፍ ችግር ምንድነው? ይህንን ችግር ለመወጣት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ሳላዲን፡- ማዕከሉ ለልብ ሕሙማን ሕፃናት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በነፃ ነው፡፡ ለቀዶ ሕክምና የሚውሉ ግብዓቶች ደግሞ በጣም ውድ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የማዕከሉ ቁልፍ ችግር የተጠቀሱት ግብዓቶችን ለማግኘት አለመቻሉ፣ ለመግዛት ቢያስብም ከአቅሙ በላይ መሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ተመዝግበው ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ያሉት የልብ ሕሙማን ሕፃናት ቁጥር ከ7000 በላይ ናቸው፡፡ ‹‹የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች›› የሆኑ እነዚህ ሕፃናት ግብዓቶቹ ተገኝተውና ተራቸውም ደርሶ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እስከሚያገኙ ድረስ የሚሞቱም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ በእጅጉ ያማል፡፡ አስፈሪው ሁኔታ ከመከሰቱ አስቀድሞ ኅብረተሰቡ የዕርዳታ እጁን እንዲዘረጋ እንጠይቃለን፡፡ ለዚህም ቀጣይነት ያለው የገቢ ማስገኛ ኩነቶችን ለማከናወን እየንቀሳቀስን ነው፡፡ ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› በሚል መርህ ተነሳስቶ ይህን ግዙፍ ማዕከል ያቋቋመው ኅብረተሰቡ የዕርዳታ እጁ ይታጠፋል የሚል እምነት የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ወይም ጤና ሚኒስቴር የማዕከሉን ችግር ለመቅረፍ ምን እያደረገ ነው?

አቶ ሳላዲን፡- ጤና ሚኒስቴር አላቂ ግብዓቶችን አልፎ አልፎ በተወሰነ መልኩ በመስጠት ይተባበረናል፡፡ በተረፈ ለሦስት ዓመታት ያህል የተጠቀሱትን ግብዓቶች ሊያቀርብልን ቃል ገብቷል፡፡ ከዚህም ሌላ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ስፔሻሊስት ሐኪሞቻችንን በሚኒስቴሩ መዋቅር ውስጥ በማስገባት ደመወዛቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ እንዲያገኙ ወይም እንዲከፈላቸው አድርጓል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆንና ከሚኒስቴሩ የተጻፈ ደብዳቤ ከሁለት ሳምንት በፊት ደርሶናል፡፡ ይህ ዓይነቱም አካሄድ ከፍተኛ ሐኪሞቻችንን በሥራቸው ላይ ለማቆየት ወይም ወደ ሌላ ጤና ተቋም እንዳይከጅሉ አድርጓቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ ማኅበሩ የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት ባከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ የማኅበሩና የማዕከሉ መሥራችና ባለቤት ዶ/ር በላይ አበጋዝ ዕውቅናናና አክብሮት ተችሯቸዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...