Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የፖለቲከኞች ፉክክር በሕጋዊነት ቅጽር ውስጥ ይሁን!

  ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከሩ ተጣማሪና ውህድ ፓርቲዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው መጪው ምርጫ፣ ሃምሳ ሚሊዮን ያህል መራጮች እንደሚሳተፉበት ይታመናል፡፡ ከሃምሳ ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች 300 ሺሕ ያህል የምርጫ አስፈጻሚዎች ሲያስፈልጉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ዕጩዎችን እንደሚያቀርቡ፣ የሲቪክና የዴሞክራሲ ተቋማትም በርካታ ታዛቢዎችን እንደሚመድቡ ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡም ታዛቢዎችን ማሰማራቱ አይቀርም፡፡ ይህ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ዝግጅትና መሰናዶ በሰላም እንዲጠናቀቅ፣ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን መግራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድኅረ ምርጫ ወቅት ሊከተሉዋቸው ለሚገቡ ሥርዓቶች፣ በጋራ ውይይት በሚፀድቅ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ ይገዙ፡፡ ይህ በፖለቲካ ፓርቲዎች ይሁንታ የሚፀድቅ የሥነ ምግባር ደንብ ገዥ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን ደንብና ሌሎች የአገሪቱን ሕጎች በመጣስ የሚፈጸም ድርጊት፣ በፖለቲካ ፓርቲውና በደጋፊዎቹ ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ያስወስዳል፡፡ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው ፖለቲከኞች በሕጋዊነት ቅጽር ውስጥ ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሕጋዊነት የምርጫ ዘመቻ ለመጀመር የሚደረጉ ዝግጅቶችን ጭምር ያካትታል፡፡ ቀደም ሲል መንግሥት የሚወገዝበት ምርጫን በጉልበት የማስፈጸም አባዜ፣ አሁን ደግሞ ትከሻቸውን ወደሚያሳብጡ ፖለቲከኞች ከተሸጋገረ ሕገወጥነት ይንሰራፋል፡፡

  ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ለመጣል ከሚያገለግሉ ሁነኛ መሣሪያዎች አንዱ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ምርጫ ሰላም ይፈልጋል፡፡ በፓርቲዎች መካከል የጋራ የሆነ መግባባት ያሻዋል፡፡ የምርጫ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ለመራጩ ሕዝብ ኃላፊነት ያለበት ነፃነት ማጎናፀፍ አለባቸው፡፡ ተፎካካሪዎች በእኩል ሜዳ ላይ መሠለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሸፍጥና ከመሰሪነት የፀዳ ምኅዳር ሊኖር የግድ ይላል፡፡ መራጩ ሕዝብም ሆነ ተፎካካሪዎች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ኃላፊነታቸውን በነፃነትና በገለልተኝነት መወጣት አለባቸው፡፡ ሚዲያው በሙያው ሥነ ምግባርና በሚዘጋጅለት የምርጫ ሥነ ምግባር መሠረት፣ ሥራውን በነፃነት እንዲያከናውን መደረግ አለበት፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ የጥጋብና የትዕቢት ፉከራዎች፣ ደካማነትን ለመሸፈን የሚደረጉ ሕገወጥነቶች፣ የምርጫውን ጤና የሚያውኩ ግርግሮች፣ ለሕግ የበላይነት ላለመገዛት የሚደረጉ ሥርዓተ አልበኝነቶችና የመሳሰሉት ጋጠወጥ ድርጊቶች ከጥፋት በስተቀር ፋይዳ ቢስ ናቸው፡፡ ሕገወጥነትን በሕጋዊነት ላይ የበላይ ለማድረግ መሯሯጥ ኋላቀርነት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን አይሆንም፡፡

  ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድሏ የሰመረ እንዲሆን መጪው ምርጫ ትልቅ አንድምታ ቢኖረውም፣ በሕግ የማይገራ ባህሪ ይዘው በሚገቡ ኃይሎች መጨናገፉ ግን አይቀሬ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የተሠለፉ ኃይሎች ባህሪ ለሕጋዊነት ያለው ግንዛቤ አናሳ ከመሆኑም በላይ፣ የቀድሞው ጠባሳ ታክሎበት ራስን ለመግራት ያለው ተነሳትሽነትም አስተማማኝ አይደለም፡፡ ተፎካካሪን መናቅና እንደ ጠላት ማየት፣ ደጋፊን በሥርዓት አልበኝነት ማሰማራት፣ ለውይይትና ለድርድር ጀርባ መስጠትና ለዘመናዊው ዓለም የፖለቲካ አመለካከት ባዕድ መሆን ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ከእነዚህ ህፀፆች ራሳቸውን በማፅዳት ለፓርቲ ፖለቲካ ሥራው ራሳቸውን ያበቁ አነስተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ በዚህ ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው ችግሩን ያከፋዋል፡፡ አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎች እንደ ወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ራሳቸውን ስለማያዘጋጁ፣ ከዘመናት ልማዳዊ ድርጊቶች ለመላቀቅ ይከብዳቸዋል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ሳይገባቸው በአፈ ጮሌነት ከተሰማሩት ጀምሮ፣ ፈፅሞ ለሕጋዊነት ዋጋ የማይሰጡ ጀብደኞችም አሉ፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ ለመሥራት ከመሞከር ይልቅ፣ በረባ ባልረባው በመተናነቅ ግጭት ለመቀስቀስ የሚያደቡም አሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለምርጫ ፉክክር ሲቀርቡ ደግሞ፣ ሒደቱን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይቅርና ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አደጋ ይጋብዛሉ፡፡ በነፃነት መደረግ የሚገባውን የምርጫ ፉክክር የጦር ቀጣና ያስመስሉታል፡፡

  የምርጫ ተዋንያን በሕጋዊነት ቅጽር ውስጥ ይሁኑ ሲባል፣ በተቻለ መጠን ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባቸው ማለት ነው፡፡ የአገሪቱን ሕጎች፣ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሕጎች፣ ተያያዥ ደንበኞችንና መመርያዎችን በማክበር አርዓያነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ማንነቶችን፣ እምነቶችንና መሰል ልዩነቶችን በማባባስ ጥላቻ መስበክ አይገባቸውም፡፡ ውጥረት በመፍጠር ግጭት ማስነሳትም ሆነ ማባባስ የለባቸውም፡፡ በተፎካካሪዎቻቸው ፕሮግራሞች፣ አጀንዳዎችና ፖሊሲዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በሰብዕናቸውም ሆነ በማኅበራዊ አመጣጣቸው ላይ ትችት ወይም ነቀፌታ መሰንዘር አይገባቸውም፡፡ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ግጭት ከሚያስነሱ ትንኮሳዎችና ቅስቀሳዎች እንዲታቀቡ ማድረግ አለባቸው፡፡ የእምነት ተቋማትን መሣሪያ ማድረግ ክልክል ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን በስውር የሚቆጣጠሩዋቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አፍራሽ ድርጊት ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌሎች አላስፈላጊ ጉዳዮችን ጨምሮ ለምርጫው መሰናክል የሚሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶችን ማስወገድ አለባቸው፡፡ ምርጫው የሚደረገው የተሻለ ሥርዓት ለመገንባት እስከሆነ ድረስ፣ በተፎካካሪነት ካባ የሕግን ልዕልና መዳፈር ውጤቱ ምርጫውን ማበላሸት ነው፡፡ ለዚህም ነው ካለፉ ስህተቶች በሙሉ በመማር አዲስ ታሪክ ለመሥራት መነሳት የሚያስፈልገው፡፡ ተወደደም ተጠላ የመንግሥት ሥልጣን በሕጋዊ ምርጫ ካልተያዘ ተቀባይነት የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ፍላጎት ከድብቅ ዓላማ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ከግጭትና ከመራር ድህነት ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ የተሻለ ኑሮ ማግኘት ይገባዋል፡፡ ንፁህና ምቹ የመኖሪያ ሥፍራ፣ አስተማማኝ የሆነ ሥራና ገቢ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት መንግሥታዊ ሥርዓት፣ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስረክባት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገር እንድትኖረው የግድ ነው፡፡ ይህንን በተግባር ለማሳየት ደግሞ ሕዝቡ ከልቡ የሚቀበለው ምርጫ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ተዋንያን ይህንን ሕዝብ ማክበር አለባቸው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን በግብርም በነቢብም ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፅ የሚያሰባስቡት ከመራጮች ነው፡፡ ሕዝብ ዘንድ የሚቀርብ ማንኛውም ፓርቲ ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ዓይነት ጨዋነት ሳያሳዩ ተመቸን ብሎ መጋለብ አያዋጣም፡፡ ለእያንዳንዱ ድርጊት ተመጣጣኝ አፀፋ ስለሚኖር፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራው ለሕግ የበላይነት ዕውቅና ሳይሰጥ እንደፈለጉ መሆንን ካስቀደመ፣ ከሌላው ወገን የሚመጣው ምላሽ ከበድ እንደሚል ሊያስቡበት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ብልሹ ምርጫዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይከሰቱ ተጠንቀቁ፡፡ ሕገወጥነት ያተረፈው አምባገነንነትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አምባገነንነት ሰልችቶታል፣ ከሚታገሰው በላይ ሆኖበታል፡፡ ካሁን በኋላ የሚሻው በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ አማካይነት የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ስለሆነ ለፍላጎቱ ተገዙ፡፡ ሕጋዊነትን አጠናክሩ፡፡ በሕጋዊነት ቅጽር ውስጥ ተፎካከሩ! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...