Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማራቶን ሞተርስ አገር ውስጥ የገጣጠማቸውን አዳዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎች ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሁለት ወራት በኋላ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ያስመጣል

ከተመሠረተ አሥር ዓመታት ያስቆጠረው ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ፣ የሃይንዳይ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ከጀመረ ወራት አስቆጥሯል፡፡ ግንባታው አንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፈጀ አዲስ ፋብሪካው የተገጣጠሙ ሦስት አዳዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎችን ለገበያ አቅርቧል፡፡

ሐሙስ ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ገላን አካባቢ በሚገኘው መገጣጠሚያ ፋብሪካ 3,800 የሲልንደር አቅም (ሲሲ) ወይም የፈረስ ጉልበት ያለውንና ‹‹ፖሎሴድ›› የተሰኘውን የቤት አውቶሞቢል፣ 1,300 ሲሲ አቅም ያለውንና ‹‹አቶዝ›› ሞዴል እንዲሁም ‹‹ማይቲ ኤክስ 8›› የተሰኘና 45 ኩንታል የመጫን አቅም ያለውን ተሽከርካሪ ጨምሮ 3‚907 ሲሲ ጉልበት ያለውን ተሽከርካሪ ለገበያ አብቅቷል፡፡

በቀን 36 ተሽከርካሪዎች የመገጣጠም ዕቅድ የያዘው ማራቶን ሞተርስ፣ አዳዲስ ሞዴሎችን ጨምሮ ለገበያ ያስተዋወቃቸውን ተሽከርካሪዎች ከስድስት ወራት በኋላ ለገበያ እንደሚያቀርባቸው የማራቶን ሞተርስ እንጂነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

ማራቶን ሞተርስ እስካሁን ለገበያ ሲያቀርባቸው የቆዩት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በውጭ አገር ተገጣጥመው (Completely Built up) ከሚገቡት ተሽከርካሪዎች ይልቅ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ማቅረብ መሸጋገር በመቻሉ፣ እነዚህኑ ምርቶቹን ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

ማራቶን ሞተርስ

 

ኩባንያው የሃይንዳይ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 12 ሞዴሎችን ለገበያ ማቅረብ የቻለ ሲሆን፣ ‹‹ፖሊሴድ›› የተሰኘው አዲሱ አውቶሞቢል በቴክኖሎጂ ረገድ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚገኝና አዲሱ የሃይንዳይ ምርት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዓለም አቀፍ የሃይንዳይ ኩባንያ በቅርቡ ይፋ ካደረጋቸው ምርቶቹ ውስጥ ፖሊሴድ አንዱ ሲሆን፣ በርቀት መቆጣጠሪያ አማካይነት ሞተሩን ማስነሳት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት፣ የማርሽ እጀታውን ወደሚፈለገው አቅጣጫ በማመላከት ብቻ ማሽከርከር የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተካተተበት ነው፡፡ ሁሉንም የታክስ ወጪዎች ጨምሮ በ6.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ለገበያ እንደቀረበ ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሃይንዳይ የሚታወቅባቸው አቶዝ የተሰኘው ሞዴል በአዲስ መልክ ተሻሽሎ ከመቅረቡም ባሻገር፣ አዲሱ አቶዝ ሞዴል በ850 ሺሕ ብር እንዲሁም 45 ኩንታል የመሸከም አቅም ያለው አዲሱ ‹‹ማይቲ ኤክስ 8›› ሞዴል ተሽከርካሪ በ1.5 ሚሊዮን ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡

የተሽከርሪ ሽያጭ የድንበርና አኅጉራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ያሉት አቶ መልካሙ፣ ለኢትዮጵያ እንግዳና አዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎች እያጥለቀለቋት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከተሻሻለው የኤክሳይስ ታክስ ጋር የተያያዘ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ ከተረጋጋና የተሽከርካሪ ግብዓት በቀላሉ ማስገባት ከተቻለ የመኪና ዋጋ ላይ በሒደት ከ25 እስከ 30 በመቶ ቅናሽ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ከአፍሪካ የመኪና አምራች ድርጅቶች ጋር የንግድ ስምምነት የመፈጸም ዕቅድ እንዳለው የገለጸው ሃይንዳይ፣ የግራ በኩል መንጃ ወይም መሪ ተጠቃሚ ለሆኑ የጎረቤት አገሮች የሃይንዳይ ተሽከርካሪዎችን የማቅረብ ፍላጎት እንዳለውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በኢትዮጵያ በዓመት የ100 ሺሕ የመኪና ገበያ ፍላጎት እንዳለ የተጠቀሰ ሲሆን፣ 85 በመቶ የመኪና አቅርቦት ግን ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች እንደሚሸፈን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ማራቶን ሞተርስ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ከመሸጥ ባሻገር በኢትዮጵያ  የተለያዩ የተሽከርካሪ ግብዓቶችን የሚያቀርቡ ኩባንያዎችን መፍጠር ከተቻለ፣ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ የማቅረብ ዕቅዱን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የነዳጅና የዘይት ማጣሪያ ወይም ፊልተር ለማምረት የሚያስቸለውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ከወራት በፊት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ተሽከርካሪ ለማስመጣት ስለማቀዱ አስታውቆ የነበረው ማራቶን ሞተርስ፣ ይህንን ዕቅዱን ከሁለት ወር በኋላ ተግባር ላይ በማዋል ተሽከርካሪዎቹን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል፡፡

በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ዘይት፣ ጋዝ ወይም ቤንዚን አለመጠቀማቸው ተመራጭ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ በ130 ኪሎ ዋት ኃይል መጓዝ የሚችል መኪና እንደሚያስመጣ አስታውቋል፡፡ በመደበኛው ወይም በ220 ቮልት ኃይል በቤት ውስጥ ለስድስት ሰዓታት ቻርጅ ተደርጎ እስከ 300 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ያለው የኤሌክትሪክ መኪና እንደሚመጣ ሲጠበቅ፣ እንደ ሁኔታው ከአንድ ሰዓት እስከ አሥራ አምስት ደቂቃ ቻርጅ ቢደረግ ከ60 እስከ 70 ኪሎ ሜትር በሰዓት መጓዝ እንሚችል ተነግሯል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪው ምንም ዓይነት የበካይ ጋዝ ወይም የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት የማያስከትል ሲሆን፣ በአዲሱ የኤክሳይስ ሕግ የአምስት በመቶ ታክስ ብቻ ይጣልበታል፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪው ተንቀሳቃሽና 450 ኪሎ ግራም የሚመዝን ባትሪ ተገጥሞለት እንደሚሽከረከር ተብራርቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2019፣ 77 ሚሊዮን ተሽከርካሪ በዓለም ገበያ ላይ ሲቀርብ፣ ከእነዚህ ውስጥ 860 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ለአፍሪካ ገበያዎች እንደቀረቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  እ.ኤ.አ 2009 የተመሠረተው ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ በዓመት 2000 ተሽከርካሪዎች ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች