Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናፓርላማው የሕግ አስከባሪ አካላትና ግለሰቦች የሚታጠቁት የጦር መሣሪያ አያያዝን በሚወሰነው ረቂቅ አዋጅ...

ፓርላማው የሕግ አስከባሪ አካላትና ግለሰቦች የሚታጠቁት የጦር መሣሪያ አያያዝን በሚወሰነው ረቂቅ አዋጅ ላይ ማሻሻያዎችን አድርጎ አፀደቀ

ቀን:

ማንኛውም ሰው በሕግ የተፈቀደ መሣሪያ በሁለት ዓመት ገደብ ውስጥ የማስመዝገብ ግዴታ አለበት

ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በስተቀር ሌሎች በክልል መንግሥታትና በፌዴራል መንግሥት የተደራጁ ሕግ አስከባሪ አካላትና ግለሰቦች እንዲታጠቁ የሚፈቀድላቸውን የጦር መሣሪያ አያያዝ በሚወስነው ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ አፀደቀ።

አዋጁ ለግለሰብ የሚፈቀድ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ማንኛውም ሰው የታጠቀውን መሣሪያ በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያስመዘግብም አስገዳጅ ድንጋጌ ይዟል። የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አዋጅ ሕግ አስከባሪ ለሚለው ቃል ትርጓሜ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ሚሊሻ፣ የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የፌዴራልና የክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋማትና ፍትሕ ቢሮዎች፣ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን መሆናቸው በሕጉ ተመልክቷል።

- Advertisement -

እነዚህ አካላት ሊታጠቁዋቸው የሚችሉዋቸው የጦር መሣሪያ ዓይነቶች ሽጉጥ፣ አውቶማቲክ ያልሆነ ወይም ግማሽ አውቶማቲክ የሆነ ጠብመንጃ፣ ቦምብና ሌሎች ተያያዥ ዕቃዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ ሰባት ሥር ይዘረዝር ነበር።

ለግለሰብ የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ አንድ ሽጉጥ ወይም አንድ አውቶማቲክ ያልሆነ ጠብመንጃ፣ ወይም አንድ ግማሽ አውቶማቲክ ጠብመንጃ ብቻ መሆኑን ረቂቁ ይዘረዝር ነበር። ራሳቸውን ለመከላከልና የአካባቢያቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በተለምዶ የጦር መሣሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑና የጦር መሣሪያ የያዙ ሰዎች፣ የያዙት የጦር መሣሪያ በረቂቅ ሕጉ ለግለሰብ ያልተከተለ የጦር መሣሪያ ዓይነት እስከሆነ ድረስ፣ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ በሚወጣ የጊዜ ሰሌዳ በየአካባቢው ሥልጣን ወደተሰጠው ተቋም በአካል ቀርበው ፈቃድ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውና ለአንድ ሰው የሚፈቀደውም አንድ የጦር መሣሪያ ብቻ እንደሆነ በረቂቁ ተካቶ ነበር።

ነገር ግን የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮማቴ ጋር በመሆን የረቂቁ ይዘቶችን በመመርመርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ሕግ አስከባሪዎችና ግለሰቦች እንዲታጠቋቸው ተብለው በረቂቁ የተለዩ የጦር መሣሪያ ዝርዝሮች እንዲወጡ በማድረግ በሌላ ድንጋጌ እንዲተኩ አድርጓል።

በዚህም መሠረት ለሕግ አስከባሪ ተቋማት የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛት፣ እንዲሁም የጥይት ብዛት በተቆጣጣሪው ተቋም በሚወጣ መመርያ መሠረት ይወሰናል በሚል ድንጋጌ እንዲተካ አድርጓል።

በተመሳሳይም ለግለሰብ የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ ዓይነት ብዛት፣ እንዲሁም የጥይት ብዛት በከተሞች አካባቢ፣ በአርብቶ አደርና አርሶ አደር አካባቢ ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው መመርያ እንዲወስን በማለት ማሻሻያ አድርጎበታል። ‹‹የቁጥጥር ሥርዓቱ ከተቀመጠ መታጠቅ የሚፈቀደውን የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛት፣ እንዲሁም የጥይት መጠን ተቆጣጣሪው ተቋም እንዲወስን ማድረግ የተሻለ ነው፤›› ሲሉ፣ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዳባ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ግን የሚታጠቁትን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና የአጠቃቀም ሁኔታ በራሳቸው ተቋማዊ አሠራር መወሰን እንደሚችሉ አዋጁ ያስረዳል፡፡ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ለመታጠቅና ለመገልገል የሚችሉባቸው የሕግ አግባቦች በአዋጁ ተካተዋል።

በዚህም መሠረት የተሟላ ጤንነት ያለውና የአዕምሮ ሁኔታው የተስተካከለ፣ አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ ሥልጣን ባለው ተቆጣጣሪ ተቋም የታመነበት ዕድሜው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ ያለው ሰው፣ የጦር መሣሪያ የመያዝና የመገልገል ሕጋዊ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የጦር መሣሪያ የመታጠቅ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ምዝገባ፣ መሣሪያውን በሚያስመዘግብበት ወቅት የጣት አሻራውንም እንደሚሰጥ በመሥፈርትነት ተካቷል።

በተለምዶ የጦር መሣሪያ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የጦር መሣሪያ የታጠቁ ነዋሪዎች ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው ግለሰቦች መታጠቅ ስለሚችሉት የመሣሪያ ዓይነት መመርያ መሠረት፣ አዋጁ በፀደቀ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቋሙ በአካባቢው ተገኝቶ በሚያስቀምጠው የጊዜ ሰሌዳ በአካል ተገኝተው ፈቃድ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል።

የጦር መሣሪያ ለመታጠቅ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ፈቃድ ከተሰጠው ክልል ውጪ ባሉ የክልልና ትልልቅ ከተሞች የጦር መሣሪያውን ለሕዝብ እንዲታይ አድርጎ ታጥቆ እንዳይንቀሳቀስ አዋጁ ይከለክላል።

የፀጥታ አስከባሪ ተቋም አባላት የጦር መሣሪያ የሚይዙት በተቋማቸው ለሥራቸው አላስፈላጊ ሆኖ ሲሰጣቸው እንደሆነ የሚገልጽ ረቂቅ ድንጋጌ የሕግ ሰነዱ የያዘ ሲሆን፣ እነዚህ የሕግ አስከባሪ አባላት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የተቋማቸውን የደንብ ልብስ መልበስ ወይም ፈቃዳቸውን ወይም እንደ አግባብነቱ የሥራ መታወቂያ ወረቀት መያዝ እንደሚኖርባቸውም ያመለክታል።

የሕግ አስከባሪ ተቋማቱ አባላቶቻቸው የጦር መሣሪያ እንዲይዙ የሚፈቅዱት ተቋማትን ለመጠበቅ፣ የሕግ ማስከበር ሥራ ወይም ኦፕሬሽን ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ፣ የኃይል ተግባር ሊያጋጥም ይችላል በሚል እምነት ለሥራ ሲሰማሩ፣ ለራስ መጠበቂያ ያስፈልጋቸዋል በሚል ምክንያት እንዲታጠቁ ሲያስፈልግ ብቻ እንደሆነም የአዋጁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ በባህሪያቸው ጉዳት አድራሽ ናቸው ያሏቸውን ባህላዊ የጦር መሣሪያዎች ማለትም ገጀራ፣ ሜንጫ፣ ጦርና ቀስት በአዋጁ ውስጥ እንዲካተቱ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ባህላዊ መሣሪያዎች አርሶ አደሮች ለማምረቻነት የሚጠቀሙባቸው ስለሆነ መሣሪያዎቹን ለማምረቻነት መጠቀም እንደሚቻል፣ ነገር ግን ሆን ተብሎ ለግጭት ጥቅም ላይ ለማዋል በብዛት እንዳይመረቱ፣ ወደ አገር እንዳይገቡና እንዳይዘዋወሩ ክልከላ ተጥሎባቸዋል።

በእነዚህ መሣሪያዎች ላይ የተጣለው ክልከላ በዋናነት ምክር ቤቱን ያከራከረ ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ በአጠቃላይ አዋጁ ላይ በተሰጠው ድምፅ አዋጁ በአራት ድምፀ ተዓቅቦና በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...