Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ግብፅ የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል ፍላጎት እንዳላት ነው ለእኛ የሚገባን›› ...

‹‹ግብፅ የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል ፍላጎት እንዳላት ነው ለእኛ የሚገባን›› ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር

ቀን:

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የታላቁ የህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ ሲያካሂዱት የቆየው የቴክኒክ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የሚሰጠው ትርጉም፣ ግብፅ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል ካልሆነም ግድቡ በተገቢ ዓመታት ውስጥ በውኃ እንዳይሞላ ፍላጎት እንዳላት ነው ሲሉ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ለዘጠነኛና ለመጨረሻ ዙር በአዲስ አበባ ያካሄዱት የቴክኒክ ውይይት ሐሙስ ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ያለ ስምምነት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ይኼንንም ተከትሎ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ሲካሄዱ በቆዩት የቴክኒክ ውይይቶች ያልተነካና ያልተመነዘረ የቴክኒክ ችግር እንዳልነበረ፣ በዚህም በሦስቱም ወገኖች በተለይም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የነበረው የቴክኒክ ልዩነት በጣም ከመጥበቡ የተነሳ ለመስማማት የሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሶ እንደነበር አስረድተዋል። ነገር ግን ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻሉንና በግብፅ ወገን ውሳኔ ለመስጠት የሚችለው አካል በዚህ ድርድር ውስጥ አለመኖሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

- Advertisement -

‹‹በዚህ መንገድ መስማማት ካልተቻለ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል አመለካከት ግብፆች እንዳላቸው ነው ለእኛ የሚገባን፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ግድቡ በተገቢዎቹ ዓመታት ውስጥ እንዳይሞላ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ብለዋል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚህ የመጨረሻ የቴክኒክ ውይይት ቀድሞ ስምምነት ተደርሶበት ከነበረው በተለየ፣ ግድቡ ከ12 እስከ 21 ዓመታት እንዲሞላ የሚያደርግ የጊዜ ሰንጠረዥ ግብፅ ማቅረቧን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የዓባይ ውኃ የተፈጥሮ ፍሰት መጠበቅ እንዳለበት በድጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህ ማለት በኃይድሮሎጂ ዘርፍ (በውኃ ምህንድስና) የሚይዘው ትርጓሜ፣ የዓባይን የውኃ ፍሰት የሚያስተጓጉል ማናቸውም ዓይነት መሠረተ ልማት ሊኖር አይችልም እንደ ማለት መሆኑን አመልክተዋል። ነገር ግን የግብፅ ተደራዳሪዎች እንደዚያ ማለታቸው እንዳልሆነና ግድቡንም እንደማይቃወሙ ይገልጹና ይህንኑ በጽሑፍ እንዲገልጹ ሲጠየቁ፣ ተፈጥሮአዊ ፍሰቱ መጠበቅ አለበት ከሚለው ውጪ በወረቀት ላይ እንደማያሰፍሩ አስረድተዋል።

‹‹ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ ተስማማች ማለት የአሁኑንም የወደፊቱንም ትውልድ ጥቅም አሳልፎ እንደ መስጠት ነው። ይህ የማይታሰብ ነው፤›› ብለዋል። ግድቡ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ማን ነው ኦፕሬት የሚያደርገው (የሚያስተዳድረው) የሚል ጥያቄ ከአንድ የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኛ ለሚኒስትሩ ቀርቦላቸው የነበረ ሲሆን፣ ሚኒስትሩም መገረምና ግራ መጋባት በተቀላቀለበት ስሜት ውስጥ ሆነው፣ ‹‹ይህ የእኔ ግድብ ነው! የእኔን ግድብ ማን ሊያስተዳድረው ይችላል?›› ሲሉ ለጥያቄ አቅራቢዋ ጥያቄ አዘል ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥያቄ ያቀረበችው ጋዜጠኛም በግብፅ በኩል ግድቡን የማስተዳደር ፍላጎት ከዚህ ቀደም ሲንፀባረቅ የነበረ በመሆኑ ምናልባት በቴክኒክ ድርድሩ ወቅት ተነስቶ እንደሆነ በማሰብ ያነሳችው መሆኑን በመጥቀስ፣ ለሚኒስትሩ ጥያቄ ያዘለ ምላሽ በድጋሚ ሰንዝራለች። እንዲህ ዓይነት ሐሳብም ሆነ ጥያቄ በቴክኒክ ድርድሩ ወቅት ከግብፅ ወገን አለመነሳቱን ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ የግድቡ ባለቤት ግድቡን እንደሚያስተዳድር ነገር ግን ይህንን በሚያደርግበት ወቅት ከታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር መረጃ በመለዋወጥ፣ በትብብርና ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚያስችሉ የመፍትሔ ሥልቶችን በመጠቀም እንደሚሆን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን በቴክኒክ ድርድሩ ስምምነት የተደረሰባቸውንና ልዩነት የታየባቸውን ጉዳዮች በመለየት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት እንደሚያቀርብ፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች የበኩላቸውን ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚሰጡበት እምነታቸው መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይና የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትና የአሜሪካ ትሬዥሪ ኃላፊ እስካሁን በነበረው የቴክኒክ ውይይትና ምክክር ውጤት ላይ በቀጣዩ ሳምንት መጀመርያ በአሜሪካ እንደሚወያዩም ገልጸዋል።

ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን ይህንኑ የቴክኒክ ውይይት በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በወንዙ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን የማስከበር፣ እንዲሁም የመጪውን ትውልድ የመጠቀም መብት የማረጋገጥ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቋል፡፡

 በማከልም ኢትዮጵያ በናይል (ዓባይ) ወንዝ ላይ ለተፈረሙና አባል ላልሆነችባቸው የቅኝ ግዛትና ድኅረ ቅኝ ግዛት ኢፍትሐዊና አግላይ፣ እንዲሁም ለናይል ወንዝ 77 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለምታበረክተው ኢትዮጵያ ዜሮ ድርሻ ለሚሰጡ ‹‹ውሎች›› ዕውቅና እንድትሰጥ የሚደረጉ ሙከራዎችን እንደማትቀበል አስታውቋል፡፡

ነገር ግን ከተፋሰሱ አገሮች ጋር በሚደረግ ውይይት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትብብርና የጋራ ልማት ምሳሌ እንዲሆን በወንድማማችነት፣ በቅን ልቦናና በመተባበር መንፈስ ለመሥራት ኢትዮጵያ ጥረቷን እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አክሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...