Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር ባለሀብቶችን በማስተባበር ከ224 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የዘመናዊ መንደሮች...

የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለሀብቶችን በማስተባበር ከ224 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የዘመናዊ መንደሮች ግንባታ እያስጀመረ ነው

ቀን:

በመንደሮቹ 500 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገር ውስጥና የግል ባለሀብቶችን በማስተባበር፣ እንዲሁም ከፊል ድርሻ በመያዝ ከ224 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ዘመናዊ መንደሮች ግንባታ እያስጀመረ ነው።

 ግንባታቸው በተጀመሩና በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ይፋ በሚደረጉ በእነዚህ ዘመናዊ መንደሮች ውስጥ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አቅም ያገናዘቡና ቅንጡ የሚባሉ፣ በጥቅሉ 500 ሺሕ መኖሪያ ቤቶች መካተታቸውን ሪፖርተር ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

- Advertisement -

ባለፈው ኅዳር ወር ግንባታው ከተጀመረው የለገሃር ዘመናዊ መንደርና በቅርቡ የግንባታ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለለት ጎተራ አካባቢ ከሚገነባው አሚባራ ፕሮፐርቲ ሲቲ ሴንተር ከተባለው ዘመናዊ መንደር በተጨማሪ፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ተመሳሳይ የዘመናዊ መንደር ግንባታ ፕሮጀክቶች ይፋ እንደሚደረጉ ታውቋል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ወስጥ አንዱ በጉራጌ ተወላጅ ባለሀብቶች የሚገነባ ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪውም 1.6 ቢሊዮን ዶላር (51.2 ቢሊዮን ብር) እንደሚሆን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ይህ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት ግንባታ የሚከናወነው ቀደም ሲል ድርና ማግ ተብሎ በሚታወቀው ወይም በተለምዶ ቫቲካን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

ባለሀብቶቹ በ6.8 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ግንባታ ለማከናወን ያቀዱ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ከዚህ ፕሮጀክት ጋር የሚያያዝ አምስት
ሔክታር በመጨመር በጋራ የሚያለሙት መሆኑ ታውቋል። ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ ከሁሉም የላቀ የኢኮኖሚ ዞን፣ የመኖሪያና የመዝናኛ መንደርን የሚያካትት የልዩ መንደር ግንባታ ይፋ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ይኼንን ፕሮጀክት በሚስጥር የያዘው ቢሆንም፣ በአንድ የቻይና ኩባንያ በ3.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም በወቅታዊ የባንክ የምንዛሪ ተመን መሠረት በ112 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ እንደሆነ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) በተገኙበት፣ ቅዳሜ ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. የግንባታ ማስጀመር ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነው የአሚባራ ዘመናዊ መንደር በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።

 ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታዋቂው የአፋር ባለሀብት ሐጂ አቡዱለጢፍ ዑመር ድርጅት የሆነው አሚባራ የእርሻ ልማትና ሌሎች እህት ድሮጅቶችን አካቶ በልጆቻቸው የሚመራው ኩባንያ፣ ጎተራ አካባቢ በሚገኘው 35 ሺሕ ካሬ ሜትር የቀድሞ ይዞታቸው ላይ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ተጨማሪ 15 ሺሕ ካሬ ሜትር በማግኘት፣ በአጠቃላይ በ50 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባ ፕሮጀክት ነው።

አሚባራ የተባለው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር በውስጡ ከ450 በላይ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን ጨምሮ የገበያ ማዕከላት፣ ሆቴል፣ ተመራጭ የመዝናኛና የንግድ ማዕከል፣ አረንጓዴ ሥፍራዎችና የአፋር ባህል ማዕከልን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስድስት ዓመታት ሊፈጅ ይችላል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ ከአሥር ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘው የለገሃር ዘመናዊ መንደር ደግሞ 50 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ እየተከናወነ ነው፡፡ ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑም ቤት ፈላጊዎች በዚህ ፕሮጀክት የመጀመርያ ምዕራፍ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶችን ለመግዛት፣ ከተያዘው ሳምንት መጀመርያ አንስቶ መመዝገብ እንደሚችሉ ኩባንያው በድረ ገጹ በማስተዋወቅ ላይ ነው።

ለገሃር የተቀናጀ የመኖሪያ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ሥፍራ ልማት የሚል መጠሪያ የያዘው ይህ ፕሮጀክት፣ የለገሃርን ታሪካዊ ገጽታዎች ይዞ በ36 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።

በዚህ ፕሮጀክት ለገበያ የሚቀርቡ 4,000 መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ግዙፍ የንግድ ማዕከላት፣ መጋቢና ዋና መንገዶችና ሌሎች ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫዎችም ሥፍራዎችም ተካተዋል። ከዚህ ውጪ ለፕሮጀክቱ ሲባል ከአካባቢው እንዲለቁ ለተደረጉ 1,600 ነዋሪዎች በ1.8 ቢሊዮን ብር የሚገነቡ ቤቶች ይገኙበታል።

ፕሮጀክቱ ለ25 ሺሕ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይገመታል። በሪል ስቴት የልማት ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የዱባይ ኤግል ሂልስ ኩባንያ በለገሐሩ የዘመናዊ መንደር ፕሮጀክት ላይ ትልቁ ባለድርሻ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ 27 በመቶ ድርሻ በመያዝ በጋራ የሚያለሙት ነው።

የኤግል ሂልስ ሊቀመንበር መሐመድ አልባረ ‹‹እንደ አንዷ የአፍሪካ ዕንቁዎች ኢትዮጵያ በባህል፣ በታሪክና በተፈጥሮ ውበት የበለፀገች ነች፡፡ ስለዚህ የእኛ ፍላጎት እንዲህ ውብ ከሆኑ የአገሪቱ ትሩፋቶች አንዱ የሆነውን በአዲስ አበባ የለገሃር አካባቢን አልምቶ፣ ዓለም እንዲያውቀውና ሰዎች ከተለያየ የዓለም ክፍል ኢትዮጵያን መዳረሻቸው አድርገው ሁሉ ነገር የተሟላለት መንደር መኖር፣ መዝናናትና መገብየት እንዲችሉ ማድረግም ጭምር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ይህ ፕሮጀክት ለአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የአገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ የማነቃቃት ሰፊ ሚና ይኖረዋል፤›› ሲሉ ግንባታው ከወራት በፊት በይፋ በተጀመረበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ (ኢንጂነር) የአሚባራ ዘመናዊ መንደር ግንባታን ባስጀመሩበት ወቅት፣ ‹‹በቀጣይ ደግሞ ከጉራጌ ወንድሞቻችን ጋር፣ ከሶማሌ ወንድሞቻችን ጋር የምንጀምራቸው ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ይኖራሉ፤›› ብለዋል።

‹‹የእነዚህ ፕሮጀክቶች ዓላማ አዲስ አበባ የሁላችንም ስለሆነችና ይህንንም ከቃል ባለፈ ተግባር ማረጋገጥ ስለምንፈልግ ነው። ሌላው ዓላማ በጀመርነው የለውጥ ጉዞ ውስጥ ለግል ባለሀብቶች የምንሰጠው ቦታ ጉልህ መሆኑን ከቃል ባለፈ ለማረጋገጥ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...