Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከፊል መቋጫ ያገኘው የባለ ልኳንዳዎች አቤቱታ

ከፊል መቋጫ ያገኘው የባለ ልኳንዳዎች አቤቱታ

ቀን:

ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ሊከበር፣ ሊበረታታና በእንቅስቃሴው ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችና ተግዳሮቶች ሊወገዱለት ይገባል፡፡ ይህም የሚሆነው በውይይት፣ በጋራ መግባባት፣ በሰከነ መንፈስና በመደማመጥ ላይ በተመሠረተ አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች የተጨማሪ እሴት ታክስና የቁም እንስሳት ግብይት ሥርዓትን አስመልክቶ በተከሰቱባቸው ልዩ ልዩ ችግሮች ዙሪያ ያተኮረ ምክክር ሰሞኑን አካሂደው ነበር፡፡

በስብሰባው ላይ ነጋዴዎቹ ደርሶብናል ያሏቸውን ችግሮች አንፀባርቀው ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡ ከተንፀባረቁት ችግሮቻቸው መካከል ዋነኛው ነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በወጣውና እስካሁን ሲሠሩበት በቆየው መመርያ መሠረት በ2011 በጀት ዓመት ከተጨማሪ እሴት ታክስ የሰበሰቡትን ገንዘብ ግብር አስገቢው መሥሪያ ቤት ለመረከብ ፈቃደኛ አለመሆኑ ይገኝበታል፡፡ ፈቃደኛ ያልሆነበትም ምክንያት ተጨማሪ እሴት ታክስ የመታወቂያ ቁጥር 138/2010 ዓ.ም. በግምት ለመወሰን በወጣው አዲሱ መመርያ መሠረት አልተከናወነም በሚል ነው፡፡

በአዲሱ መመርያ መሠረት ባለመሰብሰቡም፣ ገቢውን ባለመረከብ ብቻ ሳይወሰን የንግድ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ የሚያስችል ክሊራንስ እንደማይሰጣቸው፣ እስካሁን ድረስ ገቢ ያላደረጉትን ልዩነት ሁሉ ከመክፈል እንደማይድኑ ከግብር አስገቢው መሥሪያ ቤት ተነግሯቸዋል፡፡ ልኳንዳ ነጋዴዎቹ ደግሞ አዲስ መመርያ ስለመውጣቱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ የነገራቸውም ሆነ ያሳወቃቸው አካል አለመኖሩንና ለእነርሱም እንግዳ ነገር እንደሆነባቸው አመልክተዋል፡፡

- Advertisement -

እንደ ልኳንዳ ነጋዴዎቹ፣ መመርያውን ያወጣው መንግሥታዊ አካል አንድ ዓመት ሙሉ ሳያሳውቃቸው በመቅረቱ ተጠያቂ መሆን ሲገባው፣ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ምንም የማያውቀው የልኳንዳ ነጋዴ መሆኑ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ልኳንዳ ቤቱን እንዲዘጉ፣ የሚያስተዳድሯቸውን ሠራተኞች እንዲበትኑና እነርሱም ከነቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲጋለጡ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የቁም እንስሳት ግብይት ሥርዓቱም የሕገወጦች መፈንጫ፣ ደላሎች፣ ገልባጮች (የንግድ ፈቃድ ያለው ነጋዴ በአግባቡ የገዛውን ሠንጋ እየተረከቡ ባሰኛቸው ዋጋ የሚሸጡ) እና ሕገወጥ ደረሰኝ አዟሪዎች እንደ ልብ የሚንቀሳቀሱበት ማዕከል መሆኑ ደግሞ ችግሮቻቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው ነው ልኳንዳ ነጋዴዎች የተናገሩት፡፡ በተለይ ገልባጮች ለሸጡት ሠንጋ ደረሰኝ ሲጠየቁ፣ ‹‹ብትፈልግ እንዲሁ ግዛ ካልፈለግክ ተወው›› በሚልና እብሪት የተሞላበት መልስ እንደሚሰጧቸው፣ አልፎ አልፎ ደረሰኝ ቢሰጡም ሕጋዊነት የሌለውና ተቀባይነት የማይኖረው መሆኑን ነው በስብሰባው ላይ የገለጹት፡፡ ደላላው ከአንድ ሠንጋ ለአሻሻጠበት እስከ 300 ብር የሚጠይቃቸው ሲሆን፣ ይህም ካልተከፈለው ልካንዳ ነጋዴው እንዳይሸምት ልዩ ልዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል፡፡ ዛቻና ድብደባም ይከተለዋል፡፡ ገበያ ውስጥም እንዳይገባ ለማድረግ የሚያስችል ልዩ ልዩ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩበት ከታዳሚ ነጋዴዎች በተሰነዘረው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ልኳንዳ ነጋዴዎቹ ያንፀባረቋቸው ችግሮች የቆዩና ሥር የሰደዱ በመሆናቸው የተነሳ በአንድ ጊዜ ለመፍታት እንደማይቻል ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ስለሆነም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀየስ ግድ ሆኗል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቀረቡትና የስብሰባው ታዳሚዎች ያለምንም ተቃውሞ ከተቀበሏቸው ከእነዚህ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል ለመጀመርያ ጊዜ ዕውን የሚሆነው የአጭር ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡

ይህም አቅጣጫ ልኳንዳ ነጋዴዎቹ ነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በወጣው መመርያ መሠረት በ2011 በጀት ዓመት የሰበሰቡትን ተጨማሪ እሴት ታክስ ለግብር አስገቢው መሥሪያ ቤት ገቢ እያደረጉና የንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ሥራ የሚከናወነው ከታኅሣሥ 23 ቀን እስከ ታኅሣሥ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት ነው፡፡

ከንግድ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሕጎ፣ ደንቦችና መመርያዎችን የንግድ ማኅበረሰቡ እንዲያውቃቸው እንዲገዘባቸውና ከዕለት ተዕለት ሥራው አንደ አንዱ አካል አድርጎ እንዲያያቸው ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት በመንግሥት በኩል የሚጠበቅ፣ እንዲሁም ችግር በሚታዩባቸው የሕግ አንቀጾች ዙሪያ የንግድ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር በመቆም እልባት መሻት የመካከለኛው የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሆነ ነው የተጠቆመው፡፡

ሥር የሰደደ ችግር የሚታይበትን የቁም እንስሳት ግብይት ሥርዓት በሕግ ማዕቀፍ ለማስገባት፣ የተጠቀሱትን ሕገወጦች እንቅስቃሴ ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት አማራጭ የሌለው የረዥም ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫ ሲሆን ለተግባራዊነቱም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ባለሥልጣን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ፣ የፖሊሲ ኮሚሽን፣ የፀጥታና የሰላም ቢሮና የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር በጋራና በቅንጅት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ነው የተጠቆመው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማው ገብረ ሥላሴ ‹‹በቁም እንስሳት ግብይት ሥርዓት ውስጥ ሠንጋ በግምት ተገዝቶ ምርቱ በኪሎ ሲሸጥ ይስተዋላል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ሲባል የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

በአንዳንድ የግብር አዋጆች ላይ ክፍተት ከታየ በሥርዓቱና በአግባቡ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ችግሩ ተለይቶ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ እንዳወቅ አብቴ (ኢንጂነር) ‹‹የብልፅግና መርህ መልካም አሠራሮችን ወይም አካሄዶችን መያዝ፣ ችግሮችና ስህተቶች ካሉ ደግሞ ለይቶና ከሕዝቡ ጋር ተወያይቶ መፍትሔዎችን በጊዜና በቦታ ከፋፍሎ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላትን የማቋቋሙ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አለመሆኑን ምክትል ከንቲባው አመልክተው ልኳንዳ ነጋዴዎች ዘመናዊ የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከልና የቄራዎች ድርጅት ለማቋቋም ከፈለጉ አስተዳደሩ ከጎናቸው እንደሚቆም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ በ2006 ዓ.ም. በወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ አፈጻጸም መመሪያ ላይ ማኅበሩ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸው አሁንም በሚከናወን የማሻሻያ ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን በገንዘብና በዕውቀት ለማሳደግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...