Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለረቂቅ ሕጎች በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች ተሳታፊዎች አለመገኘታቸው ፓርላማውን አሳሰበው

ለረቂቅ ሕጎች በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች ተሳታፊዎች አለመገኘታቸው ፓርላማውን አሳሰበው

ቀን:

የተመሩለትን ሕጎች በወቅቱ ለማፅደቅ ተቸግሯል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋነኛ ተግባሩ የሆነውን ሕግ የማውጣት ኃላፊነት የማኅበረሰቡን ጥቅም በሚያስከብርና አሳታፊ በሆነ መንገድ ለመወጣት በሚያዘጋጃቸው ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ላይ፣ ተሳታፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተገኙ አለመሆናቸው አሳሳቢ ሆኖበታል።

ችግሩን በተመለከተም አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች መወያየታቸውን ሪፖርተር አረጋግጧል።

- Advertisement -

በምክር ቤቱ የአባላትና የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ አንቀጽ 100፣ “ምክር ቤቱ አስፈላጊ ናቸው በሚላቸው ጉዳዮች ላይ ዜጎችና የተለያዩ አካላት እንዲሳተፉ ያደርጋል፤የሚል ድንጋጌ የተቀመጠ ሲሆንበአንቀጽ 101 ሥር ደግሞ ዜጎችና የተለያዩ አካላት የሚሳተፉባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ደንግጓል።

በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሰውም በሕግ አወጣጥ ሒደት ዜጎችና የተለያዩ አካላት እንዲሳተፉ ማድረግ ሲሆን፣ የወጡ ሕጎችን አፈጻጸምና ያስገኙትን ውጤት፣ የበጀት ማፅደቅ ሒደትን፣ የበጀት አፈጻጸምና ያስገኘው ውጤትንና የኦዲት ግኝትን በተመለከተ ዜጎችና የተለያዩ አካላት ሊሳተፉባቸው ይገባል ተብለው ከተለዩት ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

 የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመሩላቸውን የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች በዝርዝር ለመመርመር በሚዘጋጇቸው ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተው አስተያየት እንዲሰጡ ይፋዊ በሆነ መንገድ በደብዳቤ ጥሪ እንደሚያደርጉ፣ እንዲሁም ይመለከተኛል የሚሉ ማናቸውም ግለሰቦችና የማኅበረሰብ ክፍሎች መገኘት እንዲችሉ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያን ጨምሮ ተደራሽ በሆኑ ልዩ ልዩ የመገኛ ዘዴዎች የጥሪ ማስታወቂያ ቢያስነግሩም፣ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ተሳታፊዎች እየተገኙላቸው አይደለም።

በዚህ የተነሳም የውይይት መድረኮቹ እየታጠፉ ተጨማሪ ጥሪዎች ተደርገው በሌላ ጊዜ መድረኮቹ እንዲካሄዱ አማራጭ መፍትሔ ቢወሰድም፣ የሚፈለገውን ውጤት እያስገኘላቸው አይደለም።

ለአብነት ያህል ፓርላማው በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ከአስፈጻሚው አካልቀረበለትን አዲሱን የፀረ ሽብር ረቂቅ አዋጅ በመጀመሪያ ንባብ ተመልክቶ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶ የነበረ ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴውም ረቂቅ አዋጁን ለመመርመር ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ቢጠራም የተገኙ ተሳታፊዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።

በዚህም የተነሳ ተዘጋጅቶ የነበረው መድረክ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ቋሚ ኮሚቴው ወስኖ፣ በወቅቱ የመጡትን ተሳታፊዎች እንዲመለሱ አድርጓል። በመቀጠል ተደጋጋሚ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኃን በማስነገር፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የፀጥታ መዋቅሮች ኃላፊዎችን ጨምሮ ደብዳቤ በመላክ ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀውዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቢያደርግም፣ በተጠቀሰው ቀን የተገኙት አንድ ግለሰብ ብቻ ነበሩ።

ለሁለተኛ ጊዜ በተጠራው ሕዝባዊ መድረክ ላይ ለመሳተፍ የተገኙትን አንድ ግለሰብ በማክበር፣ በረቂቅ የፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ያሏቸውን ጥያቄና አስተያየቶች እንዲያነሱና በአስረጂነት ከተጋበዙት አዋጁን ያረቀቁ ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው አድርገናል፤ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበበ ጌዴቦ፣ የፀረ ሽብር አዋጁ ባለፈው ሳምንት በምክር ቤቱ በፀደቀበት ወቅት ረቂቁን ለመመርመር የታለፈበትን ውጣ ውረድ ለምክር ቤቱ አጋርተዋል።

በምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በዝርዝር እንዲታይ ለቋሚ ኮሚቴ የተመራ ረቂቅ አዋጅ አስቸኳይ ሁኔታዎች አለመኖራቸው ተገልጾ በአፈ ጉባዔው ተጨማሪ ጊዜ ካልተፈቀደ በስተቀር፣ 20 ቀናት ውስጥ ተጠናቆ መፅደቅ ይገባዋል።

 በግንቦት ወር መጨረሻ ለቋሚ ኮሚቴው የተመራው ረቂቅ የፀረ ሽብር አዋጁ በዚያው ዓመት መፅደቅ የነበረበት ቢሆንም፣ ከላይ በተገለጸው እክል ምክንያት ወደ ዘንድሮ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

ቋሚ ኮሚቴው የገጠመውን ችግር በተመለከተ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጋር ባደረገው ምክክር የሕግ አወጣጥ ሒደቱ እስከተቻለው ድረስ የሕዝብ ተሳትፎን ያረጋገጠ ሊሆን እንደሚገባው፣ በመሆኑም ተደጋጋሚ ጥረቶችን በማድረግ ተሳትፎውን መመለስ እንደሚገባ በመተማመን ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት፣ በመጠኑ የተሻለ ተሳታፊ በመገኘቱ ውይይቱን አካሂዷል።

የሕዝብ ተሳትፎን መጨመሩ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ተጨማሪ፣ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ለአራተኛ ጊዜ ታኅሳስ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄዱንም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበበ ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠመው፣ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ ገልጸዋል።

 2011 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ ለምክር ቤቱ የቀረበው የጦር መሣሪያ አያያዝና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴው ቢመራም፣ ረቂቁን ለመመርመር በተዘጋጀው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በተሳታፊ ድርቅ በመመታቱ ረቂቁን በዝርዝር የመመልከት ሒደት ላይ እክል መፍጠሩን፣ ሐሙስ ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለተካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ገልጸዋል።

 ከተጠቀሱት አዋጆች በተጨማሪ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅም፣ ተመሳሳይ እክል ከገጠማቸው መካከል ተጠቃሽ ነው።

በደብዳቤ ጥሪ ተደርጎላቸው ያልተገኙ የመንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት ምክንያታቸውን እንዲገልጹ በመጠየቅና ተደጋጋሚ ጥሪ በማድረግ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎውን መመለስ ያለው ብቸኛ መፍትሔ መሆኑ ታኅሳስ 23 ቀን በነበረው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።

በማግሥቱ ዓርብ ታኅሳስ 24 ቀን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም በክልል መንግሥታት መካከል የሚደረግ ግንኙነት በተቋማዊ ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ ለምክር ቤቱ የቀረበውን የመንግሥታት ግንኙነት ረቂቅ አዋጅን ለመመርመር የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዘጋጅቶት በነበረው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ላይም ተሳታፊ ባለመገኘቱ ውይይቱ ተበትኗል፡፡

የዚህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አበበ የችግሩ ምንጭ ምን ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣የትኛው ረቂቅ ሕግ በአገር አስተዳደር ላይ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ካለመገንዘብ የመነጨ ሊሆን ይችላል፤የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

 ይህንንም ለማስረዳት ባለፈው ሳምንት ሕዝባዊ ውይይት የተደረገበት የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ በምክር ቤቱ ታሪክ ግንባር ቀደም ሊሆን የሚችል እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተሳታፊ መገኘቱን፣ እንዲሁም እሳቸው የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴ በጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል በተረቀቀው አዋጅ ላይ ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው መድረክ ላይ በርከት ያሉ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን በማሳያነት ጠቁመዋል።

 ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካና አስተዳደር ጉዳዮች ባለሙያ፣ከሕዝብ ወገን የሚነሳን ምክንያታዊ ተቀባይነት ያለው ጥያቄ ተቀብሎ በገዥው ፓርቲ ደረጃ አቋም በተያዘበት፣ ፖለቲካና ፖለቲካዊ ትርጉም ባላቸው ኢኮኖሚ ነክ ረቂቅ አዋጆች ላይ ፓርላማው ማስተካከያ አድርጎ ያውቃል ወይ?” በማለት፣ ይህ ጉድለት ጎልቶ በሚታይበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ከሕዝብ ወገን ተሳታፊ አለመገኘቱ ሊገርም አይገባም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ አንዱ የችግሩ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል የሚስማሙት ባለሙያው፣ ይህ ግን የችግሩ አንድ ሰበዝ እንጂ አጠቃላይ ምንጭ እንደሆነ ተደርጎ ሊደመደም እንደማይቻል፣ በመሆኑም ምክር ቤቱ በጥልቀት ወደ ውስጡ ሊመለከት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...