Thursday, June 1, 2023

የፖለቲካ ፓርቲዎች አዳዲስ ጥምረቶችና የቀጣይ አገር አቀፍ ምርጫ ፉክክሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሳምንት በፊት ‹‹መስመራችንን አጠናክረን ወደፊት እንሄዳለን›› በሚል ርዕስ ክልላዊ ጉባዔ በመቐለ ከተማ የሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ ሲከናወን፣ ሁለት የሥነ ጥብብ ሥራዎችን ቀርበው ነበር፡፡ የመጀመርያው ዳኛው ከተቃራኒ ቡድን ጋር ሆኖ የሚታገልበት የገመድ ጉተታ ሲሆን፣ የዚህ ቡድን ውክልና ተደምረን በፍቅር አንድ እንሁን የሚለው የለውጡ ኢሕአዴግ እንደሆነ በግልጽ ከምልልሶቹና ከአቀራረቡ መረዳት አያዳግትም፡፡ ይኼ የገመድ ጉተታ የተማረውን ኃይል የሚቃረነው ቡድን በተለይም ሕወሓት ሆኖ እንዲታይ አድርጎ ያቀረበ ሲሆን፣ ውድድሩ በኋለኛው ቡድን አሸናፊነት ሲጠናቀቅም አዳራሹ ውስጥ የነበረው ደስታና ሳቅ የድራማውን ዓይነት ፖለቲካዊ ውጤት ምንኛ እንደሚናፍቅ አመላካች ነበር፡፡

የተከተለው ሙዚቃዊ ድራማ ወደ እርሻ በሚሄድ ሰውና በጓደኛው መካከል በሚደረግ ቃለ ምልልስ ተጀምሮ፣ በመሀል ሰላምታ ሰጥታ በምትቀላቀላቸው ወይዘሮ በሚነገር አባባል እንንገራቸው እስኪ ተብሎ፣ ‹‹አገር እየፈረሰና እየተበተነ ውህደትና ብልፅግና የሚሉት አይሠራም፤›› ሲል በሙዚቃ ይጀምራል፡፡ ወይዘሮዋ፣ ‹‹መልካም በመሥራቷ ጥፊ ሆነ እራቷ›› ብለው በሚጀምሩት ሙዚቃዊ ድራማ በንግግራቸውም፣ ውህደታቸውም መሠረት የለውምና እምልላችኋለሁ ጠፊ ነው፤›› ብሎ ይደመድማል፡፡ ይኼ ድራማ ሲጠናቀቅ በአዳራሹ የተሰጠው ምላሽ፣ ቅዳሜና እሑድ የሚካሄደው የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ አመላካች ነው ሲሉ የገመቱ አልጠፉም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አዳዲስ ጥምረቶችና የቀጣይ አገር አቀፍ ምርጫ ፉክክሮች

 

የጉባዔው ውሳኔ እምብዛም አስቀድሞ በሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴ ከተንፀባረቁ፣ እንዲሁም በአባላት ከተስተጋቡ አቋሞች የተለየ እንደማይሆን የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከመጪው አገራዊ ምርጫ መቃረብ ጋር በማያያዝ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሠላለፍ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ይደመጣል፡፡

ይህ ጥያቄ በስፋት የቀድሞ ኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የግንባሩን ውህደት ሲያፀድቅ፣ የሕወሓት አባላት በመቃወማቸውና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውይይት ላይ ባለመሳተፋቸው ጎላ ብሎ የተሰማ ነው፡፡ በመቐለ ከተማ ከተደረጉ በርካታ ፖለቲካዊ ውይይቶችና ዓውደ ጥናቶች፣ ሕወሓት በማዕከላዊው ፖለቲካ መድረክ አጋር ሊሆኑት የሚችሉ ቡድኖችን ለመለየት ያደገረው እንቅስቃሴ እንደሆነ በርካታ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

በተደጋጋሚ በመቐለ ከተማ ለክልሉ መንግሥት ወይም በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄዱ ውይይቶች፣ በፌዴራሊዝምና በብሔር ፖለቲካ ላይ በብዛት የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ በእነዚህ ስብሰባዎች የሚጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋሞችን የሚያንፀባርቁ እንዲሆኑ በጥንቃቄ እንደሚሠራ፣ በተሳታፊዎቹ ስብጥርና በመድረኮች በሚነሱ ሐሳቦች መረዳት ይቻላል፡፡

እነዚህ የዳሰሳ ጥናት የመሰሉ ዓውደ ጥናቶች ሲደረጉ የቆዩና የፓርቲው አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት ከሚመስሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ኅብረት ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ እስካሁን ፍሬ አፍርቶ ከሕወሓት ጋር ሊያብር ተስማማ የተባለ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የፓርቲዎች ቡድን አልታየም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያውያና አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት የተባለ ጥምረት ፈጥረው ቀጣዩን ምርጫ በአንድ ምልክት ለመወዳደር፣ ታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

አብሮነት ስለመግባቢያ ሰነዱ በሰጠው መግለጫ ላይ፣ ‹‹ኢሕአዴግ የለውጥ ሒደቱን ሁሉን አቀፍ በሆነ የጋራ የሽግግር ተቋምና እንዲህ ዓይነቱ ተቋም የውይይትና የድርድር ሒደት በመነጨ ፍኖታ ካርታ እንዲመራ ማድረግ ሲገባው፣ በተለምዶ አምባገነናዊ ባህርይ ‹እኔ አሻግራችኋለሁ› በሚል መታበይ በራሱ ፍላጎትና መንገድ ብቻ ሊመራው በመሞከሩ የለውጥ ሒደቱ የመክሸፍ አደጋ ገጥሞታል፤›› ሲል ትችት ያቀረበ ሲሆን፣ ‹‹የተጀመረው የለወጥ ሒደት አግባብ ባለው መንገድ ባለመመራቱ ምክንያት አገራችን በአሁኑ ወቅት ህልውናዋን የሚፈታተን አደጋ ውስጥ ትገኛለች፤›› ሲልም ይከራከራል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አዳዲስ ጥምረቶችና የቀጣይ አገር አቀፍ ምርጫ ፉክክሮች

 

በዚህም ምክንያትም አገሪቱ ምርጫ የማድረግ በምትችልበት አቅም ላይ አይደለምና ምርጫው መራዘም አለበት በማለት ለሪፖርተር የገለጹት የኅብር ኢትዮጵያ የፓርቲና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ፣ ‹‹እኔ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ መርምረን አገሪቱ በአሳሳቢ የአገር ህልውና ፈታኝ ጊዜ ላይ ስለምትገኝ፣ ይኼንን ፈታኝ ሁኔታ ለማለፍ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል ከሚሠራ ተመሳሳይ ሐሳብ ያለን ለምን በጋራ አንሠራም ብለን ነው የተስማማነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ይህም በፈታኝ ሁኔታ ለምትገኝ አገር የማዳን እንቅስቃሴ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ቀጣዩ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ መቀመጥ አለበት በማለት የሚከራከሩት አቶ ግርማ፣ ምርጫው በ2012 ዓ.ም. ይደረግ የሚለው ላይ ስምምነት አለመኖሩንና የጋራ ምክር ቤቱም ለውይይት ከመረጣቸው አንዱ አጀንዳ እንደሆነ በመጠቆም፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው በ2012 ዓ.ም. ይደረግ ቢባል ገዥው ፓርቲ ላለፉት 27 ዓመታት ሕዝቡን ምን እንዳደረገ እያወቅን፣ ባለፉት 18 ወራት ተለወጥኩ ብሎ ምንም እንዳልመጣ ዓይተናል፡፡ ይህ ሪፎርም ድጋፍ ይደረግለት ተብሎ ቢሠራም፣ ‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ› እንደሚባለው ወደ ቀድሞው ሁኔታ ተመልሷል፤›› በማለት፣ ለውጡ ከሽፏልና ምርጫው መራዘም አለበት ብለው ሦስቱም ፓርቲዎች እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡  

ሆኖም ምርጫው የግድ በ2012 ዓ.ም. ይደረግ ቢባልም፣ ከገዥው ፓርቲና በእሳቸው አገላለጽ ኮንፌዴራሊስት ከሚሏቸው እንደ ሕወሓት ካሉ ፓርቲዎች በስተቀር ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመተባበር ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ፣ ይህም የበለጠ ተፎካካሪ እንዲሆኑና የመራጮች ድምፅ ለተለያዩ ፓርቲዎች እንዳይበታተን እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሌላው ለኢትዮጵያ አገራዊ ህልውናና የአገሪቱ ቀጣይ ሁኔታ ላይ እሠራለሁ የሚል ኃይል ሊቀላቀለን ይችላል፤›› ሲሉም ጥሪ አድርገዋል፡፡ ይሁንና ምርጫ ቦርድ ምርጫው ይደረጋል የሚለው እንደ ካሁን ቀደሙ ድምፅ ለብልፅግና ፓርቲ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም የሚሉት አቶ ግርማ፣ ‹‹አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለምርጫ የማትመችበት የፖለቲካ ውጥረት ላይ ነች፤›› ሲሉም ይደመድማሉ፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት እስካሁን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ከወጣ በኋላ የተዘጋጁ 18 የምርጫ ደንቦች ረቂቃቸው ያልፀደቀ መሆኑን፣ የምርጫ ጣቢያዎች፣ የአስፈጻሚዎች ቅጥር ማስታወቂያ ገና እየወጣ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም ብዛት ያለው የአገሪቱ ክፍል በኮማንድ ፖስት የሚተዳደር መሆኑን ነው፡፡

ነገር ግን ምርጫው የግድ የሚካሄድ ከሆነ የምርጫ አዘጋጅና ዘመቻ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን፣ ብሎም የምርጫ ካርታ (Electoral Map) ማዘጋጀታቸውን በመጠቆም፣ በተመረጡ ጣቢያዎች ዕጩዎችን ለማሰናዳት እንደማይቸገሩ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ፣ ቦርዱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አማካይነት የተለያዩ ቁሳቁሶችን በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በጀት እየገዛ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ‹‹በእርግጥ አጭር ጊዜ ነው ያለን፡፡ ነገር ግን የሚያስፈልገው ዝግጀት ሁሉ እንዲጠናቀቅ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን እንገኛለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የምርጫው ተዓማኒነትም በጊዜው እጥረት ብቻ ሊለካ እንደማይገባ የገለጹት አማካሪዋ፣ ‹‹የምርጫ ተዓማኒነት በቁሳቁስና በሌሎች አቅርቦቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በበርካታ ተያያዥ ጉዳዮች የሚወሰን ነው፡፡ የቀድሞውን የተቋሙን አካሄድ በመቀየር ቁርጠኝነታችንን፣ ገለልተኝነታችንንና ተዓማኒነታችንን ለማሳየት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ስለዚህም የእነዚህ ጥረቶች ጥምር ውጤት ለምርጫው ተዓማኒነት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ሲሉ አብራርተው ነበር፡፡

የምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው ዝርዝር ፍላጎት መሠረት የሚገዙት ቁሳቁሶች ለ50,900 የምርጫ ጣቢያዎች እንዲሆኑ ታልሞ እንደሆነም የጠቆሙት የኮሙዩኒኬሽን አማካሪዋ፣ ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በተወሰደ ልምድ ለ12.5 በመቶ ጣቢያዎች ሊሆን የሚችል መጠባበቂያ ዝግጅትም እንደሚደረግ ተናግረው ነበር፡፡

በዚህ ምርጫ መካሄድ ላይ የማያወላዳ አቋም አለኝ የሚለው ብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ምርጫው በጊዜው እንዲካሄድ እንደሚደረግ በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው በቀጣዩ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት አስቀድሞ በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገ የአማራና የኦሮሞ ባለሀብቶች ባዘጋጁት የሰላም ኮንፈረንስ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር፣ ባለሀብቶች ከብልፅግና ጋር አጋርነት እንዲያሳዩ ጠይቀው ነበር፡፡

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ሥፍራ በተካሄደ የብልፅግና ፓርቲ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ማጠቃለያ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ብልፅግና ፓርቲ ለምርጫ ሳይወሰን ለትውልድ የሚሠራ ፓርቲ ነው በማለት፣ የብልፅግና ፓርቲን ሐሳብ ማሸነፍ የሚችል ኃይል ለቀጣይ 50 እና 60 ዓመታት እንደማይመጣ በመግለጽ፣ እሳቸውን በማሸነፍ ወደ ሥልጣን የሚመጣ ኃይል ቢኖር እንኳን ከዚህ ዕሳቤ ውጪ ኢትዮጵያን ለወራት ማስተዳደር እንደሚያዳግተው ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቅስቀሳ ሳይጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአዲሱ ፓርቲያቸው ቅስቀሳ ጀምረዋል ተብለው የተተቹ ቢሆንም፣ ይህንን መሰል መልዕክቶች በተለያዩ መድረኮች ሲደጋግሙ ተደምጠዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚሊኒየም አዳራሽ አስተያየት በሚመለከት ሐሳባቸውን የሰነዘሩት አቶ ግርማ፣ ‹‹የሐሳብ ልዩነት ለማስተናገድ ዝግጁነት እንደሌላቸው ያሳያል፡፡ አዲሱ ፓርቲ የ27 ዓመታቱ ኢሕአዴግ ነው እንጂ ሌላ የለውም፡፡ ስለዚህም እናሸንፈዋለን፤›› ይላሉ፡፡

ሆኖም ዋናው ትኩረታቸው ምርጫው መካሄድ አለበት ወይ በሚለው ጥያቄ ላይ እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹እኛ ሥልጣን ብንይዝስ ለብቻችን ነው ወይስ ተቋማዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ ለመፍትሔ እንሠራለን ብለን እናስባለን፤›› በማለትም ዝግጅታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ውህደት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኤዜማ)፣ በተጠናከረ ሁኔታ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራውን እያከናወነ ሲሆን፣ በመጪው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ዝግጅት እያደገ ነው፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማካሄድና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በመጪው ምርጫ ዋና ተፎካካሪ ለመሆን እየሠራ ነው፡፡

የብልፅግና ፓርቲ አንዱ ጠንካራ ተቀናቃኝ ሊሆን የሚችለውና አዲስ የሆነው ጥምር ኃይል በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) የተዋቀረ ሲሆን፣ ይህ ጥምር በክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ አቋምና አመለካከት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ሲነገር ቆይቷል፡፡

በተለይ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚታወቀው አቶ ጃዋር መሐመድ ኦፌኮን መቀላቀሉን ከገለጸ በኋላ፣ የእነዚህ ፓርቲዎች ጥምረት እንዲፋጠን ማድረጉን በተለያዩ ሚዲያዎች ያስታወቀ ሲሆን፣ የጥምሩ ስትራቴጂም እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ተናግሯል፡፡

የእነዚህ ፓርቲዎች ጥምረት መፍጠር የአገሪቱ ፖለቲካ ቅርፅ እንዲኖረውና ማን ለምን ይቆማል? የሚለውን ከመናገር ባለፈ በተለይም በቀጣዩ ምርጫ ሊኖር የሚችለው ፉክክር ከወዲሁ ለመገመት የሚያስችል እንዲሆን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

ሆኖም ግን ከ50 ሺሕ በላይ ለሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች 300 ሺሕ ያህል የምርጫ አስፈጻሚዎችን የሚያዘጋጀው የምርጫ ቦርድ፣ በምርጫ ጣቢያዎች ዕጩ ማቅረብ ያለባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንደሁም በእነዚህ ጣቢያዎች ታዛቢ ማሰማራት የሚጠበቅባቸው እንደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ ተቋማት ዝግጁነት ምን ድረስ ነው ሲሉ የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ሃምሳ ሚሊዮን ያህል መራጮች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ 2012 ከወዲሁ ማነጋገሪያ መሆን ጀምሯል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -