የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የንግድ ባንኮች የአክሲዮን ባለቤት የሆኑበት ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አትራፊነት መሸጋገሩ ታወቀ፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ኪሳራ ላይ እንደነበር ሲገለጽ የቆየው ኢትስዊች በ2011 የሒሳብ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ የተጣራ 12.9 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሳምንት የ2011 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ ይህ ትርፍ የተመዘገበው በሁለት ምክንያቶች ስለመሆኑም ይጠቅሳል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለኩባንያው አትራፊነት አንዱና የመጀመርያው ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው ኩባንያው በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ከጥር 2011 ጀምሮ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ ነው፡፡ ሌላው ለአትራፊነቱ ምክንያት ነው ተብሎ የተገለጸው ደግሞ፣ የኦፕሬሽን ሥራው መጠን እያደገ በመምጣቱ እንደሆነ የኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ አመልክተዋል፡፡
ኩባንያው ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ኪሳራ በማስመዝገቡ በ2011 የሒሳብ ዓመት የተገኘው ትርፍ እስካሁን የተከማቸውን 26.08 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ሙሉ በሙሉ የሚያካክስ አለመሆኑን በመግለጽም፣ ለባለአክሲዮኖች የሚከፋፈል ትርፍ እንደማይኖር ተገልጿል፡፡ ነገር ግን በ2011 የሒሳብ ዓመት የተገኘው ትርፍ የኪሳራ ክምችቱ ወደ 13.9 ሚሊዮን ብር ዝቅ ከማድረጉም በላይ፣ በቀጣይ የኪሳራ ክምችቱን ሙሉ ለሙሉ በማካካስ ለባለአክሲዮኖች ትርፍ የሚከፋፈልበትን ዕድል እያመቻቸ መሆኑን ያመለክታል፡፡
እንደ ኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት የኩባንያው ሀብት 221.2 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ጠቅላላ ካፒታሉ ደግሞ 202.9 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የሀብትና የጠቅላላ ካፒታል መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የኩባንያው ሀብት በሰባት በመቶ፣ ጠቅላላ ካፒታል ደግሞ በ6.8 በመቶ እንደጨመረ ያሳያል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል መጠን ብዙ ለውጥ ሳያሳይ 216.06 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ 56.9 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ107 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 10.2 ሚሊዮን ብር ወይም 18 በመቶ የሚሆነው ኩባንያው በባንኮች በቁጠባና በጊዜ ገደብ ካስቀመጠው ገንዘብ የተገኘ ወለድ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀሪው 46.6 ሚሊዮን ብር ወይም 82 በመቶ ደግሞ ኩባንያው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችና ሌሎች የገቢ ምንጮች የተገኘ መሆኑም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 1.96 ሚሊዮን ብር የካፒታል፣ 36.73 ሚሊዮን ብር የኦፕሬሽንና 6.5 ሚሊዮን ብር አስተዳደራዊ ወጪዎችን አውጥቷል፡፡
ኢትስዊች በሒሳብ ዓመቱ ያለማቋረጥ የ24 ሰዓታት የሒሳብ ማስተላለፍ፣ የሒሳብ ማጣራትና ማወራረድ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ፣ በሒሳብ ዓመቱ በብሔራዊ ስዊቹ የተላለፉ የኤቲኤም ትራንዛክሽኖች ብዛትና የገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት በሒሳብ የዓመቱ የኤቲኤም የትራንዛክሽን መጠን ወደ 10.2 ሚሊዮን ማደግ መቻሉንና በዚህ ትራንዛክሽን የተቀሰቀሰው የገንዘብ መጠንም ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተካሄደው ትራንዛክሽን ከባለፈው ዓመታት ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት በንጽጽር ከባለፈው ዓመት በመጠን 72 በመቶ ብልጫ ያሳየ ሲሆን፣ ያንቀሳቀሰው ገንዘብ ደግሞ 60 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የኤቲኤም ትራንዛክሽን ስኬት አማካይ ምጣኔ አምና 69 በመቶ የነበረ መሆኑን የሚጠቁመው ይኼው የኩባንያው መረጃ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን ይህ ምጣኔ በኩባንያው በተደረገ ከፍተኛ ጥረት ወደ 80 በመቶ ከፍ እንዳለ አቶ ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡
በኤቲኤም ትራንዛክሽን ምክንያት ያልተወራረዱና ተንጠልጣይ የባንክ ለባንክ ሒሳቦች መጠን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 6.8 ሚሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት ወደ 2.3 ሚሊዮን ብር መውረዱም ተመልክቷል፡፡ ይህ ቁጥር ይበልጥ ዝቅ ብሎ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 30 ቀን 2019 ላይ 1.1 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ኩባንያው በአባል ባንኮች ጥያቄ በሒሳብ ዓመቱ 106.1 ሚሊዮን የክፍያ ካርዶችን አትሞ ሲያስረክብ፣ የካርድ ኅትመት ሥራ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ37.6 በመቶ አድጓል፡፡ ሆኖም ኩባያው የካርድ ኅትመትን በሚመለከት በሙሉ አቅሙ እየሠራ ያለመሆኑም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በሪፖርቱ ከተጠቀሱ ሌሎች ክንውኖች ውስጥ የኩባንያው አክሲዮንን ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ለመሸጥ ከተወሰነው ውሳኔ ጋር በተያያዘ የተጠቀሰው ይገኝበታል፡፡ የኩባንያው ካፒታል 300 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ተወስኖ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 216.6 ሚሊዮን ብር ከነባር ባለአክሲዮኖች ሲሰበሰብ፣ ቀሪዎቹ 83.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሸጡ ተወስኖ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የኩባንያው ባለአክሲዮኖች እንዲሆኑ ጥረት ቢደረግም የተፈለገውን ያህል ውጤት አለመገኘቱን ያመለክታል፡፡ ይህንንም ‹‹በርካታ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮን ለመግዛት ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም፣ የሒሳብ ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሦስት ተቋማት ብቻ በድምሩ 1.7 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን ገዝተዋል፤›› በማለት የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 82.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ሊሸጡ ያለመቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ አክሲዮኖች የወጡት መስከረም 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በመሆኑና በንግድ ሕጉ መሠረት ደግሞ በአምስት ተከታታይ ዓመታት ወይም እስከ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ተሸጠው ማለቅ ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ አሁን አክሲዮኖቹ ዋጋ አልባ ሆነዋል ተብሏል፡፡
የኢትስዊች የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተፈላጊነት በባንኮች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ በክፍያ ሰብሳቢዎች፣ በገቢዎች ሚኒስቴር፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በአየር መንገድና በተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶችና በመሳሰሉ ሌሎች የክፍያ ሥርዓቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በሚነካቸው ተቋማት ጭምር በመሆኑ አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር ታቅዷል፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በዓይነትም ሆነ በቅልጥፍና የተሻሉ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ጥረት በቀጣዩ ሒሳብ ዓመትም አጠናክሮ የሚሠራበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በ2012 ሒሳብ ዓመት 53.5 ሚሊዮን ብር የካፒታል ወጪዎችና 44.6 ሚሊዮን ብር የኦፕሬሽንና አስተዳደር ወጪዎች በበጀት ተይዘዋል፡፡
ኩባንያው አሁን እየሰጣቸው ያሉት አገልግሎቶች እንደተጠበቁ ሆነው በ2012 የሒሳብ ዓመት ከአባል ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር በስድስት ግቦች የተዋቀረ ዓመታዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተገበረ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትስዊች ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓትን ለማስረፅ አጋዥ ይሆናሉ ተብለው ከሚታመንባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ሁሉንም የአገሪቱን ባንኮች በአክሲዮን ባለቤትነት ያቀፈ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የሁሉንም ባንኮች ኤቲኤሞች በማስተሳሰር የማንኛውም ባንክ ደንበኛ በየትኛውም ባንክ ኤቲኤሞች ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚችሉበትን አሠራር በማዕከል እያስተባበረ ይገኛል፡፡