Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ በሞተር ብስክሌት የመልዕክት አገልግሎት ሊጀመር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ፍቃድ ያልተሰጣቸው የሞተር ብስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያደገ ሲሆን፣ የዕገዳው ምክንያትም ሕገወጥ የሞተር እንቅስቃሴ በመስፋፋቱ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ወዲህም በከተማው የሚንቀሳቀሱት የሞተር ብስክሌቶች በድርጅት ሥር እንዲሆኑ፣ ሰሌዳ ቁጥራቸውን ኮድ ሦስት  እንዲያደርጉት፣ የድርጅቱ ዓርማና ስልክ ቁጥር እንዲለጠፍ እንዲሁም የደንብ ልብስ እንዲለብሱ አዲሱ አሠራር አስገድዷቸዋል፡፡

የሕግ ዕገዳው ከወጣ ጀምሮ የተለያዩ ድርጅቶች ሞተረኞችን በማቀፍና አስፈላጊውን መርህ እንዲከተሉ በማድረግ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህ ውጪም ራሳቸው የሞተር ባለቤቶች ማኅበራት መሥርተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም 50 ማኅበራት መመሥረታቸው ታውቋል፡፡

ከእነዚህ 50 ማኅበራት መካከልም 13 የሚሆኑትን ያቀፈው ባሉበት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማክሰኞ ታኅሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ማኅበሩ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሞተረኞች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ባሉበት በ13 ማኅበራት ውስጥ የሚገኙ ከ700 በላይ ሞተረኞችን አደራጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት እየሩሳሌም መሸሻ እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት በከተማዋ የሚታወቀውን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመኪና የትራንስፖርት አገልግሎት ዓይነት በሞተር ይዘው መጥተዋል፡፡ ከእሱም በተጨማሪ በሞተር የማድረስ አገልግሎት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

‹‹ባሉበት የሞተር የትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀምር የማኅበረሰቡን ችግር ከመቅረፉ ባሻገር አቅምን በማይጎዳ፣ ኪስን ባማከለ፣ እንዲሁም ደኅንነትን ባካተተ መልኩ ወደ ሥራ ይገባል፤›› በማለት፣ ይህን ከማድረጋቸው በፊት ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በድርጅቱ የብቃት መመዘኛ ብቁ የሆኑትን በማሰማራት፣ መንግሥት ባወጣው የፍጥነት ወሰን መሠረት መንቀሳቀሳቸውን በጂፒኤስ በመከታተል፣ የሞተረኛውን ሙሉ መረጃ በማስቀመጥ፣ እንዲሁም የአደጋ መከላከያ ቁሶችን ሾፌሮች ይዘው እንዲቀርቡ በማድረግ፣ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከሞተር የትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ የማኅበረሰቡን ችግር ይቀርፋል ብለን ያሰብነው በሞተር ዕቃ የማድረስ አገልግሎት ነው፤›› ያሉት ሥራ አስኪያጇ፣ ‹‹ይህን አገልግሎት ባሉን ሞተረኞች በየትኛውም የአዲስ አበባ ቦታ ደንበኞች የሚፈልጉትን ዕቃ በፍጥነት በፈለጉት ጊዜ ማድረስና መቀበል ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ለእነዚህ ሁለት አገልግሎቶችም የሞባይል መተግበሪያና አጭር የስልክ መስመር ማዘጋጀታቸውንም ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ድርጅቶች ከፍተኛው የሞተር ቁጥር የያዘው ባሉበት ድርጅት እንደሆነና በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ማኅበሮች በሁሉም አካባቢ በመኖራቸው የተደራሽነቱን ከፍተኛነት የሚሳይ እንደሆነም ወ/ሪት እየሩሳሌም ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን ለመስጠት ከመንገድ ትራንስፖርት ፈቃድ ማግኘታቸውንም አክለዋል፡፡ ታሪፉን በተመለከተም ተመጣጣኝ እንደሆነ በመግለጽ፣ በቀጣይ ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የሞባይል መተግበሪያውንና አጭር የስልክ መስመሩንም እንዲሁ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከማኅበሩ ጋር እየሠሩ ያሉ ማኅበራት ሰላም፣ ቄራ ሰላም፣ ንሥር፣ ቦሌ ሚካኤል፣ ፈጣን፣ አቢሲኒያ፣ አዲስ ሕይወት፣ ዕድገት በኅብረት፣ ፊጋና ሰሚት፣ ብሉ ስታር፣ ዘመን፣ የካና ሐበሻ እንደሆኑ የሞረተረኞች ተወካይ አቶ ሙባረክ ጀማል ገልጸዋል፡፡፡

ከዚህ በፊት በጥቂት ጥፋተኞች ምክንያት የብዙኃኑ ስም መጥፋቱን አቶ ሙባረክ አውስተው፣ አሁን ግን የጠፋውን ስማችን ወደ ጥሩ ለመቀየር ወደ ሥራ ሁላችንም ገብተናል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ለጊዜው በአዲስ አበባ ብቻ የሚሰጥ ሲሆን፣ በቀጣይም በክልል ከተሞች ለማስፋፋት መታሰቡ ታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች