Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበግላዊነት መብት ላይ የተደቀኑ ዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶች

በግላዊነት መብት ላይ የተደቀኑ ዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ለግላዊነት ተግዳሮት ከሆኑት አንዱ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የዚህ ቴክኖሎጂ መምጣት ግላዊነትን እያጣበበው መሆኑ ‘አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው’ ጉዳይ ነው፡፡ የግል መረጃዎችን ማከማቸት፣ ማነጻጸር (ማስተያየት)፣ መያያዝ፣ ማግኘት የሚቻልባቸው ዕድሎች ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ ነው፡፡ ግላዊነትን ጠብቆ ለማቆየት ብቻ ሲባል ቴክኖሎጂውን ‘አትድረስብኝ፣ አልደርስብህም’ ማለት የሚታሰብ አማራጭ አይደለም፡፡ ስለሆነም በዚህ ሁኔታም ውስጥ ሆኖ በተቻለ መጠን የግላዊነት መብቶች ሊከበሩ የሚችሉበትን ዕድሎችና አጋጣሚዎች ማስፋት ነው፡፡

በቴክኖሎጂም ጭምር የግላዊነት መብት ጥበቃን ማጠናከር አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ የሚያልፈውን ደግሞ በሕግ ሥርዓት ማስያዝና ተላላፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ ተደራቢ አማራጭና መፍትሔ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም ሁለተኛው ነጥብ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የግላዊነት መከበር ፋይዳ

ከተለያዩ ድርሳናት መረዳት እንደሚቻለው፣ ግላዊነት የራስና የቤተሰብን ግላዊ መረጃዎችና ሕይወት፣ ቤትን፣ መረጃ መለዋወጥንና ከእነዚህ ጋር የተቆራኙ ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡ እነዚህን በተመለከተ ጣልቃ ባለመግባት መተውን፣ መረጃ አለመውሰድን አለማሠራጨትን ሕዝባዊ አለማድረግ የግላዊነት ሕግ ትኩረት ነው፡፡ ስለሆነም ግላዊነትን የሚመለከቱ መረጃዎች የሚተዳደሩበትን፣ የሚያዙበትን፣ ማግኘት የሚቻልበትን አግባብ ወዘተ ያካትታል፡፡

ግላዊነት፤ የፍልስፍና፣ የፖለቲካ፣ የሥነ ማኅበረሰብ፣ የሥነሰብ እንዲሁም የሕግ ጭብጥ በመሆን መወያያ አጀንዳ ነው፡፡ በእነዚህ መስኮች በተመሳሳይ ጊዜ ወደ አጀንዳነት መጥቷል ማለት ግን አይደለም፡፡ በጊዜ ርዝማኔ ሲታይ የግሪኩ ፈላስፋ፣ አርስጣጣሊስ ስለ ሕዝባዊና ግላዊ ንፍቀ ክበብ ሐተታውን ባቀረበበት የድርሳኑ ክፍል ማጠንጠኛው ግላዊነት ስለሆነ ቅድምና አለው፡፡ ሕዝባዊ (በይፋ) ስለሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በግል በቤትና በቤተሰብ ደረጃ ከሚደረጉት እያነጻጸረ የአንዱ ከሌላው መለየት የሚኖረውን ፋይዳ ጭምር ጽፏል፡፡

የግል ሕይወት (ግላዊነት) ሰውነትን፣ የግል መረጃን፣ ግላዊ ባህርይንና መረጃ ልውውጥን ያካትታል የሚሉም አሉ፡፡ እነዚህን የግላዊነት ዓይነቶች ጥበቃ ለማድረግ አካልን፣ ቤትን፣ ቤተሰብንና መልዕክት መላላክን የተከበሩና ጣልቃ የማይገባባቸው ማድረግ የግላዊነት ሕግ ዓላማና ግብ ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ግላዊ ማንነቶችና መለያዎች የሚጣሱባቸው አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች መልካቸው ብዙ ነው፡፡ በተለይም የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሲስፋፋና ሲበራከት ግላዊነት እየተመናመነ ሕዝባዊ መሆን እየተስፋፋ ነው፡፡ ዩቫል ኖህ ሐራሪ የተባለው የታሪክ ሊቅ ይህን ሁኔታ ለመግለጽ የጆርጅ ኦርዌልን አገላለጽ ይዋሳል፡፡ ኦርዌል፣ “1984” በተሰኘው ታዋቂ የልብወለድ ድርሰቱ ውስጥ የፈጠረው ‘ቢግ ብራዘር’ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ የሁሉንም ሰው ሁኔታ በየትም ቦታና ጊዜ የሚቆጣጠርና የሚያይ ስለሆነ በየቦታው በተሰቀሉት ቴሌቪዥን መሳይ ዕቃዎች ‹‹ቢግ ብራዘር እያየህ ነው›› (Big brother is watching you) የሚሉ ጽሑፎች ይተላለፋሉ፡፡ ልክ እንደዚያው ሁሉ በዚህ ዘመንም ግዙፍ መረጃዎች ሁሉንም ሰው ያያሉ፡፡ ከግዙፍ መረጃዎች ስለማንም ሰው ማወቅ ይቻላል፡፡ እናም ‹‹ግዙፍ መረጃ እያየህ ነው›› (Big data is watching you) ይላል፤ ሐራሪ “21 Lessons for the 21st Century” በሚለው መጽሐፉ፡፡

ፈር ቀዳጁ ብራንዴዝ

ስለ ግላዊነት መብት ሲነሳ ስማቸው አብሮ የሚነሳ ሁለት የአሜሪካ የሕግ ሊቃውንት አሉ፡፡ እነሱም ሳሙኤል ዋረንና ሉዊስ ብራንዴዝ ናቸው፡፡ በተለይም ሁለተኛው በጣም ታወቂ ነው፡፡ እንዲታወቁ ያደረጋቸውም እ.ኤ.አ. በወርሃ ታኅሳስ በ1890 ዓ.ም. በታተመው የሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መጽሔት (Harvard Law Review) ላይ በጋራ ያሳተሟት አጠር ብላ ነገር ግን በአሜሪካ የሕግ ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ የሆነችውን ‹‹የግላዊነት መብት›› (The Right to Privacy) የምትል ፈር ቀዳጅ ጽሑፍ ናት፡፡

ከዚያ በፊት የነበሩትና የሚታወቁት ጽንሰ ሐሳቦች አካላዊ ደኅንነትና የንብረት መብቶች ናቸው፡፡ አሁን ግላዊነት በመባል የሚጠራው ቀድሞ ጥበቃ የሚደረገው ከሁለቱ መብቶች ጋር ተደባልቆ፣ እንደ ነገሩ ሁኔታ ከሁለቱ በአንዱ ነበር፡፡ ይሁንና አካላዊ ደኅንነትም የሰውን ስሜትና መንፈስ ሊያካትት ስለማይችል በሰዎች አዕምሯዊ ሰላምና ደኅንነት፣ ስሜትን አዋኪ ከሆኑ ጥቃቶችና ጉዳቶች መከላከል የሚያስችል የሕግ ብልሃት እንደሚያስፈልግ እኒህ ሁለት ምሁራን ገለጹ፡፡

በንብረት መብትም በኩል የሚደረገው ጥበቃ ቢሆን እንዲሁ በቂ ላለመሆኑ የሰዎችን ደብዳቤና መረጃዎች ባለቤቶቹን ሳያስፈቅዱ በጋዜጣና በሌሎች ሚዲያዎች ይፋ ማድረግ አስጠያቂነቱ ደብዳቤውን ወይም መረጃውን እንደ አዕምሯዊ ንብረት በመውሰድ ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት በማድረግ ነበር፡፡ እንግዲህ እነ ብራንዴዝ ይኼን ዓይነቱን የሕግ ጉዞና አረዳድ እንዲገታና ግላዊነት ራሱን ችሎ እንጂ በአካላዊ ደኅንነት እና/ወይም በንብረት መብት ሥር ተወሽቆ ሳይሆን ራሱን የቻለ መብት እንዲሆንና ጥበቃም እንዲያገኝ ማድረግ ነው የክርክራቸው መቋጫ፡፡

ለጽሑፋቸው እንደ ልዩ መፍትዔ የሆናቸው ጋዜጠኞች በየሠርጉ እየተገኙ የተጋቢዎችን ፎቶግራፍ በጋዜጦች ላይ ማውጣታቸውና የማኅበራዊ ሐሜት አምዶችን በመክፈት ከየቦታው የቃረሟቸውን ሐሜቶች ማውጣት መቀጠላቸው ነው፡፡ እነዚህን ድርጊቶች ለስም ማጥፋት ብቻ በሚደረግ የሕግ ጥበቃ በቂ ስላልሆነ ግለሰቦች ‘ብቻ የመሆን’ ወይም ‘ለብቻ የመተው መብት’ (The right to be let alone) ሊከበርላቸው እንደሚገባም አትተዋል፡፡

እያደር ግን ሌሎች ጽሑፎችም መውጣት ቀጥለዋል፡፡ በተለይም የግላዊነት መብት ሲጣስ ተከትሎ የሚመጣው ከውል ውጭ አላፊ መሆንን የሚመለከተው ተጠቃሽ ነው፡፡ ብራንዴዝ በፎቶግራፍና በየጋዜጣዎች የሚወጡት የሐሜት ወሬዎች የሰዎችን የግላዊነት መብት የሚሸረሽር ነው በማለት በወቅቱ ይዞት የመጣውን መከራከሪያ፣ በዚህ ዘመን ላይ ከቴክኖሎጂው ማደግ ጋር ተያይዞ መንግሥት በስልክና በኢሜል፣ በጂፒኤስ፣ በደኅንነት ካሜራዎች ወዘተ የሚሰበስበውን መረጃ ቢያይ ምን ይል ነበር ብሎ ማሰብ አይቀርም፡፡

ለእነ ዋረንና ብራንዴዝ ግላዊነት በግላዊ ጉዳዮች የሌላ ሰውን ጣልቃ አለመግባት፣ የራስን ለራስ ብቻ መተውን ያመለክታል፡፡ የተነሺውን ፈቃድ እስካላገኙ ድረስ ፎቶ ከመነሳት መተው እንደማለት ነው፡፡ ሌላው የግል መረጃን እንዴትና ለማን መተላለፍ እንዳለበት መቆጣጠርንም ይጨምራል፡፡ የግል ማህደርን የማግኘትና ተደራሽ የማድረግ መብትም እንዲሁ በግላዊነት መብት ግዛት ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የግልና ከራስ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መረጃዎችን ማን ማግኘት እንደሚችል መወሰንንም ይመለከታል፡፡

የግል ሕይወትን ለግለሰቡ ብቻ መተው ሲባል ሰው በቤቱና በአደባባይ ባልሆነ መልኩ የሚተገብራቸው ባህርያቱ ወይም አመልና ፀባዮቹን ይመለከታል፡፡ አበላሉን፣አለባበሱን፣ የፆታ ግንኙነት ሁኔታውን ወዘተ ይመለከታል፡፡

ከሥነ ማኅበረሰብና የሥነሰብ ጥናቶች እንደሚያስረዱት የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ለግላዊነት የሚሰጡት ዋጋ የተለያየ ነው፡፡ እንደ ጥናት ጭብጥም በእነዚህ የትምህርት መስኮች ዘንድ ሰነባብቷል፡፡ በሕጉ ዓለም ደግሞ በተለይም በአሜሪካ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አጀንዳ መሆን ጀምሯል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋጋለ ውይይት በግላዊነት ላይ መደረግ የጀመረው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ ምንም እንኳን ግላዊነት ለንብረትና ለአካላዊ ደኅንነት በሚሰጠው ጥበቃ ሥር ስለሚካተትና ስለሚበቃው ተጨማሪና ራሱን ችሎ ጥበቃ ስለማያሻው ግላዊነት የሚባል ራሱን የቻለ ነገር የለም የሚሉ ቢኖሩም፣ አሁን አሁን ግን ይህ ዓይነቱ ክርክር እየቀረ ነው፡፡ ለይቶ ጥበቃ የማድረግ አስፈላጊነትም የለውም የሚለው ክርክር፣ የክርክር አጀንዳ ሲሆን አምብዛም አይስተዋልም፡፡ እንደውም ስለአስፈላጊነቱ የሚነሳው ክርክር ደርዙ እየጨመረ ነው፡፡ ምንያቶቹም እንዲሁ፡፡

ከእነዚም ውስጥ መረጃን በግል ይዞታ በብቸኝነት መያዝን ያስፋፋል ቢባልም ሰፋ ተደርጎ ሲታይ የሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ፣ የኅብረተሰብ ቁልፍ ዕሴት የሆኑ ጥልቅ ቀረቤታዎችን (የትዳር፣ የሐኪምና ታካሚ፣ የሃይማኖት አመራሮችና ተከታዮች መካከል ያሉ ግንኙነቶች ወዘተ)፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን ግለሰባዊ ግንኙነቶች ጥበቃ ለማድረግ ሲባል ግላዊነት ጥበቃ ያስፈልገዋል ባዮች አሉ፡፡

ግላዊነት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች

ግላዊነት የሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ሰው በሰውነቱ ብቻ መብቱ የሆነለት፡፡ ሰብዓዊ መብት ስለሆነም በልዩ ልዩ ሰብዓዊ መብት ሰነዶች ዕውቅና በመስጠት ጥበቃ እንዲደረግለት የሕግ ኃይል ሰጥተውታል፡፡ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ አንቀጽ 12፣ ዓለም አቀፉ ሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 17፣ የሕፃናት መብት ስምምነት አንቀጽ 16፣ የአውሮፖ መሠረታዊ ነፃነትና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስምምነት አንቀጽ 8፣ አሜሪካ የሰዎች መብትና ግዴታ መግለጫ አንቀጽ 5፣ አሜሪካ ሰብዓዊ መብት ስምምነት አንቀጽ 11 ላይ ስለግላዊነት ተደንግጓል፡፡ ከስፋትና ከጥበት በስተቀር መሠረታዊ ነጥቦቹ ወይም ይዘቶቹ ተመሳሳይ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አጭሩ ድንጋጌ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ ላይ ያለው ሲሆን፣ ሌሎቹ ይህንን ድንጋጌ ተንተርሰው ተጨማሪ መገለጫዎችን አክለዋል፡፡

ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ ላይ ያለው “No one shall be subjected to arbitrary interference with his privacy, family, home or correspondence, nor to attacks upon his honour and reputation. Everyone has the right to the protection of the law against such interference or attacks.” ወደ አማርኛ ሲመለስ የሚከተለውን ሊመስል ይችላል፡፡ ‹‹በማንኛውም ሰው ግላዊነቱ፣ ቤተሰቡ፣ ቤቱ ወይም የመረጃ ቅብብሎሹ ላይ ዘፈቃዳዊ ጣልቃገብነት ሊፈጸምበት፣ ስሙና ዝናው ላይም ጥቃት ሊደረግበት አይገባም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከእንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገብነት ወይም ጥቃት በሕግ ጥበቃ የማግኘት መብት አለው፡፡››

የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ የተጨመረው ሐሳብ ቢኖር “… arbitrary or unlawful interference…. nor to unlawful attacks …’’ በማለት ‘ሕገወጥ’ የሚለው ቃል ወይም ሐሳብ ብቻ ነው የተጨመረው፡፡ ከዚያ ውጭ ቃል በቃል ሳይቀር ተመሳሳይ ናቸው፡፡

የሕፃናት መብት ስምምነት ላይ ያለውን ብናይም ‘ማንኛውም ሰው’ በሚለው ፈንታ ‘ማንኛውም ሕፃን’ በሚል ተክቶ ሌላው ከዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብት ስምምነት ጋር እንዲሁ ቃል በቃል ሳይቀር አንድ ናቸው፡፡

ከላይ ከቀረቡት ለየት ያለና ሰፋ ያለው የአውሮፓ መሠረታዊ ነፃነቶችና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ስምምነት ላይ ያለው ነው፡፡ የአማርኛ አቻ ትርጉሙ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የስምምነቱ አንቀጽ 8 ንዑስ ቁጥር አንድ ‹‹ማንኛውም ሰው የግልና የቤተሰብ ሕይወቱ፣ ቤቱና የመረጃ ቅብብሎሹ ይከበሩለት ዘንድ መብቱ ነው›› ይላል፡፡ ንዑስ ቁጥር ሁለት ደግሞ የሚከተለውን ነው፣ ‹‹ማንም ሰው በእነዚህ መብቶቹ ሲገለገል የመንግሥት ባለሥልጣን በሕግ መሠረትና ስለብሔራዊ ፀጥታ፣ ሕዝባዊ ደኅንነት፣ የአገር ኢኮኖሚያዊ መልካም ዕድገትና ጥበቃ ሲባል ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ ሲሆን፣ እንዲሁም ሥርዓት አልበኝነትንና ወንጀልን ለመከላከል፣ የሌሎችን ጤናንና ሞራልን፣ መብትና ነፃነት ለመጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡››

ስለግላዊነት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተደነገጉት ከሞላ ጎደል ከላይ የተገለጹት ናቸው፡፡ ከእነዚህም የምንገነዘባቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ፡፡ ጣልቃገብነቱ ወይም ሕገወጥ የሆነው ጥቃት የሚፈጸመው በመንግሥትም በግልም ሊሆን ይችላል፡፡ ግለሰቦችም የግላዊነት መብታቸው ሊከበርላቸው የሚገባው ከማንኛውም አካል ነው፡፡

መንግሥት ያለበት ግዴታ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ ብቻ ሳይሆን፣ የግላዊነት መብት እንዳይጣስም ጥበቃ ማድረግ ከተጣሰም ተገቢ መፍትሔ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል የሕግና የተቋማት አደረጃጀት መዘርጋትንም ይጨምራል፡፡ ለማስከበር የሚሆኑ ሕጎችን፣ አሠራሮችን፣ ተቋሞችን ማዘጋጀት የመንግሥት ግዴታዎች አካል ነው፡፡

ሕገወጥ’ የሚለው የሚያሳየው በሕግ ያልተፈቀደ ጣልቃ ገብነትን ለማመልከት ነው፡፡ በሕግ በታወቀውና በተፈቀደው አግባብ ብቻ ሊሆን ይገባል በግላዊነት ላይ ሊኖር የሚችለው ጣልቃ ገብነት፡፡

ሕገወጥ ብቻ አለመሆን ሳይሆን ዘፈቀዳዊ ጣልቃገብነትም ክልክል ነው፡፡ ሕጋዊ ሆኖም ሕጉ በራሱ ዘፈቀዳዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያታዊ መሆን፣ መብቱ ዕውቅና የተሰጠበትን ሰነድ ጥቅል ግብና ዓላማ የሚያሟላ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ቤተሰብና ቤትን በሚመለከት የሚኖረው ትርጓሜ እንደየአገሩ መለያየቱ አይቀሬ ነው፡፡ ፈራሚ አገሮች ቤተሰብና ቤት በማለት የሚወስዱትን ካልሆነ በስተቀር አንድ ወጥ ትርጓሜ ማስቀመጥ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ በግመል ተጭኖ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወረው የአርብቶ አደሮች ቤትም ያው ቤት ነው፡፡

ግላዊነት ላይ የሚኖሩት ገደቦች በሕግ ተለይተው ሊታወቁ ይገባል፡፡ ስልክና የኢሜይልና ሌሎች መሰል የመረጃ መቀያየሪያ መንገዶች፣ ፖስታና ሌሎች የመረጃ ልውውጦችን መጥለፍ የተከለከለ መሆኑን ያካትታል፡፡ እነዚህ ድርጊቶችን አለመፈጸም ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው እንዲሁ የሌሎችን ግላዊነት መብት እንዳይዳፈር የሚከለክል ሕግና አሠራርን ማስፈን አለበት፡፡

የግለሰቦችን መረጃዎች በኮምፒውተርና በሌሎች መሣሪዎችም አማካይነት ቢሆን የሚከማቹበትን ሁኔታ የሚወስን ሕግ መኖር እንዳለበት ከጥቅል አስተያየቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ መረጃዎቹን ማን እንደሚቆጣጠራቸውና በማን እጅ ሥር እንዳሉ የሚወስን ሕግ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ለስምና ዝናም ተገቢውን ጥበቃ ማድረግን እንዲሁ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡

ከላይ ያየናቸው ሰብዓዊ መብት ሰነዶች ጥበቃና ዕውቅና የሰጡት ለግላዊ ሕይወት፣ ለቤተሰብ ሕይወት፣ ለቤትና መረጃ ቅብብሎሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ግላዊነት በሕገ መንግሥቶቹ

ስለግላዊነት ሲነሳ በመጀመሪያ የምናገኘውና ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት የ1923ቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25 እና 26 ላይ እንደተገለጸው በሕግ ከሚፈቀደው በስተቀር የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤትና ዕቃው የማይበረበር መሆኑ፣ የሚጻጻፈው ወረቀትን ማንም ሰው ቢሆን ሊመረምር የማይችል ስለመሆኑ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት ጥበቃ የሚያገኙት ኢትዮጵያዊያን (ዜጎች) ብቻ ሲሆኑ፣ የሚከበሩትን ቤት፣ ንብረትና የመልዕክት ልውውጦች ናቸው፡፡ በምን ሁኔታ ሊገደቡ እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ የሚነግረን ነገር የለም፡፡ ሕግ አውጭው የግላዊነት መብትን የሚገድብበት መለኪያዎች ስላልተቀመጡለት በምን ሁኔታና መቼ ይገደቡ የሚለውን የመወሰን ሙሉ ነፃነት አለው ማለት ነው፡፡

1948ቱ ሕግ መንግሥት ቢሆን፣ አንቀጽ 42 መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ካልሆነ በስተቀር በጽሕፈት የመላላክ ግንኙነት ላይ የሚደረግ ቁጥጥር አለመኖሩን ዕውቅና በመቸር ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 61 ላይ ደግሞ ማንኛውም ሰውና የግል መኖሪያ ቤት በሕግ መሠረት ካልሆነ በስተቀር እንደማይያዝና እንደማይበረበር ተደንግጓል፡፡ ከቀድሞው ሕገ መንግሥት መጠነኛ ልዩነት በማከል ጥበቃ መስጠቱን ልብ ይሏል፡፡ ከተስፋፋባቸው ጉዳዮች አንዱ ግላዊነት የሰውን አካል መጨመሩ ነው፡፡ ሌላው ለየት የሚያደርገው በጽሕፈት የመላላክ ግንኙነት የሚታገድበትን ወይም የሚገደብበትን ሁኔታ መጨመሩ ነው፡፡ መገደብን ከማገድ ሳይለይ በአስቸኳይ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ይህ መብት የተከበረ እንደሆነ ደንግጓል፡፡

በደርግ ዘመን በወጣው፣ በ1979ኙ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 43 እንደሰፈረው የኢትዮጵያውያን ሰብዕና የማይደፈር፣ መኖሪያ ቤቱ በሕግ ከተደነገገው ወይም ከባለቤቱ ፈቃድ ውጭ መግባት እንደማይቻል፣ እንዲሁም በአንቀጽ 49 ደግሞ የሚለዋወጧቸው መልዕክቶች ሚስጥርነት የተረጋገጠ ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት የተገለጸው ከ1923ቱ ጋር የተቀራረበ ነው፡፡

በሽግግር መንግሥቱ ወቅት የሰብዓዊ መብትን በሚመለከት በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር መሠረት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ ስለሆነ እንዲተገበር የተወሰነው ስለግላዊነት መብት የመግለጫው ይዘት ከላይ የቀረበው ስለሆነ ድጋሚ ማቅረብ አላስፈለገም፡፡

አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 26 ስለግላዊነት የቆመ ነው፡፡ ንዑስ አንቀጽ አንድ ማንኛውም ሰው የግላዊነት መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ፣ ይህ መብትም መኖሪያ ቤትን፣ ሰውነትንና ንብረትን እንደሚያካትትና ምርመራና ንብረትን ከመያዝ የመጠበቅ መብት ያለው እንደሆነ ያሳስባል፡፡

ንዑስ ቁጥር ሁለት በበኩሉ ማንኛውም ሰው በጽሑፍ፣ በፖስታ፣ በቴሌፎንና በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የሚፈልጋቸው ግንኙነቶች የዚሁ የግላዊነት መብቱ አካል ሆነው ጥበቃ እንዳላቸው ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ንዑስ ቁጥር ሦስት በግላዊነት መብት ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ገደቦችን የሚለይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የመንግሥት ባለሥልጣናት እነዚህን የግላዊነት መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ ያለባቸው መሆኑን፣ ብሔራዊ ደኅንነትን፣ የሕዝብን ሰላም፣ ወንጀልን ለመከላከል፣ ጤናና ሞራልን ለማስጠበቅ፣ የሌሎችን መብት ለማስከበር ሲባል አስገዳጅ ሁኔታ ሲኖርና በሕግ መሠረት ካልሆነ በስተቀር ሊገደቡ እንደማይችሉ አስፍሯል፡፡

በአሁኑ ሕገ መንግሥት የተቀመጠው የግላዊነት መብት ግላዊ ሕይወትን፣ቤትን፣ ሰብዕናንና ንብረትን ጥበቃ ያደርጋል፡፡ መረጃዎችን በተለያዩ ሁኔታዎች መለዋወጥንም እንዲሁ ይዟል፡፡ ስለሚገደብባቸው ሁኔታዎችም ከበፊቶቹ ሕገ መንግሥቶች በተለየ ሁኔታ ዝርዝር መሥፈርቶችን ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ ሕግ አውጭው አስቀድሞ ለብሔራዊ ደኅንነት፣ ለሕዝብ ሰላም ወንጀልን ለመከላከል፣ ጤናና ሞራልን ለማስጠበቅ፣ የሌሎች ሰዎች መብቶችን ለማስከበር ሲባል የሌላ ሰውን የግላዊነት መብት መገደብ አስገዳጅ የሚሆን ከሆነ ሊታገድ እንደሚችል ሕግ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ የሕጎቹ ግብ እነዚህን ማስጠበቅ ነው፡፡ 

የግላዊነት መብት የሚገደብባቸው ሁኔታዎችም በአውሮፓው መሠረታዊ ነፃነትና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ‹‹አስገዳጅ ሁኔታ›› ሲል ያኛው ‹‹ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ›› መሆን የሚሉ ናቸው፡፡

በሕገ መንግሥትም ሆነ በሰብዓዊ መብት ሰነዶች የሚገለጹ መብቶች፣ ጥቅሞችና ግዴታዎች ተፈጻሚነታቸውን ለማቀላጠፍ፣ ዝርዝር ተጠያቂነትና ኃላፊነትን ለመለየት ተጨማሪ ሕጎች ይወጡ ዘንድ ግድ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔርም የወንጀልም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከሕገ መንግሥትና ከሰብዓዊ መብት አንፃር የግላዊነት መብትን ሁኔታ ለመንደርደሪያነት ያህል ቀርቧል፡፡ ከኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በተለይም ከመረጃ ጥበቃ ጋር በተያያዘ፣ የግላዊነት መብት ላይ የተደቀኑትን ተግዳሮቶች በመዳሰስ፣ የአገራችንን የሕግ ከለላ ስስነት በሚቀጥለው ጽሑፍ የምንመለከተው ይሆናል፡፡

አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...