በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ 44 ዓመታት በገበያ ውስጥ የቆየው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለደንበኞቹ ከከፈለው የካሳ ክፍያ በከፍተኛነቱ ሊጠቀስ የሚችለውን የ95.14 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ከፈለ፡፡ ባለፉት 44 ዓመታትም ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን 12.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጀት ወደ ሥራ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ለያዘውና ከአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ለሆነው ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር የካሳ ክፍያ የከፈለው፣ ከስምንት ወራት በፊት ከሞጆ ወደ ጂቡቲ ይጓዝ በነበረ ባቡር ላይ ለደረሰበት አደጋ ነው፡፡ የምድር ባቡሩ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት በገዛው የመድን ሽፋን መሠረት ለአደጋው ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ መከፈሉ ተገልጿል፡፡
ይህ የካሳ ክፍያ ግን እንደሌሎች የካሳ ክፍያዎች በቶሎ የተከፈለ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰጠ አደጋ ስለነበረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ከኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ጋር ላለፉት ሁለት ዓመታት በዚህ የመድን ሽፋን አብረው የሠሩ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ በተለይ ሽፋኑን ለማስጀመር ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የተሳተፉበት በርካታ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰበትና የውጭ ብድርም ያለበት ስለሆነ ተገቢው የመድን ሽፋን ማግኘት ይገባዋል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ወደፊትም ደግሞ በሚያጋጥሙት አደጋዎች ላይ በቂ የሆነ ሽፋን ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ሥራ መሠራት ስለነበረበት በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሰጠበት ሽፋን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይኼ ሽፋን ሲሰጥ በተለይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመሆኑ በአገር ውስጥ አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ፣ በጠለፋ መድን ከፍተኛ ልምድና አቅም ካላቸው የጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር በማቀናጀት ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር የካሳ ክፍያው መከፈሉ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር የመድን ሽፋንን በራሱ አቅም ብቻ ሊሰጠው ስለማይችል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ከሚታወቁት የጀርመን ሙኒክ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ የአፍሪካ ሪ እና ዜብሪ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲሁም ከአገር በቀሉ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ እንዲገባለት በማድረግ ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር የመድን ሽፋን ሰጥቷል፡፡
ይህንን በማመቻቸት ሙሉ ንብረቱ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት እንዲሁም በሦስተኛ ወገን ንብረት ላይና የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ለሚያጓጉዛቸው ንብረቶች ተገቢውን ሽፋን የሚሰጥ ተገቢ ውል እንዲመቻች ማድረግ ስለመቻሉ ተገልጿል፡፡ የካሳ ክፍያውም ሊከፈል የቻለው እነዚህ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች አምነውበት በትክክል የተሟላ መሆኑን አረጋግጠው እንደሆነም ከሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዚህም ሌላ የጉዳት መጠኑን ለማስላት የሁሉንም ተቋማት ባለሙያዎች በማቀናጀት በመግባባት የተሠራ ነበርም ተብሏል፡፡ ንብረቱን ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና የውጭ ልምድ ያላቸውን የቻይና ባለሙያዎችን ተሳትፎም የጠየቀ እንደነበር የሚያመለክተው የዚህ ካሳ ክፍያ፣ አንዳንዶቹ ዕቃዎች ወደ ውጭ ተልከው ሊጠገኑ የሚችሉበት ሁኔታ የሚጠይቅ እንደነበር ተገልጿል፡፡ እንዲህ ያሉ የተቀናጁ ሥራዎች ተሠርተው መጨረሻ ላይ የደረሰውን የንብረት መጠን ለመተካት የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 95.14 ሚሊዮን ብር መሆኑን ከኢትዮ የጂቡቲ ምድር ባቡር ጋር በመግባባትና የጠለፋ መድን ሰጪዎችም ይህንን በማረጋገጣቸው የጉዳት ካሳ ክፍያውን በቼክ አስረክበዋል፡፡
የኩባንያውን አንደኛ ዓመት አክብረው ሁለተኛውን ዓመት በጀመሩ በሦስተኛው ወር የገጠማቸው አደጋ አስደንጋጭ እንደነበር የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ጥላሁን ሳርካ (ኢንጂነር) ጠቅሰው፣ አሁን በዚህ መንገድ መካሳቸውን አመስግነዋል፡፡
ከሞጆ ወደ ጂቡቲ 48 ኮንቴይነሮችን ጭኖ በመሄድ ላይ የነበረው ባቡር አደጋ ሲደርስበት ሁላችንም ተደናግጠን ነበር ያሉት አቶ ጥላሁን፣ እንዲህ ሲሆን የመጀመርያ በመሆኑ ድንጋጤ መፍጠሩን አስታውሰዋል፡፡
አደጋው በደረሰበት ጊዜ በውስጡ አራት ፌዴራል ፖሊሶችና ዘጠኝ የባቡር ሠራተኞች እንደበሩ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ሦስት ቻይናውያን ሦስት ጂቡቲያውያንና ሦስት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ማንም ሰው ላይ ጉዳት ያልደረሰ ቢሆንም፣ በሁለት ሎኮሞቲቮችና ኮንቴይነር የጫኑ 19 ተጎታጆች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡
የጉዳቱ መንስዔም በወቅቱ የነበረው ጎርፍ ባቡሩን ከሐዲዱ በማሳት በመገልበጡ እንደሆነም የአደጋው ዘገባ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር አጠቃላይ የመድን ሽፋን ለመስጠት የሚያስችለውን አሠራር ለመዘርጋት ብዙ መልፋቱን የተገለጸ ሲሆን፣ የመድን ሽፋኑን በመግዛቱ ግን የደረሰበትን አደጋ ለመተካት የሚያስችለውን አሳማኝነት አስኝቷል፡፡ አቶ ጥላሁንም ‹‹በቀላሉ ዛሬ ላይ አልተደረሰም፤›› በማለት በዕለቱ የተበረከተላቸውን የጉዳት ካሳ ሁሌም በመድን ድርጅት ላይ እምነት እንድናሳድር አድርጓል ብለዋል፡፡ ይህ ካሳ ባይገኝ ንብረቱን ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ እንደነበር በመግለጽም፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን አመስግነዋል፡፡ የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥት የጋራ ኩባንያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ 75 በመቶ ጂቡቲ ደግሞ 25 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባለፉት 44 ዓመታት ለደንበኞቹ የከፈለው የጉዳት ካሳ 12.3 ቢሊዮን ብር እንደነበረ ገልጿል፡፡ የኩባንያው የመድን ሽፋንም በዓመቱ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የሰጠው የመድን ሽፋን ወይም ድርጅቱ የተሸከመው የሥጋት መጠን ከ14.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ስለመድረሱም አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የመድን ድርጅት በአሁኑ ወቅት ከሚንቀሳቀሱት 17 የመድን ድርጅቶች ውስጥ ብቸኛው የመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪውም ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የያዘ እንደሆነ ይታመናል፡፡