Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ባንክ አዳዲስ የቦርድ አባላትን መረጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች ባንኩን በቦርድ ዳይሬክተርነት ለማገልገል በዕጩነት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ውስጥ የቀድሞው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የሰነዶችና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት መመረጣቸው ተገለጸ፡፡ ባንኩ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር እንደሚሰይምም ይጠበቃል፡፡

ባንኩ ባለፈው ታኅሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ምርጫ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁት ስድስት ነባር የቦርድ አባላት ምትክ አዳዲስ የቦርድ አባላትን ለመሰየም በዕጩነት የቀረቡት ተወዳዳሪዎች 22 ነበሩ፡፡ የባንኩ አስመራጭ ኮሚቴ ይፋ ባደረገው ውጤት፣ ከ22ቱ ተወዳዳሪዎች ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት የመጀመርያውን ደረጃ የያዙት የቀድሞ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ታደሰ ናቸው፡፡

አቶ ይርጋ በዚህ ምርጫ 21.27 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ በማግኘት ባንኩን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ በድጋሚ የተመረጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ይርጋ የምርጫ ዘመኑን ያጠናቀቀውና አሁን ሥራ ላይ ያለው ቦርድ አባልና ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን፣ ዳግም መወዳደር የሚችሉ በመሆኑ በዕጩነት ቀርበው በዕለቱ በተደረገው ምርጫ ከፍተኛውን ድምፅ ሊያገኙ ችለዋል፡፡

ከአቶ ይርጋ ቀጥሎ ከፍተኛ የባለአክሲዮኖችን ድምፅ ያገኙት ባንኩን በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ባለአክሲዮኖች ይሁንታ የሰጡዋቸው የቀድሞ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ናቸው፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ሌተና ጄኔራል 20.46 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ድምፅ አግኝተው፣ በአንበሳ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ለማገልገል የሚያስችላቸውን ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በቢዝነስ ዓለም ከዚህ ቀደም የተቋቋመውንና ቢጂአይ ኢትዮጵያ የጠቀለለውን ማኅበር በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ ሁለት ከፍተኛ ተመራጮች ሌላ አስመራጭ ኮሚቴው ውጤታቸውን ከገለጻቸው ውስጥ አቶ ኃይሌ በረሃ 19.78 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ፣ ግኡሽ ብርሃነ (ዶ/ር) 18.75 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ፣ ታደለ ሐጎስ (ዶ/ር) 16.98 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ፣ ገብረ ሕይወት አገባ (ዶ/ር) 16.98 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ፣ አቶ ፀጋይ ተጠምቀ 16.07 ሚሊዮን የአክሲዮኖችን ድምፅ፣ አቶ ተወልደ አስፋው 15.97 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ፣ አቶ ዓለም አስፋው 12.89 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ፣ አቶ ፋሲል ታደሰ 10.72 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅና ፀጋ ብርሃን መኮንን (ዶ/ር) 10.73 ሚሊዮን የአክሲዮኖች ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በዕለቱ በተደረገው ምርጫ ከ22ቱ ተወዳዳሪዎች ዝቅተኛ ድምፅ ተብሎ የተገለጸው 805,841 የአክሲዮኖች ድምፅ ነው፡፡

ከተመራጮቹ ውስጥ ከፍተኛውን ድምፅ ያገኙት 11 ግለሰቦች በቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ውጤታቸው የሚፀናው ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲያፀናው ነው፡፡ ከባንኩ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ባንኩን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ጣሰው ወልደሃና (ፕሮፌሰር) የኃላፊነት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ፣ አዳዲስ አባላት የተካተቱበት ቦርድ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ይሰይማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አንበሳ ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 695 ሚሊዮን ብር ማትረፉ መገለጽ አይዘነጋም፡፡ ባንኩ ከአራት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ሲኖሩት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 247 ቅርንጫፎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች