Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው ባንኮች የሚበደሩት ገንዘብ በጨረታ አቀረበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች የሚገጥማቸውን ጊዜያዊ ገንዘብ እጥረት ለመሸፈን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይበደሩበት የነበረውን መንገድ በማሻሻል፣ በጨረታ ለማበደር የሚያስችለውን አሠራር በመዘርጋት ባለፈው ዓርብ ታኅሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. 5.5 ቢሊዮን ብር በማቅረብ አጫርቷቸዋል፡፡

ባንኮች ለጊዜያዊ ክፍያዎች የሚፈልጉትን ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ በሚባል ወለድ ይበደሩ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን በተለየ መንገድ ባንኮቹ የሚፈልጉትን ብድር ሊከፍሉ በሚችሉት የብድር ወለድ መጠን አወዳድሮ እንዲበደሩ አመቻችቷል፡፡

ቀደም ባለው አሠራር ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሲበደሩ የብድር መክፈያ የወለድ መጠን፣ በባንኮች የከፍተኛ የብድር ወለድ ምጣኔያቸው ብድር እንዲያገኙ የሚያደርግ ነበር፡፡

ከዓርብ ጀምሮ የተጀመረውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በራሱ ተነሳሽነት በጨረታ ብድር እንዲያገኙ በሚያስችለው አሠራር፣ እያንዳንዱ ባንክ የሚፈልገውን ገንዘብ የሚበደርበትን የብድር ወለድ ምጣኔ በመወዳደሪያነት በማቅረብ የሚፈጸም ነው፡፡

ይህንንም አሠራር ለመተግበር ባለፈው ዓርብ የመጀመሪያው ጨረታ የተካሄደ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በዕለቱ በጨረታ ያቀረበውን የ5.5 ቢሊዮን ብር  ብድር የወለድ መጠን መነሻ ዘጠኝ በመቶ በማድረግ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት 17 ባንኮች የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ለመበደር አሸናፊ ያደርገናል ያሉትን የብድር ወለድ መጠን በመጥቀስ መጫረታቸው ታውቋል፡፡

እንዳገኘነው መረጃ ከ5.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ ብድሩን ለማግኘት ከተጫረቱት 17ቱ ባንኮች ውስጥ አንድ ባንክ የጨረታ ሰነዱ ሲሰረዝበት፣ 16ቱ ባንኮች ግን የጨረታ ሰነዳቸው አልፎ አሸናፊ ያደርገናል ባሉት የወለድ መጥሪያ ምጣኔ መሠረት የሚፈልጉት የገንዘብ መጠን ማግኘታቸው ታውቋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ በዚህ ጨረታ አንዳንድ ባንኮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመወዳደሪያ ወለድ መጠን ብሎ ያስቀመጠውን ዘጠኝ በመቶ ያስገቡ ሲሆን፣ ከዘጠኝ በመቶ በላይ ወለድ እንከፍላለን ብለው ከተወዳደሩት ውስጥ በከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ብድሩን ለማግኘት አንድ ባንክ 15.2 በመቶ ዋጋ መስጠቱ ታውቋል፡፡

በዚሁ መሠረት በዕለቱ በተደረገ ጨረታ በአማካይ ብድሩን ለማግኘት የቀረበ የብድር ወለድ ምጣኔው 10.2 በመቶ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ብድር በሁለት ወር ውስጥ የሚመለስ ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም ባንኮች ጊዜያዊ የክፍያ ችግር ሊያጋጥማቸው ቢቻል ይህንን ክፍተት ለማሟላት ነው፡፡ ባንኮች እንዲህ ባለው መንገድ ከብሔራዊ ባንክ ሲበደሩ ገንዘቡን ለብድር እንዲያውሉት ሳይሆን ለጊዜያዊ ክፍያ እንዲያውሉት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረውም አሠራር ቢሆን ባንኮች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተመሳሳይ ብድር ሲወስዱ ከተለያዩ ክፍያዎቻቸው ጋር ተያይዞ የሚቀርብላቸውን በብድር በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ይመልሳሉ፡፡

የዚህ ዓይነቱ ብድር ዓላማ ጊዜያዊ ክፍያዎችን ለመፈጸም በመሆኑ ለደንበኞች የሚያበድሩት አይሆንም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ለባንኮች ያቀረበው የብድር አሰጣጥ ለየት የሚያደርገውም ባንኮች ለጊዜያዊ ክፍያዎች የሚፈልጉትን ብድር በጨረታ እንዲወስዱ ማድረጉ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ባንክ ብድሩን ሲሰጥ የሚያበድራቸው ባንኮች ብድር ሲሰጡ በሚያስከፍሉት ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ታስቦ እንደነበር የሚገልጹት የባንክ የሥራ ኃላፊዎች፣ ይህም አንድ ባንክ የቢዝነስ ዘርፍ ብድር ሲሰጥ በከፍተኛ ወለድ የሚያስከፍለው 18 በመቶ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ለአጭር ጊዜ ብድር ለባንኮች ከሰጠ በኋላ  ብድሩን የሚቀርበላቸው በዚሁ ከፍተኛ በሚባለው የባንኮች የብድር ወለድ መጠን ወይም 18 ተሰልቶ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ የሚያደርገው ብድሩን መልሰው ለብድር እንዳያውሉት ለማድረግ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራሩ በተለየ መንገድ ለጊዜያዊ ክፍያዎች ለባንኮች ይሰጥ የነበረውን ብድር እንዲህ ባለ መንገድ ለመስጠት መወሰኑ፣ ለባንኮች ጥቅም ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የብድር ወለድ ምጣኔያቸው ልክ ብድሩን እንዲመልሱ ያስገድዳቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን አሰጣጡ በጨረታ በመሆኑ የሚከፍሉት የብድር ወለድ ምጣኔ እንዲቀንስላቸው ያደርጋል፡፡

በዓርቡ ጨረታ ባንኮች ለሚበደሩት ብድር እንከፍላለን ብለው ያቀረቡት አማካይ ዋጋ 10.2 በመቶ በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑንም ያሳያል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላ የግል ባንኮች ከፍተኛ ተብሎ የሚቀመጠው የብድር ወለድ መጠናቸው ከ17 እስከ 20 በመቶ በመሆኑ ሊጠቅማቸው ይችላል ተብሏል፡፡

ባንኮቹ እንዲህ ባለው መንገድ የሚወስዱትን ገንዘብ ካልከፈሉ የ20 በመቶ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያለውን አሠራር በቀጣይም የሚቀጥልበት እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ከወቅታዊ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ ባንኮች ሊያጋጥማቸው ለሚችል የገንዘብ እጥረት መሸፈኛ ለማድረግ ወደ 11 ቢሊዮን ብር የተመደበ ስለመሆኑ የምንጮች መረጃ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች