Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሸማቾች ማኅበራት ሊጠናከሩ ይገባል

ገበያን በማረጋጋቱ ረገድ ዓይነተኛ ሚና አላቸው ተብለው የሚታመኑ አሠራሮችና ለዚሁ ዓላማ ስኬት የሚቋቋሙ ተቋማትና ማኅበራቶች አሉ፡፡ በተለይ የግብይት ሥርዓቱን ሆን ብሎ ለመበረዝ በሚደረጉ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚታዩ የተለያዩ አማራጮች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህን አማራጮች በመጠቀም ሸማቾችን የታደገ ሥራ ሊሠራ እንደሚችልም ይታወቃል፡፡

ሸማቾች ላልተፈለገ ብዝበዛ እንዳይጋለጡና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱ ለማስቻል በነፃ ገበያ ሥርዓት ሊገኝ ከሚችለው ዕድል ባሻገር፣ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ያስችላሉ ተብለው ከሚታመኑባቸው ውስጥ የሸማቾች ማኅበራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሸማቾች ማኅበራት ለአባሎቻቸው ወይም ባሉበት አካባቢ ለሚኖሩ ሸማቾች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችንና የፍጆታ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡

እነዚህ የሸማቾች ማኅበራት በመደበኛው ገበያ ባነሰ ዋጋ ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመንግሥት የሚደረግባቸው ድጋፍ አለና የትርፍ ሕዳጋቸውን አጥብበው ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ በማድረጋቸው በገበያ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን የዋጋ ግሽበት ከመታደግ ባለፈ፣ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በዋጋ ጭማሪ እንዳይጎዳ የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎም ይታመናል፡፡

የሸማቾች ማኅበራት ሚና ሊኖረው የሚችለው ጠቀሜታ በብዙ መልኩ የሚገለጽ ቢሆንም፣ የሚጠበቅባቸውን ሥራ እየሠሩ ያለመሆኑን ግን ለመናገር ምስክር የሚያሻው አይደለም፡፡

ነገር ግን እነዚህ ማኅበራት በተቋቋሙበት ዓላማ ልክ ግልጋሎት እንዲሰጡ፣ በየጊዜውም አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ሆነ እንዲሠሩ እየተደረጉ ያለመሆኑንም በቀላሉ እንገነዘባለን፡፡ የበዙት የሸማቾች ማኅበራት እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ዘመናዊ አሠራርን የተከተለ የሸማቾቹን የልብ ትርታና በየወቅቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ከግንዛቤ ያስገባ አሠራር አልዘረጉም፡፡ የፋይናንስ አያያዛቸው፣ ከየት ተነስተው የት መድረስ እንዳለባቸው እንኳን በተገቢው መንገድ ዕቅድ አውጥተው የሚሠሩ አሉ ወይ ካልንም ከጥቂቶች በስተቀር በዚህ መንገድ እየተጓዙ አይደለም፡፡

በአብዛኛው ኮታን መሠረት ካደረገ የምርት አቅርቦት ተሻግረው በራሳቸው መንገድ ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶችን በመያዝ ለሸማቹን ሲያለግሉ አይታዩም፡፡ ዘወትር ከመንግሥት የሚቀርብላቸውን ዘይትና ስኳር ከማቅረብ ባለፈ፣ የገበያ ትስስር ፈጥረው ሌሎች ምርትና ሸቀጦችን ለማቅረብ ወገቤን የሚሉ በአብዛኛው ተሻጋሪ ራዕይ ይዘው የማይሠሩ ናቸው፡፡ በስኳርና ሌሎች መሠረታዊ ምርችን የሚያሠራጩበት መንገድ ሥርዓት የሌለው አንዳንዴም የተበላሸ አሠራር የሚታይበት ነው፡፡

እነዚህን ማኅበራት የሚመሩ አካላት የብቃት ጉዳይም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ማኅበራቱን አስፈላጊነት በመረዳት አበርክቷቸውን ከፍ ሊያደርግ በሚችል ደረጃ እንዲዋቀሩና ተገቢውን ቁጥጥር የሚያደርግ ጠንካራ የሚባል አካል አለመኖሩ እንደችግር የሚታይ ነው፡፡

ነገር ግን በተለይ የዋጋ ግሽበት በሚበረታበትና ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች በሚስተዋሉበት ወቅት፣ የሸማቾች ማኅበራት ገበያን የማረጋጋት ሚናቸው ቀላል ያለመሆኑን ያህል ግብራቸው ሲታይ በሚፈለገው ደረጃ እየሠሩ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡

ሸማቾች ማኅበራት ምን ያህል ዋጋ ሊያረጋጉ፣ ሸማቾችንም መታደግ እንደሚችሉ ከምንገነዘብባቸው አንዱ የሥጋ አቅርቦት ነው፡፡ ሉኳንዳ ያላቸው የሸማቾች ማኅበራት የሚሸጡበት ዋጋ ከሌሎች ልኳንዳ ቤቶች በሁለትና በሦስት እጅ ያንሳል፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ ቢበዛ 150 ብር ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዱ ጋር ከዚህም ያነሰ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አዋጥቷቸው ይሸጣሉ፡፡ በተለይ የበዓላት ሰሞን እነዚህ ልኳንዳ ቤቶች በሸማቾች ሲጨናነቁ የምናይበት ዋና ምክንያት፣ ከልኳንዳ ቤት ከግማሽ ዋጋ በላይ ቅናሽ ስለሚያገኙ ነው፡፡ እነዚህ የሸማቾች ሥጋ ቤቶች ባይኖሩ የመደበኛ ልኳንዳ ቤቶች ሲሳይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ወይም በአማራጭ እጦት ግማሽ ኪሎ ገዝቶ በዓልን ማሳለፍ ይቻል እንዳልነበር ያሳያል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው መንገድ ገበያውን ለማረጋጋት የሸማቾች ማኅበራት ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማቅረብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሊታገዙ ይገባል፡፡ አሠራራቸውን በማስተካከል ሸማቾች አማራጭ እንዲኖራቸው በቀላሉ መሥራት የሚቻልበት ዕድል አለና፣ ዘወትር ባልተገባ ዋጋ እየተቆነጠጠ ነው ብሎ ከመማረር ባሻገር ሸማቾችም ጠንካራ የሸማቾች ማኅበር እንዲኖራቸውና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጥ የሸማች ማኅበር ይኑረን ማለት አለባቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ ያሉትን ማኅበራት በማጣናከሩ ረገድ ሁሉም የበኩሉ ማበርከት አለበት፡፡ እንደ አገር ዋጋን ማረጋጋት ብቻ ሳይሆን ጤነኛ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠርም ያበረታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጤናማ የሆነ ምርት እንዲያቀርብ ማድረግ ይቻላል፡፡ አርቀን ካሰብነው እየተጠናከሩ የሚሄዱ ማኅበራት ሊፈጥሩ የሚችሉት የሥራ ዕድልም ይኖራል፡፡ ስለዚህ አሁን ካሉት የሸማቾች ማኅበራት ውስጥ በተሻለ የሚሠሩትን የበለጠ እንዲሠሩ በተለመደው መንገድ እየተጓዙ ያሉትንም አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ በማድረግ በማውረድ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

እዚህ ላይ የሸማቾች ማኅበራቱን በማዘመን አቅርቦታቸውን በማሳደግና ተአማኒ የሒሳብ አያያዝ ማድረጉ ብቻ የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት፡፡ የቱንም ያህል አሠራራቸውን ቢያዘምኑ ጨዋ ሸማቾችን ያስፈልጋሉና፣ በድጎማ የሚመጡና በሸማቾች ማኅበራት የሚሠራጩ ምርቶችን ተረክቦ በጥቁር ገበያ የሚያሻግሩ ሸማቾች ካሉ ነገሩ ተበላሸ ማለት ነው፡፡ እንደ ሸማች የሚበቃንን በልካችን መሸመት መልመድ ይገባል፡፡ በመሆኑም ጨዋ የሸማቾች ማኅበራት የሽያጭ ሠራተኞች እንዲኖሩ መሠራት አለበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት