Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኒያላ ኢንሹራንስ ከ184 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን ከተቀላቀለ 25ኛ ዓመቱን የያዘው የኒያላ ኢንሹራንስ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል ከፍተኛ የሆነውን የ184.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንና የኩባንያውንም ካፒታል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ እንዳሳደገ ገለጸ፡፡

ኩባንያው የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መግለጫው፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው 184.3 ሚሊዮን ብር በኢንዱስትሪው ትልቁ ነው ብሏል፡፡ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ከማል መሐመድ ታኅሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተካሄው የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ጉባዔ ላይ እንደገለጹት፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት የተገኘው ያልተጣራ ትርፍ ኩባንያቸውን በኢንዱስትሪው ግንባር ቀደም አድርጎታል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት የተመዘገበው ትርፍ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ24.7 ሚሊዮን ብር ወይም የ15.5 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ‹‹ይህ ትርፍ ለሦስተኛ ጊዜ በኩባንያውም ሆነ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ታሪክ ከተመዘገቡ ትርፎች ሁሉ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል፤›› በማለት አቶ ከማል የኩባንያቸውን ዓመታዊ የትርፍ ግኝት ገልጸዋል፡፡  

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ያሬድ ሞላ በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው በነደፈውና በተከተለው ጠንካራ የንግድ ዕድገት ስትራቴጂ፣ እንዲሁም ጥንቃቄ የተሞላበት የሥጋት አስተዳደር ዘዴዎች በሒሳብ ዓመቱ ለተገኘው ውጤት ዓይነተኛ አስተዋጾኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የካሳ ክፍያ ወጪ በከፍተኛ መጠን በመናር ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ያሬድ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ የተለያዩ ቴክኒካዊ አሠራሮችን በመተግበር፣ በማስተዋወቅና ለደንበኞች ተከታታይ ሥልጠናዎች በመስጠት፣ ወጪዎቹን ለመቆጣጠር በመቻሉ በሒሳብ ዓመቱ የካሳ ክፍያውን ቀንሷል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ መድን ቢዝነስ የ131.3 ሚሊዮን ብር፣ በሕይወት መድን ደግሞ የ30.7 ሚሊዮን ብር፣ በአጠቃላይ የ162 ሚሊየን ብር ካሳ እንደከፈለ የሚገልጸው ኒያላ ኢንሹራንስ፣ ይህ የክፍያ መጠን ባለፈው ዓመት ከተከፈለው ጋር ሲነፃፀር የስድስት በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ይጠቁማል፡፡

የኩባንያው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያትተው የኩባንያው ጠቅላላ የሀብት መጠን አምና ከነበረበት 1.9 ቢሊዮን ብር ወደ 2.1 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር የ7.5 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን ጠቅላላ ጉባዔው የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ416 ሚሊዮን ብር ወደ 530.4 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል የቀረበውን ሐሳብ በመቀበል አፅድቋል፡፡

ካፒታሉን ከማሳደግ ባሻገር የኩባንያውን ትርፋማነትና በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን የተወዳዳሪነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የኩባንያውን የሰው ኃይል አቅም በበቂ ሁኔታ መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ፣ በየደረጃው ያሉ ሁሉም ሠራተኞች ለሥራ ብቁ የሚያደርጓቸውን ሙያዊ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ከማል አስረድተዋል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመቅረፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ በምልምል ተመራቂ ሥልጠና በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፍ ከየትምህርት ተቋማቱ ተመርቀው የወጡ ምሩቃንን በመመልመልና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር ለአራተኛ ጊዜ ለማሠልጠን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ እስካሁን በነበረው ጉዞ ከ80 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎች ማፍራቱ ተገልጿል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘው እንደጠቆሙትም፣ ለደንበኞች ምቹ የሆኑ አዳዲስ ምርቶችን ለገበያ የማቅረብ ሥራዎችን፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና በሁሉም ዘንድ ተመራጭ በሚያደርገው መንገድ ለመቅረብ ሥራዎች በመሥራት ላይ መሆናቸውን፣ በተለይ የኢንሹራንሱ ዓለም ቴክሎጂን መሠረት በማድረግ በፍጥነት በመቀየር ላይ በመሆኑ፣ በዚህ አዲስ መንገድ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ኩባንያውን የመቀየርና የማዘመን ሥራ ዝግጅት ላይ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች