Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጋር የሚተሳሰር መርኃ ግብር ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳሸን ባንክ ከወቅታዊው አገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር ትስስር ሊኖረው ይችላል ያለውንና የአገሪቱን ዜጎችን የሚያሳትፍ ግዙፍ ማኅበራዊ ኢንቨስትመንት መርኃ ግብር ይፋ ማድረጉን ገለጸ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ታለንት ፓዎር ሲሪየስ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት፣ ሥራ ፈጠራን በማበረታታትና ክህሎት ላላቸው ዜጎች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ፣ የሥራ አጥነትን በመቀነስ ድህነትን ለማስወገድ ለሚደረገው አገራዊ እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለመወጣት የሚያስችል መሆኑንም በዚሁ ጉዳይ ላይ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ ባንኩ መንግሥት ከቀየሰው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ትግበራ አንፃር የራሱን ድርሻ በመወጣት በአርዓያነቱ ቀዳሚ እንደሚሆን የገለጹት ባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ይህ መርኃ ግብር በዓመት እስከ ስድስት ሺሕ ወጣቶችን ለመደገፍ የሚችል መሆኑ ነው ተገልጿል፡፡ ባንኩ ይህንን ሥራ በሚጀምርበት የ2012 ሒሳብ ዓመት በተመረጡ ስድስት ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ተመልምለው የሥራ ፈጠራ ክህሎትና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ይሰጣቸዋል። ሥልጠናውን ያገኙት ዜጎችም በአማካሪ ድርጅት እየታገዙ የቢዝነስ ክለብ ያቋቁሙና፣ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ድጋፍ ከባንኩ እንዲያገኙ የሚያስችለውን አሠራር ለመተግበር 100 ሚሊዮን ብር መመደቡም ታውቋል፡፡ ይህ ገንዘብ እነዚህን ወጣቶች ለመመልመልና ሥልጠና ለመስጠት በአጠቃላይ የአቅም ግንባታን ለመፍጠር በሚያስችሉ ተግባራት ለሚያስፈልግ ወጪ የሚውል ሲሆን፣ ለተመረጡ የሥራ ፈጣሪዎችና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚቀርብ እንደሆነ ተመልቷል፡፡  

ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆነ መልኩ ባንኩ በቴሌቪዥን ሥርጭት በየሳምንቱ የሚተላለፍ፣ በሥራ ፈጠራና ቢዝነስ ክህሎት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሳምንታዊ ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ውድድር አሸናፊዎችም የማበረታቻ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን፣ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አሸናፊ ሐሳብ ያቀረቡ ሥራ ፈጣሪዎች ደግሞ ለወደፊት ለመጀመር ለሚያስቡት የንግድ ሥራ፣ የፋይናንስ ድጋፍ በባንኩ እንደሚደረግላቸውም  ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

‹‹የኢትዮጵያ ታለንት ፓዎር ሲሪየስ›› የተባለው ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ስድስት ዋና ዋና መገለጫዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም የሥራ ፈጠራ ሥልጠና፣  የጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም ግንባታ የከፍተኛ ትምህርት የፋይናንስ ድጋፍ መርኃ ግብር፣ የፋይናንስ ተደራሽነት መርኃ ግብር፣ የቢዝነስ ክለብ ምሥረታ፣ የገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ባንኩ ያደረገው ጥናት መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር የገንዘብ እጥረት ያለ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ወጣቶችን አሠልጥኖ ውጤታማ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ የመስጠት ዓላማ ያለው መሆኑን ከአቶ አስፋው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ ወጣቶች እርስ በርሳቸው እንዲማማሩ የሚደረግበት፣ ሲጠነክሩ ደግሞ የራሳቸውን ኢንተርፕራይዞች ኖሯቸው ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ የሚገኙበት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ወደ ባንኩ የሚመጡትንም ደንበኞች በማፍራት የራሱ ዕድል ይኖረዋል፡፡

የሥራ ፈጣሪዎችና  አነስተኛ ኢንተርፕራይዞቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ወደ ገበያ አውጥተው እንዲሸጡ ልምድ ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው የገበያ ዕድል ሁሉ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሠራር እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ዳሸን ባንክ ይህንን ፕሮግራም ለመተግበር ለረዥም ጊዜ ሲዘጋጅበት እንደነበርም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች