ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትና የፋይናንስ አገልግሎትን ከማስፋፋት አንፃር ሊተገበሩ ይገባቸዋል ተብለው ከሚታመንባቸው አገልግሎቶች ገና እየተተገበሩ አይደለም፡፡
ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓትን ከማስፋት አንፃር እየተሞካከሩ ያሉ አዳዲስ አሠራሮች ያሉ ቢሆንም፣ አሁንም ግን ገና ብዙ የሚቀሩ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ ከዛሬ 11 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲቋቋም በፍጥነት እተገብረዋለሁ ብሎ አስተዋውቋቸው ከነበሩ የዘመናዊ ግብይት መገለጫዎች መካከል አንዱ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡
ነገር ግን ይህንን አገልግሎት ሳይጀምር ከቆየ በኋላ በዚህ ሳምንት በአንድ ምርት ላይ የሚንተራስ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት በይፋ መጀመሩን አስታውሷል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንደገለጸውም ይህ አዲስ አገልግሎት ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ከታኅሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህንንም አገልግሎት በበቆሎ ምርት የሚጀምር ሲሆን፣ የበቆሎ ምርት ወደ ምርት ገበያው መጋዘን ለሚያስገባ ማንኛውም አባል ወይም ደንበኛ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ነው፡፡
የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አንድ አምራች ወይም ተገበያይ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን ምርቱን በማስገባትና ደረሰኙን እንደማስያዣ በመጠቀም፣ ከምርት ገበያው ጋር በጣምራ ከሚሠሩ ባንኮች የብድር አገልግሎት የሚያገኝበት አሠራር ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት አርሶ አደሮችን ያቀፉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖች፣ የግብርና ምርት አቀነባባሪ ድርጅቶችና አቅራቢዎች የአጭር ጊዜ ብድር የሚያገኙበትን የመጋዘን ብድር አገልግሎት ለመጀመር ላለፉት 18 ወራት ሲያከናውን የነበረውን ዝግጅት በማጠናቀቅ፣ ወደ ሥራ መግባቱን የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ገልጸዋል፡፡ ይህንን አገልግሎት በቡሬና ነቀምት ቅርንጫፎች የሚጀምር ሲሆን፣ በቀጣይነትም ሌሎች ምርቶችን በማከል አገልግሎት የሚሰጥበትን ቅርንጫፎች ቁጥር እንደሚያሳድግ ታውቋል፡፡
የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ከዚህ በፊት ምርቱ ለግብይት እንደደረሰ መሸጥ ግዴታ ውስጥ ይገባ የነበረውን አርሶ አደር፣ ጥሩ ዋጋ ባገኘ ጊዜ በመጋዘን ያስቀመጠውን ምርት በምርት ገበያው በኩል በመሸጥ ብድሩን መክፈል ወይም ከራሱ ገንዘብ መክፈል የሚያስችለው መሆኑ ተገልጿል፡፡ የተሸጠው ምርት ከተበደረው ዋጋ በላይ ካወጣ የወሰደው ብድር ተቀናሽ ተደርጎ፣ ቀሪው ለምርቱ ባለቤት ወይም ለተበዳሪው ተመላሽ እንደሚሆን አገልግሎቱን በተመለከተ ከተሰጠ ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመጋዘን ብድር አገልግሎት የሚያገኙ ተበዳሪዎች መያዣ እንዲሆን ካስገቡት ምርት ውጭ ሌላ ንብረት ለመያዣነት የማያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የራሳቸው የሆነ የምርት ማከማቻ መጋዘን እንዲኖራቸውም አይጠበቅባቸውም፡፡ ይህ አሠራር ለባንኮች አዲስ የብድር መስክ ከመፍጠሩም በላይ ምንም ዓይነት የሰነድ ልውውጥ በኢትዮጵያ ምርት ገበያና በባንኮች መካከል ሳይካሄድ፣ ሁሉም ሒደት በኤሌክትሮኒክ የቀጥታ ግንኙነት የሚፈጸም መሆኑን የምርት ገበያው መረጃ ያስረዳል፡፡ አቶ ወንድማገኝም በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ይህ አገልግሎት አንድ አምራች ወይም ተገበያይ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን ምርቱን በማስገባትና የሚቀበለውን የመረከቢያ ደረሰኙን እንደ ማስያዣ በመጠቀም፣ ከምርት ገበያው ጋር በጣምራ ከሚሠሩ ባንኮች ብድር የሚያገኝበት የአሠራር ሥርዓት የሚፈጠር ነው፡፡
በዚህም ተበዳሪው አርሶ አደር፣ አቅራቢ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የእርሻና ኢንዱስትሪ ተሳታፊዎች መያዣ እንዲሆን ካስገቡት ምርት ውጭ ሌላ ንብረት ለመያዣነት ሳይጠበቅባቸው የመጋዘን ደረሰኙን በመጠቀም የሥራ ማስኬጃና ማስፋፊያ ገንዘብ ወይም ካፒታል የሚሆን የአጭር ጊዜ ብድር እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ እንዲሁም ምርቱ በምርት ገበያው መጋዘን ለሽያጭ በሚቀርብበት ጊዜ ለሚደርስ ማንኛውም የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋ ምርት ገበያው ሙሉ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአገልግሎቱ ስምንት በመቶ የወለድ መጠን ያስከፍላል፡፡ ለአንድ ተበዳሪ ብድሩን ተመላሽ የሚያደርግበት ቀን ገደብ ለሻጭ ወይም ለአቅራቢ 90 ቀናት ወይም ሦስት ወር ሲሆን፣ ለገዢ ደግሞ 60 ቀናት የሚሰጥ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህንን አዲስ አሠራር ሥራ ላይ ለማዋል ምርት ገበያው ቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ስለነበረበት የበቆሎ ምርት የግብይት ኮንትራት ክለሳ፣ ከባንክ ጋር የብድሩን ሥርዓት የሚቀላጠፍበት የኤሌክትሮኒክ መስመር ዝርጋታ፣ የመጋዘን ዝግጅት፣ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የመፍጠርና የመሳሰሉት ተግባራት መሠራታቸውን ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በዕለቱ የመጋዘን ደረሰኝ ብድርና አገልግሎት በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ሥርዓት በአብዛኛው አርሶ አደር እጅ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ የግብርና ምርቶች የብድር ማስያዣ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉበትን አሠራር የሚያመቻች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማሻሻልና አርሶ አደሩን የዘመናዊ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድርግ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ሥርዓት መተግበር ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ መንግሥት የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል በማሰብ ያወጣውን የተንቀሳቃሽ ንብረቶች ማስያዣ አዋጅ፣ በግብርናው ዘርፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ወሳኝና ቀዳሚ ዕርምጃ ስለመሆኑም ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ሥርዓቱ ተግባራዊ መሆን የምርት ገበያው የተቋቋመለትን ለውጭ ገበያ ከሚውሉ ምርቶች ባሻገር፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችንም የዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ለማሳካት የራሱ ሚና እንዳለውም የይናገር (ዶ/ር) ገለጻ ያስረዳል፡፡
አገልግሎቱ የአርሶ አደሩን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና የአቅራቢዎችን የገበያ አማራጭ ከማጎልበት ባሻገር፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚኖራቸውን የመወዳደር አቅም በመጨመር ለምርቶቻቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ይረዳል ተብሏል፡፡ በአገልግሎቱ ተሳታፊ የሚሆኑ ባንኮች የደንበኛ ቁጥራቸውን ከፍ በማድረግ በብድር አገልግሎቱ የሚያገኙትን ተጠቃሚነት እንደሚያሰፋም ተገልጿል፡፡
‹‹እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያለምንም መስተጓጎል በመከናወን ላይ የሚገኝ የክፍያና ርክክብ ሥርዓት አለው፡፡ ይህ ስኬት ከባንኮች ጋር ባለን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ጥልቅ የሥራ ግንኙነት መሠረት የተገኘ ነው፤›› ያሉት አቶ ወንድማገኝ፣ አሁን በበቆሎ የሚጀመረውን አገልግሎት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የመጋዘን ብድር አገልግሎትን አሁን በጋራ ለማከናወን ስምምነት ላይ በመደረሱ በዚሁ መሠረት ሥራው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ባንኮችንም በቅርቡ ወደዚህ ሥራ በማስገባት ለዓመታት የዘለቀው የሥራ ግንኙነታችን ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ማዕከላዊ ስታትስቲክስን መረጃ ዋቢ ያረጉት ይናገር (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከ10.5 ሚሊዮን በላይ ቤተሰብ በበቆሎ ምርት ላይ ሕይወቱ የተመሠረተ ሲሆን፣ 2.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ይመረታል፡፡ ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች በቆሎን እንደሚያመርቱ ማሳያ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ብቻ በአገራችን 83.9 ሚሊዮን በላይ ኩንታል በቆሎ ተመርቷል፡፡ እነዚህ መረጃዎች የሚያሳዩትም የበቆሎ አምራች አርሶ አደሩን አቅም የማጠናከር ሥራዎች ለአገር አቀፍ ኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ባንኮችም የተለያዩ የግብርና ምርቶች የብድር ሥርዓት እያመቻቹ ይገኛሉ፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም አርሶ አደሩ በምርቱ ላይ ለሚደርስበት ጉዳት የዋስትና ሥርዓት ገንብተዋል፡፡ እነዚህ ለአርሶ አደሩ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩ ዕድሎች ናቸው፤›› በማለት ይህ ብቻውን ግን በቂ አለመሆኑም ይናገር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት አስይዘው የሚበደሩበትን ሥርዓት በመፍጠር በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በሚያጋጥማቸው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ለበርካታ ወራት ደክመው ያገኙትን ምርት በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ከመሸጥ ማዳንና ገቢያቸውን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ ይናገር (ዶ/ር) ጨምረው የገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከ2013 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ የሚደረግ የአሥር ዓመት የብልጽግና ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑንና ለዚህ ዕቅድ ዝግጅትና ተግባራዊነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት የሚያስፈልግ እንደሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመንግሥት ከተሰጠው አገራዊ ተልዕኮ አንፃር ለወጪ ንግድ ዕድገት ያለውን የማይተካ ሚናውን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ አገልግሎቱን ለማሻሻልና አዳዲስ የሥራ መስኮችን ለመጀመር ትኩረት መስጠት የሚያስፈልግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት 12.46 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን 237,309 ቶን የተለያዩ ምርቶችን አገበያይቷል፡፡ ይህ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዋጋ 19 በመቶ በመጠን 27 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ በምርት ገበያው የተገበያየው ቡና ከአጠቃላይ ግብይቱ በመጠን 51 በመቶ፣ በዋጋ 70 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡
ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ መገንዘብ እንደሚቻለው አሁን ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በቅድሚያ ሥራ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 11 ዓመታት ከ308 ቢሊዮን ብር በላይ ለአቅራቢዎች ክፍያ የፈጸመ ነው ተብሏል፡፡