የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች በአስገዳጅነት ሲተገብሩት የነበረውን የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ ካነሳ በኋላ፣ ባንኮች ለብድር ያስከፍሉ የነበረውን የወለድ ምጣኔ እየቀነሱ ሲሆን፣ ኅብረት ባንክም እስከ 4.5 በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔውን መቀነሱን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ከሚያደርገው ከዚህ ውሳኔ ጎን ለጎን ከሌሎች ባንኮች በተለየ ከ27 በመቶ መመርያ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ አድርጎ የነበረውን የሦስት በመቶ የብድር ቅጣት አብሮ ማንሳቱንም አስታውቋል፡፡
ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መነሳት የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም፣ እንደየቢዝነስ ዘርፉ እስከ 4.5 በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔውን በመቀነስ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ መተግበር ይጀምራል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የ27 በመቶው የቦንድ ግዥ መመርያ ተግባራዊ በሆነባቸው ወቅቶች አንድ ተበዳሪ የወሰደውን ብድር እመልሳለሁ ብሎ ከተቀመጠው ገደብ በታች በሆነ ጊዜ የሚመልስ ከሆነ፣ የሦስት በመቶ ቅጣት እንዲከፍል ይደረግ የነበረውን አሠራር ሙሉ ለሙሉ አንስቷል፡፡
ሦስት በመቶ ተሠልቶ ይከፈል የነበረው ቅጣት ተበዳሪው ላይ ይፈጥር የነበረውን ጫና ያስቀራል የሚለው የኅብረት ባንክ መረጃ፣ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ግን ከብድር አመላለስ ጋር ተያይዞ ይጣል የነበረውን የሦስት በመቶ ቅጣት በማንሳት ይሠራል፡፡
ባንኮች ይህንን ቅጣት መተግበር የጀመሩት የ27 በመቶው የቦንድ ግዥ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ደንበኞች ብድራቸውን ከጊዜው በፊት ሲከፍሉ ባንኮች ማግኘት የነበረባቸውን ጥቅም እያሳነሰው ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኅብረት ባንክ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ መሠረት፣ ከፍተኛው የብድር ወለድ ምጣኔ የሚያደርገው ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ለሚሰጡ ብድሮች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡