Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመጀመርያው የአውቶቡሶችና የታክሲዎች የጉዞ ዕቅድ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

የመጀመርያው የአውቶቡሶችና የታክሲዎች የጉዞ ዕቅድ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

ቀን:

በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የአውቶቡሶችና የታክሲዎች የጉዞ ዕቅድ መተግበሪያ ዲጂታል ካርታ፣ ዓርብ ታኅሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ይፋ ሆነ፡፡

የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ ዲጂታል ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ከዓለም ሀብት ድርጅት (World Resource Institute) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተመተባበር ይፋ ያደረጉት ይህ መተግበሪያ፣ የጂፒኤስ ሲስተም ያላቸው ስማርት ስልኮችን  በመጠቀም የአንበሳ የከተማ አውቶብስ፣ የሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት፣ እንዲሁም የሚኒባስ ታክሲዎችን መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ አካባቢዎችን ጠቋሚ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መተግበሪያው ይፋ ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የአዳዲስ አካባቢዎች መፈጠርና የአዳዲስ የጉዞ መስመሮች መጀመር የአውቶብስና የታክሲ መስመሮችን ለማወቅና ለመጠቀም ፈታኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹ይህንን ችግር ለመፍታት ከናይሮቢ (ዲጂታል ማታቱስ) እንዲሁም ከካይሮ (የካይሮ ትራንስፖርት) ተሞክሮ በመውሰድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት የጉዞ ዕቅድ መተግበሪያ ካርታ (ዲጂታል ማፕ) ላይ በማስፈር ከጥቂት የአፍሪካ ከተሞች ጋር ተቀላቅለናል፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

የዓለም ሀብት ድርጅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በመሆን፣ የመተግበሪያውን ቴክኒካዊ ድጋፍ እንዳደረገ ወ/ሮ ዳግማዊት አክለዋል፡፡

 ‹‹በሒደቱ ከ90 በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ከ40 በላይ የትራንስፖርት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ ይህም የፕሮጀክቱን ቀጣይነትና ትራንዚት ዳታ የመሰብሰብ፣ የመተንተንና የመጠበቅ ዘላቂነቱን ከማረጋገጥ አንፃር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የትራንስፖርት መረጃ በካርታ (በወረቀት መልክ) መሥራት የተዘወተረ ሲሆን፣ በቦታዎች ስም መለዋወጥ፣ በከተሞች በፍጥነት ማደግና መቀየር የተነሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ መረጃዎቹ ያረጁና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው እያለፈባቸው ሲሄዱ እንታዘባለን፤›› በማለት፣ ይህንን ችግር ለመፍታት በዲጂታል የታገዘ የትራንዚት ዳታ መኖር መረጃን ሁልጊዜ አዲስ እንደሆነ ለማቆየት፣ ወቅታዊ ለማድረግ፣ ለሚፈለገው ዓላማ ለመጠቀምና ለተለያዩ አካላት ለማጋራት ቀላል በመሆኑ ተግባራዊ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የጉዞ ዕቅድ መተግበሪያው ለሁለት ዓላማዎች ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተገልጿል፡፡ የመጀመርያው አንድ ግለሰብ ከአንድ ነጥብ ተነስቶ ወደ ሌላ ነጥብ መሄድ ከፈለገ የጉዞ ዕቅድ ካርታውን በመመልከት ለመተርጎም ጥቅም ላይ ሊያውለው ይችላል፡፡ ይህም ግለሰቡ ባለበት ቦታ ላይ ሆኖ መተግበሪያውን ለመጠቀም፣ እንዲሁም ያለበትን ቦታ ለማመላከትና ወደ መዳረሻ ቦታው ለመድረስ የሚፈጅበትን ጊዜና ርቀት ያሳየዋል፡፡ ሁለተኛው ጠቀሜታ የደርሶ መልስ መስመር ትግበራው (አፕሊኬሽኑ) ከአንድ ነጥብ ወደ ነጥብ የሚጓዝበትን መስመር የሚያሳይ ነው፡፡ አውቶብስ፣ ሚኒባስ ወይም ቀላል ባቡር በምን ሰዓት መድረስ እንደሚችል የሚያመላክት መሆኑ ተገልጿል፡፡

መተግበሪያው የደርሶ መልስ የጉዞ ክፍያና የኦፍላይን አገልግሎትን  እንደሚያካትትም ታውቋል፡፡ የሞባይል መተግበሪያው ለጊዜው በአዲስ አበባ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች እንደሚስፋፉ ተገልጿል፡፡

መተግበሪያውን በማዘጋጀት ወቅት መረጃ የመሰብሰብ ችግር ትልቅ ተግዳሮት እንደነበር የገለጹት አቶ ምትኩ አስማረ ሲሆኑ፣ ታክሲዎችና አውቶቡሶች ከየት ተነስተው የት ነው የሚደርሱት የሚለውን ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር አውስተዋል፡፡

እንደሳቸው ገለጻ የመረጃ ስብስቡ የተካሄደው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከውጭ ድርጅቶች ሥልጠና እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡

ሁለት ዓመት እንደፈጀ የተገለጸው ይህ መተግበሪያ፣ መረጃ  በማሰባሰብ ሒደት የ504 የታክሲና የ124 የአውቶቡስ መስመሮች መካተታቸው ተገልጿል፡፡

መተግበሪያው ‹‹የኔ ጉዞ›› የሚል ስያሜ ሲኖረው፣ ከታኅሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በፕሌይ ስቶር ላይ ማግኘት እንደሚቻል ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...