Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየተጠናከረ ንቅናቄ የሚጠይቀው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሥርዓት

የተጠናከረ ንቅናቄ የሚጠይቀው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሥርዓት

ቀን:

ለጤና አገልግሎት የሚወጣ ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቷል፡፡ የዓለምና የአገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚያሳዩትም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ግለሰብ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል በሚያጋጥመው ጊዜ የሕክምና ወጪው የሚሸፈንበት ሥርዓት የጤና መድን  ተዘርግቷል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሚዛን ኪሮስ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በተደረጉ ጥናቶች የጤና እክል ካጋጠማቸው ሰዎች መካከል 20 በመቶ ያህሉ የጤና ወጪን መሸፈን ስላልቻሉ ወደ ጤና ተቋማት አልሄዱም፡፡ ወደ ጤና ተቋማት ከሄዱትም መካከል ሁለት በመቶ የሚሆኑት የጤናው ወጪ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡

ሁለት በመቶ በቁጥር ደረጃ ሲታይ ትንሽ ሊሆን እንደሚችል፣ ነገር ግን ያለውን የሕዝብ ብዛት ታሳቢ ተደርጎ ሲሰላ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፍተኛ ወጪ ከዛም አልፎ ለድህነት እንደተዳረጉ፣ ለዚህ ዓይነቱ እክል ብቸኛው መፍትሔ ሁሉም ኅብረተሰብ የሚገለገልበት ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሥርዓት (ማአጤመ) መዘርጋት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

- Advertisement -

በዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑትም በዋነኛነት መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ዘርፍ የተሰማሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ናቸው፡፡

ይህ የጤና መድን ሥርዓት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ በ2003 ዓ.ም. እንደተጀመረ፣ የተገኘውን ልምድም በመቀመር እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በተጠቀሱት ክልሎች በሚገኙ 509 ወረዳዎች ሥርዓቱ ሊስፋፋ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ በወረዳዎቹ የሚኖሩ ከ22.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች በጤና መድን ሥርዓቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጤና መድን ሥርዓቱ ከታቀፉት ውስጥም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ዓመታዊ የጤና መድህን መዋጮአቸውን መክፈል የማይችሉ ከአምስት ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የጤና መድን መዋጮአቸው በመንግሥት እንዲሸፈንላቸው መደረጉን ዶ/ር ሚዛን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከዚህም ሌላ በ2011 በጀት ዓመት ከማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የአባላት መዋጮ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን፣ አባላትና ቤተሰቦቻቸው በመድኑ ላገኙት የሕክምና አገልግሎት ከ617 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸማቸውን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት፡፡

ኤጀንሲው ኅብረተሰቡን የማአጤመ ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ያለው አፈጻጸም መልካም መሆኑን፣ እንዲሁም በመጪው ዓመት የሚኖረውን ተደራሽነትንም ወደ 645 ወረዳ፣ የተጠቃሚውን ቁጥር ደግሞ ወደ 30 ሚሊዮን የማሳደግ ሐሳብ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቅምት እስከ ኅዳር፣ በቀሩት አራት ክልሎች ከታኅሣሥ እስከ ጥር የሚተገበር መርሐ ግብር ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ መርሐ ግብሩም የሚያተኩረው የነባር አባላትን ዕድሳትና አዳዲስ አባላትን ወደ ጤና መድኑ የማስገባት እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡  ሥርዓቱ ከተተገበረባቸው ክልሎች የሚገኙ ዜጎች ግን ለጤና መድን አባልነት የሚጠበቀውን ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል እንዲመዘገቡ፣ አባል የሆኑ ዜጎችም አባልነታቸውን በማደስ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ሥርዓቱ ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑና ከዚህም ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ጥቅሙን እስከሚረዳው ድረስ ነው፡፡ የዓለም ተሞክሮ የሚያሳየው ግን ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሥርዓት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የውዴታ ግዴታ መሆን ይገባዋል፡፡ ለዚህም ከመጪው ዓመት በኋላ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሥርዓቱ ተስፋፍቶ ሁሉም የሥርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ አዋጅና የሕግ ሰነድ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

ለሥርዓቱ ትግበራ ስኬት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ክልሎች፣ የጤና ሴክተር ባለድርሻ አካላት፣ ዞኖችና ወረዳዎች ነዋሪዎቻቸውን በጤና መድን ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩትን የንቅናቄ ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛን አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...