Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ባንክ ከታክስ በፊት ከ695 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር በ2011 የሒሳብ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ በ45 በመቶ በማደግ 695.5 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገለጸ፡፡

ባንኩ የ2011 ዓመት የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው፣ ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠን 539 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ባንኩ የሒሳብ ዓመቱ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር የሚያመላክት ሲሆን፣ በተለይ በሁሉም የተቀማጭ ሒሳብ ዓይነቶች 4.8 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉ ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 16.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ይህም የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ አፈጻጸሙ ከቀዳሚው ዓመት በ41 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡

የደንበኞቹንም ቁጥር ከ794 ሺሕ በላይ ያደረሰው ባንኩ፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ዕድገት ያሳየበት ሌላው አፈጻጸሙ ደግሞ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎ ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ በ86 በመቶ ማሳደጉ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ 218.9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አግኝቷል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠንም ወደ 11.6 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥ 3.8 ቢሊዮን ብር አበድሯል፡፡ በብድር አመላለስ ረገድም በሒሳብ ዓመቱ 3.5 ቢሊዮን ብር ተመላሽ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደሚችልም ገልጿል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የገቢ መጠኑም በ50 በመቶ ማደጉን የሚያመላክተው የባንኩ ሪፖርት፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት 2.3 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ከባለፈው ዓመት በ772 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ49 ሺሕ በላይ ማድረስ መቻሉም ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 20.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ ካፒታሉና ሕጋዊ መጠባበቂያ ገንዘብ 2.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ቋሚ ንብረት ከመፍጠር አንፃር በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ በ1,352 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ G+8 ሁለገብ ሕንፃ በሃራጅ ጨረታ በ470 ሚሊዮን ብር አሸንፎ የገዛ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ባንኩ ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በቅርቡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ያፀደቀለትን ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኝ 3‚005 ካሬ ሜትር ቦታ ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ባንኩ ቦታውን ሲረከብ ለዋና መሥሪያ ቤት የሚውል የከተማዋን ደረጃ የጠበቀ ሕንፃ እንደሚገነባም ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ በሊዝ በተረከበው 2‚000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሕንፃ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት 247 ቅርንጫፎች ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን፣ የባንክ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድግ ቅርንጫፎቹ ባልተደረሰበት አካባቢዎች በመለመላቸው 1,756 የኤጀንት ባንኪንግ ወኪሎችና ‹‹አንበሳ ሄሎ ካሽ›› በተሰኘ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት አማካይነት ከ202‚834 ለሚበልጡ ደንበኞችን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች