የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዳግም አልወዳደርም አሉ
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ የነበረበትንና የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ ዘንድሮም ጊዜውን ጠብቆ ሊካሄድ አለመቻሉ እያነጋገረ ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በበኩሉ፣ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን ያላካሄድኩት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ነው ይላል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. ማካሄድ የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔና የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ እስካሁን ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ሳይካሄድ መቆየቱ አግባብ ያለመሆኑን የሚገልጹ ወገኖችም፣ ቀድሞም ቢሆን በወቅቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ዝግጅት አልነበረም በማለት ይሞግታሉ፡፡
ከሁለት ወራት በፊት የንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ከተገለጸ በኋላ፣ የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት እስካሁን አለመካሄዱ አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡ አሁንም በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ከደንብና ከሕግ ውጪ የሆነ አሠራር ስለመኖሩ ያሳያል በማለት እኚሁ ሁኔታውን የሚከታተሉ ወገኖች ይወቅሳሉ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በወቅቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ያለማድረጉ ሕጋዊ ካለመሆኑም በላይ፣ አባል ምክር ቤቶችም ይህንን ክፍተት እንዲታረም ያለማድረጋቸው አግባብ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡ የአገልግሎት ዘመኑን ካጠናቀቀ ወራት ያስቆጠረው የንግድ ምክር ቤት፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ያላካሄድኩት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ነው ማለቱንም አይቀበሉም፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም በተለይ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ብዙ ውዝግቦችን የሚታዩበትና በዚሁ ሰበብ ጠቅላላ ጉባዔውን በወቅቱ ማድረግ ሲቸገር እንደነበር የሚያስታውሱት እኚሁ ምንጮች፣ አሁንም ከሕግ ውጪ የምርጫ ዘመኑ የተጠናቀቀ ቦርድ ኃላፊነቱን ይዞ መቆየቱ ግልጽ ያለመሆኑን ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ዕዘዘው (ኢንጂነር) በዚሁ ጉዳይ ላቀረብንላችሁ ጥያቄ ሲመልሱ፣ እርሳቸው የሚመሩት ቦርድ እስከ ኅዳር 2012 መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነበር ይላሉ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድም ሆነ ምርጫውን ለማስፈጸም ምንም የቸገረን ነገር አልነበረም በማለትም ያክላሉ፡፡ ሆኖም ከአንድ ወር በፊት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባዔው ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይካሄድ በማለቱ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ አሁን ጉዳዩ በእንጥልጥል ላይ መሆኑን በመግለጽ የጠቅላላ ጉባዔው የሚካሄድበት ቀን ወደፊት የሚገለጽ እንደሆነም ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲዘገይ እንደ ምክንያት ያቀረበው ከደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ነው ተብሏል፡፡ ይህም ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ሌሎች ሒደቶችን ለማካሄድ ባለመቻሉ፣ እኔ በሌለሁበት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ መካሄድ የለበትም ከሚል አቤቱታ ጋር የተያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲራዘም በማሳሰቡ፣ የጠቅላላ ጉባዔውን ለማዘግየት ስለመገደዱ የአቶ መላኩ ገለጻ ያስረዳል፡፡
ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጻፈ የተባለው ደብዳቤ ለሁሉም አባል ምክር ቤቶች ያሳወቁ መሆኑንም የገለጹት አቶ መላኩ፣ እርሳቸው ለአባል ምክር ቤቶች የጻፉት ደብዳቤ ይዘት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ማሳሰቢያ በመንተራስ የተጻፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ በቅድሚያ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶችና ማኅበራት በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 እና በተሻሻለው የአገራዊ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ድንብ ቁጥር 03/2011 ንዑስ አንቀጽ 5 እና 6 መሠረት ጉባዔቸውን ካካሄዱ በኋላ የአገራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚካሄ ይታወቃል፡፡
‹‹ሆኖም የደቡብ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በክልሉ ተነስቶ በነበረው የሲዳማ ዞን በክልል የመደራጀት ጉዳይና በክልሉ ባለው የፀጥታና ሰላም መደፍረስ ችግሮች የተነሳ ጉባዔውን ማካሄድ አለመቻሉን ገልጾ፣ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በደብዳቤ አሳውቀው ነበር፤›› ይላል፡፡
በዚህም መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በቁጥር 03-14/8297 በሰጠው ምላሽ ሁሉም አባል ምክር ቤቶች ምርጫ ሳያካሂዱ በተለይም የደቡብ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያልተሳተፉበት ምርጫ ማከናወን በአገር አቀፍ ምክር ቤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጠጥርና የጋራ ምክር ቤትነቱ ላይ ጥያቄ የሚስነሳ እንደሆነ አቶ መላኩ የጻፉት ደብዳቤ ይጠቅሳል፡፡ አያይዞም ስለዚህ በደቡብ ክልል የተፈጠሩ ችግሮች እስከሚቀረፉ ድረስና የደቡብ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሕጋዊ መንገድ ምርጫቸውን በማካሄድ ተወካዮቻቸውን መሰየማቸው እስኪረጋገጥ፣ እንዲሁም ምርጫ ያላከናወኑ ሌሎች አባል ምክር ቤቶች ምርጫ ማከናወናቸው ከተረጋገጠ በኋላ አገራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን እንዲያካሂድ ተገልጿል፤›› በማለት ያክላል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ ማሳረጊያም አገራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም እንዲደረግ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር የተወሰነ መሆኑን አባል ምክር ቤቶቹን እናሳውቃለን፤›› የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ ለማወቅ አሁንም የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ምላሽ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንዳለው በኅዳር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ ጉባዔው ያካሄዳል ቢባል እንኳን፣ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት ያለመኖሩን የሚሞግቱና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ፣ የደቡብ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ንግድ ምክር ቤቶችም ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ያላካሄዱ በመሆናቸውና አሁንም ባለማካሄዳቸው ኅዳር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ነበር የተባለው ጉባዔም ይካሄድ እንዳልነበር ያስታውሳሉ፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ምክር ቤቶች ከሁለት ወራት በፊት በፊናቸው ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አድርገው በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ የሚገኙ ተሳታፊ ተወካዮችን ባላሳወቁበት ሁኔታ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማሳሰቢያ እንዲራዘም ተደርጓል የሚለው ነገር እንደ ሰበብ የቀረበ ነው ይላሉ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን በወቅቱ ለማካሄድ ቢፈለግ፣ ከደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውጪ ያሉ ምክር ቤቶች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያጠናቅቁ ማሳሰብ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ ያለመሆኑ አሁንም የንግድ ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔያችሁን አድርጉ ቢል እንኳን ጠቅላላ ጉባዔን ለማካሄድ ወራት ይፈጃል በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ጉባዔውና ምርጫው ለመራዘሙ ምክንያት የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በገጠመው ችግር ጉባዔውን አለማሄዱ ሊያሳምን ቢችልም፣ የአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤቱን ጉባዔና ምርጫ ላለማካሄድ እንደ ምክንያት መቅረቡም ያከራክራል፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ቢሆን ጉዳዩን እንዴት ተመልክቶ ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዳደረሰ ግልጽ እንዳልሆነላቸው የገለጹም አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የክልል ንግድ ምክር ቤቶች እስካሁን ጠቅላላ ጉባዔ ያለማካሄዳቸው ሁኔታው እየታወቀና በአንድ ምክር ቤት ጥያቄ የአገር አቀፍ ጉባዔ እንዲራዘም ሆኗል መባሉም አነጋጋሪ ሳያደርግው አልቀረም፡፡
አሁን አመራር ላይ ያለው ቦርድ ኃላፊነቱን ሲወስድ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለመሥራት ጭምር እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፣ በተግባር ግን አሁንም የሕገ ደንብ ጥሰቶች እየተስተዋሉ እንደሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ መላኩ ግን በዚህ የማይስማሙ ሲሆን፣ ባለው ደንብ መሠረት እየሠሩ መሆኑ ሁኔታውም ከዚህ በተለየ መታየት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አዳዲስ አመራሮችን የሚመረጡበት የዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔ መቼ እንደሚደረግ መገመት ባይቻልም፣ ውሳኔ አሁንም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እጅ እንደሆነ በመግለጽ ሚኒስቴሩ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄዱ ሲል ይደረጋል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ መላኩ በቀጣዩ ምርጫ ለውድድር እንደማይቀርቡ ገልጸዋል፡፡ ከጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት በመምራት የቆዩት አቶ መላኩ፣ በቀጣዩ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን በሚደረግ ምርጫ መወዳደር ያልፈለጉበትን ምክንያት ባይጠቅሱም፣ ‹‹በቃኝ›› ብለዋል፡፡
ቀደም ብሎ በነበሩ የምርጫ ወቅቶች ንግድ ምክር ቤቱን ለመምራት የሚሹ ወገኖች ይታወቁ የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን ይህ ባይስተዋልም የአቶ መላኩ አልወዳደርም ማለት ንግድ ምክር ቤቱ አዲስ ፕሬዚዳንት እንደሚኖረው የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡